ብስራት ወልደሚካኤል
afrosonb@gmail.com
በኢትዮጵያ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር፡፡ የቀድሞው የሀገሪቱ ኢህዴሪ መንግስት (ደርግ) በነበረ ወቅት ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ይሰጥ የነበረው ግምት ከፍተኛ በመሆኑ በሀገሪቱ ያሉ ደኞች ከነ ዱር እንሰሳቱ ከፍተኛ ጥበቃ ይደረግላቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመንም ቢሆን ምንም እንኳ የአካባቢ ጥበቃ ምንነት በውል የታወቀ ባይሆንም በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ እና የዱር አራዊትም እንደልባቸው ይቦርቁበትና ቱሪስቶችም እንዳሻቸው ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ከደደቢት በረሃ የመጡት ታጣቂዎች ቡድን ህወሓት/ኢህአዴግ የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 1983ዓ.ም. ጀምሮ ያሉት የደን ሽፋኖች እጅግ እየመነመኑ ሄደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ በፊት 40% የነበረው የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 3% በመውረድ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ወደ 2.5% መውረዱን የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ለ21ዓመታት እስካሁንም በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ያለው አመለካከት እጅግ የወረደ በመሆኑ ቀደም ሲል በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ዙሪያ ያሉ ደኖች በካድሬዎች ፈቃድ ለገዥው አባላት ጊዜያዊ ጥቅም ሲባል እየተጨፈጨፈ ቦታው ለመኖሪያ ቤት ግንባታ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ለዚህም በአሁን ወቅት የአዲስ አበባን ሰሜንና ምዕራብ(ሳንሱሲ፣ ጉለሌ፣ሽሮሜዳ፣የካ…የመሳሰሉ በደን የተሸፈኑ አካባቢዎች) መመልከት በቂ ነው፡፡
በተለያየ ምክንያት ከፍተኛ የደን ክምችት ያለባቸው እንደ ባሌ ተራራዎች፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያሉ ደኖች እየተቃጠሉ ይዘታቸው ቢመናመንም መልሶ እምዲለሙ ሲደረግ አልተስተዋለም፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ብርቅዬ የዱር እንሰሳት ወደሌላ ሀገር እንዲሰደዱ ምክንያት በመሆን ሀገሪቱ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ በደኖቹ ዙሪያ ያሉ በግብርና ስራ( መሬት በማረስና እንሰሳት በማርባት)የሚተዳደሩ ገበሬዎች በአካባቢያቸው በተፈጠረው የተፈጥሮ መዛባት ምርቶቻቸው እየቀነሰ ወደ ከተማ እንዲፈልሱ አስገድዷቸዋል፡፡
ሌላው ለደኖች ውድመት ገዥው መንግስት ተጠያቂ ከሚሆንበት አንዱ የደን ውጤቶችን ለየ አካባቢው የገዥው ቡድን አመራሮች ሙስና መጠቀሚያ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ገንዘብ እንዲሸጡ መደረጉ ነው፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን አቅጣጫ 123 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረብርሃን አካባቢ ያለው ደን በ2004ዓ.ም. እያንዳንዱን ዛፍ በ40ሳንቲም ሂሳብ ለመሸጥ የዞኑና የከተማው መስተዳደሮች ከተስማሙ በኋላ በአካባቢው ማህበረሰብ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ አሁን ካሉት የደን ክምችቶችም ከተወሰኑ ብሔራዊ ፓርኮች በስተቀር አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ዙሪያ ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ንብረትነታቸው የመንግስት የሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን(የአሁኑ ኢትዮ ቴሌኮም) ለመስመር ዝርጋታ የሚያገለግላቸውን የምሰሶ እንጨት የሚጠቀሙት ከሀገሪቱ ደን በመቁረጥ ቢሆንም በቆረጡበት ምትክ ግን መልሰው ሲያለሙ አይታይም፡፡ ባለፈው 2004 ዓ.ም ደግሞ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ክልል ያሉ ከፍተኛ የደን ክምችቶች መሬቱን ለውጭ ባለሃብቶች ለመስጠት በሚል ተጨፍጭፈው ቢያልቁም መልሶ የተካም ሆነ ዜጎችን አፈናቅሎ ለባለሃብቶቹ ከመከስጠት ያለፈ ለምን ያለ የመንግስት አካል አልነበረም፤የለምም፡፡ ደኑን እንዲመነጠር የፈቀደትና ቦታውን የመሩት የፌደራሉ እና የክልሉ መንግስታት ናቸውና፡፡
በከተሞች ውስጥ ያለውን የተመለከትን እንደሆነ ዕፅዋቶች ሙሉ በሙሉ እንዲወድሙ ተደርጎ የድንጋይ ካብ ህንፃ ብቻ መገንባት እንደስልጣኔና እንደዕድገት እየተወሰደ በመምጣቱ ቀደም ሲል በየከተሞቹ የነበረው የአየር ፀባይ እንዲቀየር አስገድዶታል፡፡ እዚህ ላይ ስለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ አነስተኛ ግንዛቤ ያላቸው ደካማ መሪዎችን ፈለግ በመከተል ነዋሪዎችም የአካባቢውን ተፈጥሮ በማዛባት ትልቅ ሚና መጫወታቸው እሙን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ ላይ ያልተለመደ የአየር ፀባይ እየተስተዋለ ቢሆንም ገዥዎች የራሳቸውን ድክመት ሳይቀርፉ የተለመደውን የገንዘብ ሱስ ለመወጣት ሌሎች ላይ ምክንያት ሲደረድሩና የገንዘብ ካሳ ብቻ ሲያባርሩ ይስተዋላል፤ የቤታቸውን የአደባባይ የአካባቢ ጥበቃ ችግር ገመና ግን እየኖረ ያለው የሀገሬው ሰው የሚያውቅ ሐቅ ነው፡፡
የወሬ ዘመቻ የማይታክተው ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር 2000ዓ.ም.(ሚሊኒየም) ክብረ በዓል ወቅት እያንዳንዱ ሰው ችግኝ እንዲተክል ለማበረታታት በሚል የውሸት ዘመቻ ሁለት ዛፍ በሁለት ሺህ ሲባል ቢከርምም እንክብካቤ ተደርጎላቸው የፀደቁ ችግኞችና ዛፍ የሆኑትን ልናይ አልቻልንም፡፡ በርግጥ በወቅቱ ዓላማው የተፈጥሮ መዛባትን ከመከላከል አኳያ የሚበረታታ ተግባር ቢሆንም ኢህአዴግ በባህሪው ከወሬ ዘመቻ ባለፈ የተግባር ቁርጠኝነት ስለማይታይበት ይባሰ ያሉትም ደኖች እየወደሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ፕሮፖጋንዳ የተነዛበትና ከፍተኛ በጀት የፈሰሰበት “ሁለት ችግኝ ለሁለት ሺህ” የሚለው ፕሮጀክት ከወሬ ባለፈ የታሰበው ሳይሆን ይኸው 5ኛ ዓመት ላይ ደርሰናል፡፡
በአጠቃላይ ተፈጥሮን እያዛቡ ልማት ማምጣት የማይታሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፈጥሮን መንከባከብ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በደኖች ማልማት፣ በከተሞች የሚሰሩ ህንፃዎች በእያንዳንዳቸው ግቢ እንደየስፋታቸው መጠን ቢያንስ አምስትና ከዛ በላይ ዕፅዋቶችን(ዛፎች) እንዲተከሉ አስገዳጅ ህግ በማውጣት መተግበር ግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ተፈጥሮን በማዛባት ልማት ማምጣት ቅዥት ካልሆነ እውን ሊሆን ስለማይችል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮን መንከባከብ ከሰብዓዊ መብት ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡