የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተለይም በጎንደር ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ እና አደባባይ ኢየሱስ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 3 ቀን 2005ዓ.ም. ድረስ የመራጮች ካርድ እየሰጠ መሆኑን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን በብሔረዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ካርድ መውሰጃ ቀን የተጠናቀቀው የካቲት 1 ቀን 2005ዓ.ም. መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አርብ ሚያዚያ 4 ቀን 2005ዓ.ም. ለምርጫ ታዛቢዎች በሚል በጎንደርና በመቀሌ ከተሞች ያሉ የቀበሌ ሰራተኞች እየዞሩ ገንዘብ ለመሰብሰብ መሰማራታቸውን የከተሞቹ ነዋሪዎችም በመታዘብ “ተወዳዳሪ በሌለበት የምርጫና ታዛቢ ለምን ያስፈልጋል?” በሚል ፊት እየነሷቸው እንዳባረሯቸው ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ባደረግነው የማጣራት ሙከራ በጎንደር ከኢህአዴግ ውጭ ምንም ዓይነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሌለና ብቻውን ለውድድር እንደቀረበ ከስፍራው ምንጮቻንን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጠን ጸደጋጋሚ ፅረጽ ብናደርግም አልተሳካም፡፡