የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ(ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ የመድረክ ከፍተኛ አመራርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦፌኮ አመራር አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳን ጨምሮ ወጣት ወልቤካ ለሚ፣ አደም ቡላ፣ ደረጀ ከተማ፣አዲሱ ምክሬ፣ገልገሎ ጉፉ፣ መሐመድ መሉ እና ወይዘሪት ሐዋ ዋቆ በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተወሰነባቸውን ክስ በመቃወም ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን ውሳኔ አላገኙም፡፡ በዚህም ምክንያት ይግባኝ የጠየቁት ክስ 6 ኪሎ በሚገኘው በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በቀለ ገርባ ለሚያዚያ 14 ቀን 2005ዓ.ም. የተቀጠረ ሲሆን የአቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ ለሚያዚያ 16 ቀን 2005ዓ.ም. ክርክር ለማድረግ ተቀጥሯል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ ያሉ ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ይግባኝ ቢጠይቁም እስካሁን የተሰጠ ቀነ ቀጠሮ አለመኖሩ ታውቋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ቀደም ሲል በከፍተኛው ፍርድ ቤት የተወሰነባቸው ቅጣት 8 ዓመት ሲሆን አቶ ኦልባና ሌሊሳ ደግሞ 13 ዓመት ፅኑ እስራት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በተያያዘ ዜና በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተጠርጥረው በተሸለ በከሺ የክስ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ተሸለ በከሺ፣ሐሰን መሐመድ፣ አለማየሁ ጋሮምሳ፣ ልጅዓለም ታደሰ፣ ቶሎሳ በቾ እና ወጣት ሙላታ አብዲሳን ጨምሮ 69 ተከሳሾች ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. የመከላከያ ምስክር ለመስማት ቀነ ቀጠሮ የተሰጠ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 27 ቀን 2005ዓ.ም. ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ የኦፌኮ አባላትን ጨምሮ የቀድሞ የፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ አቶ ጉቱ ሙሊሳ ይገኙበታል፡፡ ተከሳሾቹ የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ ከሚያዚያ 19 ቀን 2003ዓ.ም. ጀምሮ በፍርድ ቤት እየተመላለሱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡