በአፋር ክልል ዞን አንድ “ኤሊዳኣልና ቢሩ “ በሚባሉ ወረዳዎች ከፍተኛ የሆነ ርሃብ መከሰቱ ተጠቆመ፡፡ በተለይ በሁለቱ ወረዳዎች ከመጋቢት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ የረሃቡ ሁኔታ እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ በአካባቢው ምግብና ውሃ በመጥፋቱ ለከብቶች መኖ “አብዳ” የሚባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሰጠውን ፉርሽካ ነዋሪዎች ጋግረው መብላት መጀመራቸውን ምንጮቻችን ከስፍራው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ነዋሪዎች ባለ25 ሊትር ውሃ እስከ 200 ብር እየገዛ ከመሆኑም በተጨማሪ በተከሰተው ርሃብ እስካሁን 7 ሰዎች መሞታቸውንም ከስፍራው የዓይን እማኞች ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በስፍራው ቢገኝም ባልታወቀ ምክንያት እስካሁን ምንም ዓይነት የዕርዳታ ድጋፍ ባለማድረጉ ባካባቢው ነዋሪዎች ቅርሬታ ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተነግሯል፡፡ የፌደራሉ አደጋ መካላከል ዝግጁነት አስተባባሪ መስሪያ ቤትም እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱ ተጠቁሟል፡፡
የዝግጅት ክፍሉም የአፋር ክልላዊ መንግስት በተጠቀሱ ወረዳዎች የተከሰተው ርሃብ ያደረሰውን ጉዳትና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ጠይቀን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መሐመድ “የደረሰውን ጉዳት ገና እያጣራን ነው፣ ልዑካንን ወደ አካባቢው ልከናል፤ አደጋ መከላከል መረጃውን ስላልሰጠን ባልተጣራ ጉዳይ ላይ መረጃ ልሰጥ አልችልም “ ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡