በአፋር ክልላዊ መንግስት ገዥው ፓርቲ አብዴፓ ባካሄደው ጉባዔ የክክሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አወል ውቲካ እና የአብዴፓ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ቡልቡል የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም በሚል ሙሉ በሙሉ ከስልጣናቸው ሲነሱ የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ ያዮ ከኃላፊነታቸው ዝቅ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ እስማኤል አሊሴሮ ከክልሉ ህዝብ ጥቅም ይልቅ ለኢህአዴግ ስልጣን ጥቅም ብቻ ይሰራሉ በሚል እየተወቀሱ ውስጥ ውስጡን ከስልጣናቸው እንዲነሱ ቢፈለግም በኢህአዴግ ባለስልጣናት ፍላጎት ሳይወርዱ መቅረታቸውን የአዲስ ሚዲያ ምንጮቻችን ከስፍራው ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ ዜና በአፍር ክልል ዞን ሶስት በሚገኙ ገዋኔ፣ አሚባራ እና ጉሩመዳች ወረዳ ከሚገኙ አርብቶ አደሮች በፌደራል ፖሊስ ለከብቶቻቸው ጥበቃ የሚገለገሉበት የጦር መሳሪያ በፌደራል ፖሊስ ተነጥቆ ሲወሰድ የአጎራባች የሶማሌ ክልል ወረዳ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ተነጥቆ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀሱ ወዲያው ሲመለስላቸው የአፋሮች ግን ሳይመለስ በመቅረቱ ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች 80 ፍየሎችና 17 የቀንድ ከብቶች እንደተሰረቁባቸው ምንጮቻችን በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ መሐመድ ያዮ የተደረገው ሹም ሽር አስመልክቶ፣ የአርብቶ አደሮቹ መሳሪያ መነጠቅ ላይ እና ተፈፀመባቸው ስለተባለው ዝርፊያ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡