! …. የኢህኣዴግ ኣጀንዳና የኣማራ ተወላጆች መፈናቀል …..!

 

አብርሃ ደስታ

(ከመቀሌ)

ህወሓት/ኢህኣዴግ ከሚከተለው ‘ኣብዮታዊ ዴሞክራሲ’ የተሰኘ የፖለቲካ ኣቅጣጫ (እነሱ ‘ርእዮተ ዓለም’ ይሉታል) ኣንፃር ‘የቡድን መብት’ ከ’ግል መብት’ ይቀድማል። በብዱን መብት እሳቤ መሰረት (በኣንቀፅ 39 የ’እስከመገንጠል መብት’ ታግዞ) ብሄሮች በየክልላቸው ያለ ሃብት (ለምሳሌ መሬት) በዋናነት እንዲቆጣጠሩ ያስችላል።

በዚ መሰረትም ‘የሌላ’ ክልል ተወላጆች በ’ሌላ ክልል’ መሬት የማግኘት መብታቸው ሲነፈጉ ይታያል። የኣማራ ተወላጆች ብዙ ግዜ ኑሮኣቸው ከመሰረቱበት ቀያቸው በኃልና በግፍ ሲፈናቀሉ እያየን ነው። በቡድን መብት መሰረት የኢትዮዽያ ሕጋዊ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው መኖርያ መሬት ሲከለከሉ ማየት እጅግ ያሳዝናል። በሌላ በኩል በስልጣን ያለ ድርጅት (የራሱን ዜጎች እያፈናቀለ) መሬ ታችን ተቀባይነት በሌለው መንገድ ለዉጭ ዜጎች ሲቸረችር ይታያል። ዜጎቻችን በገዛ መሬታቸው ባዕድ ሁነዋል ።

የሚገርመው ደግሞ ‘መሬት ኣይሸጥም ኣይለወጥም’ ከሚል ግራ የተጋባ ፍልስፍና መሬታችን ለውጭ ዜጎች የሚሰጠው በነፃ ሊባል በሚችል ሁኔታ መሆኑ ነው። (በነፃ የሚሰጥበት ምክንያት መሬት ተሸጠ እንዳይባል ነው)። የኣማራ ተወላጆች ከቀያቸው መፈናቀል የገዢው ፓርቲ የተሳሳተ ፖሊሲና ለህዝብ ያለው ንቀት የሚያሳይ ነው። ዜጎችን በማባረር (‘ሕጋዊ ያልሆኑ ኗሪዎች’ በሚል ስም) መሬት ለውጭ ዜጎች ሲሰጥ እነዚህ የሌላ ሀገር ዜጎች እንዴት ‘ሕጋዊ’ ሆኑ???

ሰዎች ከቀያቸው በሃይል (በግፍ በዘርሓረጋቸው እየተለዩ) ሲፈናቀሉ (ሲባረሩ) የከፋ የሰብኣዊ መብት ጥሰት ነው። ዜጎቻችን (ወገኖቻችን) ሲፈናቀሉ የሚደርሳቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ (Helplessness) መገመት ኣይከብድም። ሁሉም ኢትዮዽያ ሊተባበራቸው ይገባል፤ መንግስት ይህን ተግባሩ እንዲያቆም ተፅዕኖ ማድረግ ኣለብን።

እኛም እየተፈናቀሉ ካሉ ሰዎች ጎን መሰለፍ ያለብን ይመስለኛል። ምክንያቱም (1) ወገኖቻችን ናቸው። እኛ ኢትዮዽያውያን ያልደረስንላቸው ማን መጥቶ ይረዳቸዋል? (2) ዛሬ በኣማራ ተወላጆች እየተፈፀመ ያለው ግፍ (ኣሁንኑ ካልቆመ) ነገ በእያንዳንዳችን እንደሚፈፀም ማወቅ ይኖርብናል። (3) የማፈናቀል ተግባሩ የብሄር ፖለቲካ ችግር ኣባብሶ የጥላቻ ፖለቲካ ስር ሰዶ የኢትዮዽያ ሀገራችን ኣንድነት የሚፈታተን ይሆናል።

የስርዓቱ ደጋፊዎች ይህንን ችግር ተረድታቹ በገዢው ፓርቲ Pressure ፍጠሩ ፤ ኣለበለዝያ ግን ችግሩ ሁሉም ዜጋ ይነካል። በተለይ የትግራይ ተወላጆች በግልፅ ተቃውሞኣችንን ማሰማት ኣለብን። ህወሓት /ኢህኣዴግ ከተግባሩ እንዲቆጠብ ማድረግ ወይ ተግባሩ እንዲያቆም በመቃወም ከነዚህ ተፈናቃዮች ጎን መሰለፍ ኣለብን። ምክንያቱም እነዚህ ተፈናቃዮች ብዙ ችግር እንደሚደርስባቸው የታወቀ ነው። ቂም መያዛቸው (በገዢው ፓርቲ ቅር መሰኘታቸው) ኣይቀርም። ገዢው ፓርቲ (ኢህኣዴግ) የህወሓት ስራ መሆኑ ይታወቃል። ህወሓት ስልጣን መያዝ የቻለው በትግራይ ህዝብ ትግል ነው (ህወሓት ህዝቦች ማፈናቀል ወይ መጨቆን እንዲችል ለማብቃት ባይሆንም)።

ስለዚ የኣማራ ተፈናቃዮች በህወሓት ተግባር ምክንያት በትግራይ ህዝብ ቅር ሊሰኙ ይችላሉ። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ዛሬ በኣማራ ህዝብ እየተፈፀመ ያለው ግፍ ነገ በትግራይ ህዝብ መደረጉ ኣይቀርም። ግለሰዎች በስልጣን ለማቆየት ሲባል በሰለማዊና ንፁህ ዜጎች ግፍ እየተፈፀመ ዝም ብሎ መመልከት ተገቢ ኣይደለም።

ስለዚ ተቃውማችን ማሰማት ኣለብን። ደሞ የትግራይ ተወላጆች በኣማራ ክልል የሉም? የደቡብ ክልል ወይ ኦሮምያ ወይ ሌላ ክልል ተወላጆች በኣማራ ክልል የሚኖሩ የሉም ? የማፈናቀሉ ተግባር ካልቆመ መጨረሻው ምን ሊሆን ነው? ስለ ሌሎች ስናስብ ስለራሳችን እያሰብን ነው፤ ሌሎችን ስንተባበር ራሳችን እየተባበርን ነው። ተግባራችን ስንቃችን ነው።

ለዜጎች ቅድምያ እንስጥ!

It is so!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: