! ……. የትግራይ ሥጋት (On the Fear of Tigray) ….!

ጥያቄ

“ኢህኣዴግን ትቃወማለህ፣ ግን ህዝብን ለለውጥ ኣነሳስተህ ከህወሓት የባሱ እንደነ ግንቦት ሰባት ስልጣን ቢይዙስ ??? ስትቃወም ስለዉጤቱም ማሰብ ኣለብህ። የምትፅፋቸውን ነገሮች ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የምታውቅ ኣይመስለኝም። ኣውቀህ ፃፍ። (የትግራይ ተወላጅ)

መልስ

ሁሉም ዜጋ (የገዢው ፓርቲ ደጋፊም ተቃዋሚም) መጠየቅ ያለበት (የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ ባህሪያዊ ሂደት መሆኑ ተገንዝቦ) በኢህኣዴግ እጅ ያለው ስልጣን (በለውጡ ሂደት) ‘ለማን ይሰጥ’ የሚለውን ነው። ሁለት ስልጣን ለመቀበል ያሰፈሰፉ ሃይሎች ኣሉ፤ (1) የኢትዮዽያ ህዝብና (2) ስልጣን በሃይል ለመያዝ የጓጉ የፖለቲካ ቡድኖች።

ኣንድ

እኔ ታድያ ‘ስልጣን ለኢትዮዽያ ህዝብ መሰጠት ኣለበት’ ከሚሉ ሰዎች ጎራ ነኝ (የምቃወምም ለዚህ ነው)። ምክንያቱም ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ዲሞክራሲን ማስፈን ነው። በዲሞክራሲያዊ መንግስት ህጋዊ ተቃዋሚዎች ይበረታታሉ፣ ኣማራጭ ፖሊሲያቸው ለህዝብ እንዲያቀርቡ ነፃ ሚድያ ይኖራል። ህዝቦች በነፃነት የፈለጉትን ፓርቲ ይመርጣሉ፤ ድምፃቸውም በገለልተኛ የምርጫ ቦርድና የፍትሕ ኣካላት መኖር ይከበራል። የህዝብ ድምፅ ከተከበረ ሲቪላዊ መንግስት የማቋቋም ዕድል ይኖራል። በዚ መንገድ በሃይል ስልጣን ለመያዝ የሚቋምጡ ሃይሎች ቦታ ኣያገኙም።

ዲሞክራሲ ማስፈን የብዙ ችግሮች መፍትሔ ይሆናል። የኣፍርሶ መገንባት ስትራተጂ ዕዳ ይቀንሳል። ደም ማፋሰስ ያስወግዳል። ኧረ ሲንቱን …… ህወሓት/ኢህኣዴግ ኣሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ማድረግ የሚችለው ትልቁ ኣስተዋፅኦ ዲሞክራሲን በማስፈን ስልጣን ለህዝብ ማስረከብ ነው። የትግራይ ህዝብ ትግልም ለውጥ ኣመጣ እንላለን።

ሁለት

ህወሓት ኢህኣዴግ የያዘውን ስልጣን በፍቃደኝነት (በምርጫ) ለህዝብ ካላስረከበ በሃይል እስኪወርድ ድረስ በስልጣን ይቆያል ማለት ነው። ይህንን የሚያሳየን ህወሓት ስልጣኑን ለሌላ ታጣቂ (ተዋጊ) ሃይል እንጂ ለህዝብ ለመስጠት ፍላጎት የለዉም ማለት ነው።

ሌላ የታጠቀ ሃይል ስልጣን ከያዘ ሌላ ህወሓት /ኢህኣዴግ መጣ ማለት ይሆናል። ምክንያቱም ስልጣን በሃይል ለመያዝ ሰው መግደልን ጨምሮ ሌሎች የተወሰኑ ወንጀሎች ይሰራሉ፣ ግድያ ይኖራል። (ሃይል ስንጠቀም ወንጀሎችም ይኖራሉ ኣለበለዚያ ግን ለውጡ በሃይል ሳይሆን በሰለማዊ መንገድ ነው ማለት ነው)። እነዚህ የተወሰኑ ወንጀሎች ለመሸፈን ሲባል ሌሎች ተጨማሪ ወንጀሎች ይፈፀማሉ። እነዚህ ወንጀሎች እንዳይጋለጡ ለማድረግ (ጉዳቸውን እንዳይወጣ) ስልጣን የያዘውን የፖለቲካ ቡድን የራሱ ዳኞች፣ ወታደራዊ መኮነኖች፣ የደህንነት ሃላፊዎች ወዘተ ይኖሩታል።

ከተሸናፊው የፖለቲካ ድርጅት ደህንነታዊ ስጋት በመስጋትም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በጠላትነት ይፈርጃል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችም ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ሌላ የኣደረጃጀት ኣማራጭና የፖለቲካ ስልት ያፈላልጋሉ። የሃገር ኣንድነትም ኣደጋ ላይ ይወድቃል።

ስልጣን ላይ የወጣ ሃይል ድክመቱን ለመሸፈን ሲል የሚጠራጠራቸውን ህዝቦች ለመቆጣጠር (የመገንጠል ጥያቄን በሃይል ለመመለስ) እንዲችል ኣሻንጉሊት ድርጅቶችን ያቋቁማል። ይህንን ሁኔታ ሌላ ኢህኣዴግ ያደርገዋል። እኛ ደግሞ “ኣዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ …” እንዘፍናለን።

ሦስት

በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ህዝቦችን የመጨቆን ዕድሉ ይቀንሳል። ምክንያቱም ፖለቲከኞቹ ከወንጀል ነፃ የመሆን ዕድል ኣላቸው። (ከወንጀል ነፃ ካልሆኑ ኣይመረጡማ) ወይም ከስልጣናቸው ለማውረድ ቀላል ይሆናል። እነሱም ከስልጣን መውረድን የሞትን ያህል ኣይፈሩም (በህዝብ የተመረጡ ናቸዋ)። ስልጣን ላለመልቀቅ ኣያንገራግሩም (ህዝቡ ሰልፍ ይወጣላ)። መሪዎቹ ሰልፍ ለወጣ ህዝብ እንዲገድሉ ወታደሮቻቸውን ኣያዙም። ምክንያቱም በፖለቲከኞችና ወታደሮች መሃከል (ህገ መንግስታዊ ከሆነ በቀር) ልዩ ግንኙት ኣይኖራቸውም።

በህዝብ የተመረጡ መሪዎች ተጠያቂነታቸው ለመረጣቸው ህዝብ ይሆናል (የስልጣን ምንጫቸው ህዝብ ነውና)። ስልጣን የያዙት በሃይል ከሆነ ግን ተጠያቂነታቸው ለጠመንጃቸው ነው። የህዝብ ጉዳይ ኣያሳስባቸውም። ስልዚ የኔ ጉዳይ የዲሞክራሲ ጥያቄ እንጂ ኣንድ በስልጣን ላይ ያለው ድርጅት በሌላ እንዲተካ ለማስቻል ኣይደለም።

ኣራት

ኢህኣዴግን መቃወም ለምን???

(ኣንደኛ) ገዢው ፓርቲ ስልጣን ወደ ህዝብ እንዲመልስ ለማገዝ ነው። የህዝብን ድምፅ ኣላከበረም፣ ህዝብ እየገዛ እንጂ እያስተዳደረ ኣይደለም ያለው። ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንፈልጋለን። የሁሉም ህዝቦች ደህንነትና ልማት የሚረጋገጠው ዲሞክራሲያዊ ነፃነት ሲፈቀድ ነውና።

(ሁለተኛ) ኢህኣዴግ ችግሮቹን እንዲያርም ለማድረግ ነው። የመናገር መብት ያፍናል፤ ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም ሌሎች ህዝቦች ይጨቁናል፤ ለራሱ ጥቅም ሲባል ኣሻንጉሊት ድርጅቶች በማቋቋም (ብኣዴን ለኣማራዎች፣ ኦህዴድ ለኦሮሞዎች ….) የሚገዙትን ህዝብ የማይወክሉ መሪዎች በኣስገዳጅነት እንዲገዙ ያደርጋል። እነዚህ ህዝቦች ራሳቸው ይወክሉናል ብለው በመረጡዋቸው ድርጅቶች መተዳደር ኣለባቸው። ህዝቦች በሚወክሉዋቸው መሪዎች ሲተዳደሩ የትግራይ ህዝብ ቢጠቀም ነውጂ ኣይጎዳም።

(ሦስተኛ) ለውጥ ፈልገን ነው። ለውጥ የመፈለግ ኣባዜ የተፈጥሮ ጥሪ ነው። እያንዳንዱን ትውልድ የራሱ/ለራሱ የሆነ ለውጥ የማምጣት ወይም የማድረግ የግል የቤት ስራ ኣለው። የኣባቶቻችን ታሪክ ለኛ (የኛ) ሊሆን ኣይችልም። ስለዚ ለውጥ መፈለግ በራሱ ስሕተት ኣይደለም። ለለውጥ መነሳት የህይወት ግዴታችን ነው።

ኣምስት

የትግራይ ስጋት የሚመነጨው ከነዚህ ዲያስፖራ ፖለቲከኞች ከሚያራምዱት ኣስተሳሰብ እንደሆነ ተነግሮኛል። እነዚህ የ ‘ትግራይ ጠላቶች’ እንደሆኑ ተደርገው የሚታሰቡ ሃይሎች መነሻቸው ምንድነው ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

እነዚህ ሰዎች በኢህኣዴግ መንግስት በጠላትነት ተፈርጀው ‘ኣሸባሪ’ ተሰይመው ከሃገራቸው የተባረሩ ናቸው። ከሃገራቸው ከተባረሩ ታድያ እንዴት ለህወሓት ጥሩ ኣመለካከት ሊኖራቸው ይችላል? በህወሓት ዘመነ መንግስት ወደ ሃገራቸው እንዲገቡ ካልተፈቀደላቸው ሃገራቸውን ለመግባት ህወሓትን በሃይል ማስወገድ ግድ ሊላቸው ነው። ስለዚ ጥረታችው ኣይደንቀኝም።

ጥያቄው እነዚህ ሰዎች ለምን የትግራይን ህዝብ target ያረጋሉ የሚል ነው። መልሱ ግን ቀላል ነው። (1) ህወሓት ራሱ … ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ኣንድ እንደሆኑ ኣድርጎ ይሰብካል (ድጋፍ ለመሰብሰብ)።

(2) የዲያስፖራው የፖለቲካ ስትራተጂ ተደርጎ ይወሰዳል። የትግራይን ህዝብ target ሲያደርጉ የትግራይን ህዝብ ፈርቶ ህወሓትን ከመደገፍ ይቆጠባል ከሚል ኣስተሳሰብና ከትግራይ ህዝብ ውጭ ያለው ኢትዮዼያዊ ‘በኣንድነት በመቆም’ ህወሓትን ከስልጣን ለማውረድ እንዲነሳ ታስቦ ነው።

(3) ተሳዳቢዎቹ ዲያስፖራ ኣራት ዓይነት ናቸው።

(ሀ) የፖለቲካ ብቃት የሚያንሳቸው (ህዝብና ገዢው ፓርቲ መለያየት ያቃታቸው ወይም መለያየት ያልፈለጉ)። እነዚህ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ህወሓትን ያግዛሉ። የትግራይን ህዝብ ሲሳደቡ, የትግራይ ተወላጆችም ሳይፈልጉ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፉ ይገደዳሉ። ግን ስጋት ሊሆኑ ኣይችሉም ስልጣን ኣይዙምና (የፖለቲካ ዕውቀት ያንሳቸውል በሃይል ካልሆነ በቀር)።

(ለ) ወደ ሃገራቸው እንዳይገቡ የተከለከሉ (በሰለማዊ መንገድ እንዲታገሉ በህወሓት ያልተፈቀደላቸው)። እዚ ላይ ስጋት ፈጣሪው ህወሓት ራሱ ነው።

(ሐ) በሻቢያ ተልከው ኢትዮዽያን ለመበጥበጥ ተከፍሎቸው የሚሰሩ (ኣብዛኞቹ ኤርትራውያን ናቸው)። ኢትዮዽያውያን ካልተባበርናቸው የትም ኣይደርሱም።

(መ) የህወሓት ደህንነት ሰራተኞች (ኣብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ሁኖው ዲያስፖራውን ለመሰለል ተቃዋሚዎች መስለው እንዲታዩ በህወሓት የተላኩ ናቸው።) ከመሰለል ኣልፎም ትግራይና የትግራይ ተወላጆችም በመሳደብ የትቃዋሚዎችም ኣመኔታ ይገዛሉ (ከዛ ሚስጢር ያስተላልፋሉ)። ይህንን ስትራተጂ ዲያስፖራ ፖለቲከኞች ጥላቻ የሚሰብኩ ናቸው ተብለው እንዲፈረጁና የትግራይ ህዝብ እነሱን ፈርቶ ሰግቶ ከህወሓት ጎን እንዲሰለፍ ለማድረግ የታለመ ነው። ስለዚ ተጋሩን ከሚሳደቡ ብዙዎቹ የህወሓት ደህንነትና የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

ስለዚህ ጥላቻን የሚሰብኩ ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ሃገራቸውን እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ህዝባቸውን ለለውጥ እንዲያነሳሱ ቢደረግ የትግራይ ህዝብ የሚያዋሩዱበት ምክንያት ባኖራቸው ነበር። ስለዚ የትግራይ ስጋት ሆን ተብሎ በህወሓት የተቀናበረ ነው።

ስድስት

ስጋቱ ቢኖርስ??? መፍትሔው በእጃችን ነው። ሥጋቱን ለመቀነስ ራሳችን የሌሎች ህዝቦች ስጋት ፈጣሪ መሆን የለብንም። እንደ ኣሰራርም :

(1) ህወሓት በትግራይ ህዝብ ስም ሌሎች ህዝቦች መጨቆን እንዲሁም ስጋት መፍጠር የለበትም። (ካልጨቆነ ስጋቱ ኣይኖርም)። ከዚህ ኣልፎም የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮዽያ ህዝቦች በሰላም መኖር የሚፈልግ እንጂ የህወሓት የጥላቻ ፖለቲካ እንደማይደግፍ በግልፅ መናገር ኣለበት።

(2) ህወሓት ዲሞክራሲን ማስፈን ሲገባው የታጠቁ ሃይሎችን ወደ ስልጣን መጋበዝ የለበትም። ህወሓት ህጋዊና ሰላማዊ የተቃውሞ ድርጅቶችን ሲያዳክምና ሲያፈርስ ስልታቸውን ቀይሮው የሃይል መንገድ ተከትለው ከስልጣን እንዲያወርዱት እየጋበዛቸው ነው። ይህ ኣካሄድ ደግሞ ህወሓት በሌሎች ህዝቦች እንዳደረገው ሁሉ ኣሻንጉሊት ድርጅት መስርተው የትግራይን ህዝብ ለመጨቆን ያስችላቸዋል።

በመጨረሻም

እኔ ኣንድን ብሄር ወይ ፓርቲ ከስልጣን ለማውረድ ወይ ለማውጣት ኣልተነሳሁም (ኣልችልምም)። በኔ ኣቋምም ከህወሓት ‘የባሱ’ ሃይሎች ስልጣን ኣይዙም። ግፋ ቢል የራሳችውን ህዝቦች ነው የሚያስተዳድሩ። ትግራይን የሚያስተዳዱርበት መንገድ የለም። በህወሓት የሚሰጠን “እኔ ከሌለሁ ጅብ ይበላችኋል” ዓይነቱ ማስፈራርያ ግን ለትግራይ ህዝብ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው። ትግራይ የህወሓት ባለስልጣናት ብቻ ወልዳ የቀረች መኻን ኣይደለችም።

ባጠቃላይ የኔን ፅሑፍ የስጋት ምንጭ ሊሆን ኣይገባም።

Abraha Desta

It is so!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: