በደቡብ ክልል በቤንች ማጂ ዞን በሚገኘው ሚዛን 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ከሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ መዘጋቱ ታውቋል፡፡ እንደፍኖተ ነፃነት ምንጮች ገለፃ ከሆነ ከሚያዚያ 7 ቀን 2005ዓ.ም. ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና አስተዳደር አካላት በተነሳ አለመግባባት ከፍተኛ እረብሻ በመፈጠሩ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ለረብሻው መንስኤው የትምህርት ቤቱ ከአሜሪካ በተሰጠው የትምህርት ዕድል የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ተማሪዎች መካከል በተደረገው ውድድር ከሴቶች ተማሪ መድኃኒት ስታሸንፍ ከወንዶች ደግሞ በጀመሪያ ተማሪ ጌታመሳይ ማሸነፉ ከተጠቆመ በኋዋላ በተደረገ የውጤት ማጣራት ሂደት ተማሪ ዮሐንስ ማለፉ ተጠቁሟል ፡፡ ይህንንም ተከትሎ በተለይ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ በወንዶች ተማሪ ዮሐንስና ተማሪ ጌታመሳይ ውድድር ላይ የውጤት አሰራር ስህተት በመኖሩን በተማሪዎችና በትምህርት ቤቱ መምህራንና አስተዳደር አካላት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት መማር ማስተማሩ ሂደት መቋረጡ ተጠቁሟል፡፡ በመጨረሻም በተደረገው የውጤት ማጣራት መሰረት በውድድሩ ያለፈው ተማሪ ዮሐንስ መሆኑንም ምንጮቻችን አስታውሰዋል፡፡
ከረብሻው ጋር በተያያዘ ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. በትምህርት ቤቱ አካባቢ ተኩስ መከፈቱና በተፈጠረ ግጭትም 3 ተማሪዎች ቆስለው ወደህክምና ጣቢያ መወሰዳቸው ተገልፁዓል፡፡ ይህን ዜና እስከዘገብንበት ድረስም ትምህርት ቤቱ በፌደራል ፖሊስ መከበቡ ተጠቁሟል፡፡ ይህንንም በሚመለከት የትምህርት ቤቱ ዋና ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አብዱ ካሣ ስለጉዳዩ ስናነሳላቸው አሁን ስለማልችል ከ30 ደቂቃ በኋላ መልሳችሁ ደውሉ ካሉ በኋዋላ ሽልካቻን በመዝጋታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡ ምክትላቸው አቶ አበራ ጉልማንም ለማናገር ጥረት ብናደርግም ስልካቸውን ጆሯችን ላይ ዘግተዋል፡፡