ኢህአዴግ ብቻውን እየተወዳደረም ህገወጥ ስራ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ

በአዲስ አበባ የሚገኙ ባለሃብቶች “ኢህአዴግ ለሚያዚያ 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው የአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ብቻውን እየተወዳደረም ለምርጫ ቅስቀሳ በሚል በግዳጅ ገንዘብ እየጠየቀ ህገወጥ ድርጊት እየፈፀመ እንደሆነና ድርጊቱም እንዳማረራቸው ለአዲስ ሚዲያ ገለፁ፡፡ “በተለይ እኛ ሳንፈልግ ለኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ የሚሆን ገንዘብ አዋጡ የሚል እደምታ ያለውና የመንግስት መስሪያ ቤት ማኀተም ያረፈበት አስገዳጅ ደብዳቤ በየድርጅታችን ስም እየላኩ የመኖርና የመስራት ነፃነታችንን እየተጋፉ ነው “ ሲሉ ቅሬታ የተሰማቸው ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ለአዲስ ሚዲያ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት መጋቢት 20 ቀን 2005ዓ.ም. በወረዳው ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጽህፈት ቤት ማኀተም ባረፈበትና የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስልክ አድራሻን በመጠቀም የተላከው ደብዳቤ “…ባለድርሻ አካላት” ላላቸው “የኢህአዴግ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ታዋቂ ካምፓኒዎች፣ ሪል ስቴቶች፣ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት” በሚል ከተላከው አስገዳጅ ደብዳቤ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተላከው ደብዳቤ ማጠቃለያ ላይ አስገዳጅነቱን በግልፅ በሚያሳይ ማስፈራሪያ “የዚህ ፕሮግራም ማጠቃለያ የሚሆነው ለሚመለከተው አካል ጊዜውን የጠበቀ ዘገባ ማድረግ ይሆናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢህአዴግን መምረጥ የሀገራችንን ህዳሴ ወደ ሌላ ምዕራፍ ማሸጋገር ስለሆነ አገረ ባለሃብቶችና ጥያቄ የቀረበላችሁ አካላት አስፈላጊውን ታደርጉ ዘንድ ማሳወቅ ነው::” በሚል ከፈቃደኝነት ይልቅ አስገዳጅነት ያለው ደብዳቤ በመላክ ምላሽ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል ሲሉ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ባለሃብቶች ከተደገፈ መረጃ ጋር አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኢህአዴግ ብቻውን ሆኖ ይህን ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙ የከዚህ በፊቱ ልምዱን ነው የሚያሳየው፣ ይህ አዲስ አይደልም፤ እንደውም ይባስ ብሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንኳ የእሱ አጋር መሆናቸውን መግለፁ ኢህአዴግ ህገወጥ ስራ መስራቱን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገልፀውልናል፡፡

ይህንንም በሚመለከት ምርጫ ቦርድ ምን ይላል የሚለውን ለማረጋገጥ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፤ ከዚህ በተጨማሪ በመንግስት ማኀተምና አድራሻ የኢህአዴግ ምርጫ ቅስቀሳ ደብዳቤ በትነዋል ከተባሉት መካከል በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ስለሺ ካሳ መልስ እንዲሰጡን ብንሞክርም ያልተሳካ ሲሆን በወረዳው የመንግስት ቢሮ ውስጥ የህዝብ አደረጃጀት ኃላፊ በህዝብ ደመወዝ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ስራን የሚሰሩት አቶ በረከት ዮሐንስ በበኩላቸው እኛ እንዲህ አላደረግንም ቢሉም ሰነዱ ግን በዝግጅት ክፍላችን የሚገኝ ሲሆን ቅጂው ለምርጫ ቦርድ ህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደደረሰም ተጠቁሟል፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ወንድሞ ጎላ በበኩላቸው ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት ተፈፅሞ ከሆነ የእርምት እርምጃ እንወስዳለን ፤ መረጃውን ግን እስካሁን አላየሁትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: