በሀዲያ ዞን የፍትህ ስርዓቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ

 

በሀዲያ ዞን ያለው የፍትህ ስርዓት የህዝብ አመኔታ እያጣ በመምጣቱ  ወደፍርድ ቤቶች ከመሄድ የሽምግልና ስርዓትን እንደሚመርጡን ባለው የፍትህ ስርዓት መዳኘት እንደማይፈልጉ ምንጮቻችን ከስፍራው ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የሌሞ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት  ህግ ከማስከበር ይልቅ የህግ ጥሰት በመፈፀም በደል ያደረሱብኝ የወረዳው ፍርድ ቤት ዳኛም አንዱ ናቸው የሚል ጥቆማ ተሰምቶ ጉዳዩ ለዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የስነስርዓት ጉዳይ ላይ እንዲታይ አቤቱታም መቅረቡን ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

በተለይ  በሌሞ ወረዳ ሲታይ የነበረው በመዝገብ ቁጥር 06066  በወይዘሪት ቤተልሔም ወልደመስቀል እና በአቶ ጌትነት በላቸው በተባሉ ግለሰቦች መካከል በሆሳዕና ከተማ ጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሄሜ ኢንተርናሽናል ሆቴል አጠገብ በሚገኝ 400 ካሬ ሜትር ላይ ያለው ቤትና ቦታ ወራሽነት ይገባኛል በሚል በሚደረገው ክርክር ላይ የካቲት 26 ቀን 2005ዓ.ም.  በዳኛ ወ/ዮሐንስ  ለውሳኔ መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡ይሁን እንጂ ጉዳዩ የማይመለከታቸው በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ ተነጥቆ ውሳኔው እንዲስተጓጎል በማድረግ ህግ ተላልፈዋል በሚል ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቦባቸው በፕሬዘዳንቱ  የተነጠቁት ዳኛ ወ/ዮሐንስ አይተው ውሳኔ እንዲሰጡ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተላለፈው  መሰረት የክሱ  መዝገብ  መጋቢት 11 ቀን 2005ዓ.ም. ውሳኔ መሰጠቱ ታውቋል፡፡ ነገር ግን በተደረገው  ክርክር ላይ “ወራሽ ነኝ ያሉት ግለሰብ አቶ ጌትነት በላቸው እስካሁን በአካል ያልቀረቡና በወራሽነት ያለችውን ግለሰብ መብት ለማሳጣት  የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ሆን ብለው ከህግ አግባብ ውጭ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ተከራካሪ  ወገኖችን እያጉላሉ ነው” በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቀርቦባቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ውሳኔ የሰጡት ዳኛ ወልደዮሐንስ ሐንዲሶ “በርግጥ የህግ ስርዓትን ያልተከተለ ትዕዛዝ መጥቶ አላይም ብዬ በኋላ የወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ጋር ከተወያየን በኋላ ማየት እንዳለብኝ ሲነገረኝ አይቼ ለውሳኔ በተዘጋጀሁበት ወቅት ተቃውሞ በመቅረቡ ውሳኔ ሳልሰጥ ቀርቻለሁ እንጂ አልተነጠኩም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከመረመረ በኋላ ውሳኔውን እኔ እንድሰጥ በመደረጉ በድጋሚ አይቼ ውሳኔውን ሰጥቻለሁ ” ብለዋል፡፡ የወይዘሪት ቤተልሔም  ጠበቃ አቶ ተካልኝ ጴጥሮስ በበኩላቸው “ጉዳዩን የህግ ስርዓት ያልተከተለ አሰራር በወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አሰራር ላይ ቅሬታ ስላለን አቤቱታችንን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማረም ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት በማይመለከታቸው ጉዳይ እንደ ፍትህ አካል ሳይሆን እንደባለጉዳይ ከህግ አግባብ ውጭ እየተንቀሳቀሱና እያስፈራሩ  በመሆኑ አሁንም ለሚመለከተው አካል ቅሬታችንን አቅርበን ውሳኔ እየጠበቅን ነው” ሲሉ  ገልፀዋል፡፡

በደል ፈፅመዋል የተባሉት የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ተስፋዬ ሰጦሬ በበኩላቸው “እኔ ከችሎት ላይ የነጠኩት የውሳኔ መዝገብም የለም፣ ሊኖርም አይችልም፤ እንዲህ ዓይት አሰራር ከዛሬ 20  እና 25 ዓመታት በፊት እንጂ በዚህ ስርዓት የለም፡፡ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ሲቀርብ ግን በህግ አግባብ እንዳይታይ አድርጌ ነበር፤ በመጨረሻ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን መሰረት ጉዳዩን የያዙት ዳኛ ወ/ዮሐንስ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አስፈራርተሃል የተባለውን በተመለከተ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው እንጂ ያስፈራራሁት አካል የለም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ለማ ገ/እግዚአብሔር  በበኩላቸው ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም በወረዳው ህጋው አሰራርን ያልተከተለ አሰራር ነበር ፤ በኋላ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ እርማት ሰጥቶ ቀደም ሲል የያዙት ዳኛ ውሳኔ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በይግባኝ ጉዳዩ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደርሶ እየታየ ይገኛል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተለይ ከጉዳዩ ጋር እጃቸው እንዳለበት የሚጠረጠሩት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ ግርማ አበበ ከህግ አግባብ ውጭ የወራሽነት መብት ላይ እግድ ጥለዋል ከሚል ቅሬታ በተጨማሪ ከወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ጋር የጥቅም ትስስር ስላላቸው ጉዳዩ ላይ እግድ ጥለዋል የሚል ቅሬታ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ አቶ ግርማ በበኩላቸው “እግድ የጣልኩት  ንብረት እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ እንዲሁም ለሶስተኛ ወገን ተላልፎ እንዳይሰጥ እንጂ የወራሽነት መብት ላይ እግድ አልጣልኩም” ሲሉ  ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡ በመጨረሻም የአቶ ጌትነትን ጠበቃ አቶ ኤርጃቦን ለማናገር ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች በርካታ የፍትህ መጓደል በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ እንደሚስተዋልና የአንዳንድ ዳኞች ሹመትም ቢሆን ከሙያ ብቃትና አገልግሎት ይልቅ የጎሳ ዝምድና ትስስር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ዙሪያ የዞኑ ፍትህ ጽህፈት ቤትን ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: