የነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ይግባኝ ላይ ውሳኔ ተሰጠ

 

 

esekinderበፌደራሉ አቃቤ ህግ በሽብርተኝነት ክስ ተመሰርቶባቸው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በነ አንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ የተላለፈውን ውሳኔ በመቃወም 6 ኪሎ በሚገኘው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ውሳኔ ለመስጠት ለ5 ጊዜ ተደጋጋሚ ቀነ ቀጠሮ ከሰጠ በኋላ ሚያዚያ 24 ቀን 2005ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ላይ በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በአንዱዓለም አራጌ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 24 ተከሳሾች መካከል ይግባኝ የጠየቁት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ናትናኤል መኮንን፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም፣  አቶ ዮሐንስ ተረፈ እና የቀድሞ ፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ አንዱዓለም አያሌው  በተጨማሪ እውቁ የፖለቲካ ተንታኝ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአቶ አንዱዓለም አራጌ ላይ ዕድሜ ልክ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ 18 ዓመት፣ አቶ ናትናኤል መኮንን ላይ 18ዓመት፣ ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም 15ዓመት፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ 13ዓመት፣  አቶ አንዱዓለም አያሌው 14ዓመት፣ አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ 25ዓመት ፅኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሐሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2005ዓ.ም. የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ተከሳሾች በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ክስ የአቶ ክንፈሚካቼል ደበበን የቅጣት ውሳኔ ከ25ዓመት ወደ 16 ዓመት ዝቅ ከማድረግ በስተቀር ከላይ የተጠቀሱትን የሌሎቹን ይግባኝ ክስ ተቀባይነት ሳያገኝ የስር ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔን(ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 3ኛ ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ) እንዲፀና በመወሰን የፌደራሉ ማረሚያ ቤት ቅጣቱን እንዲያስፈፅም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በዕለቱ በችሎት ተሰይመው የነበሩትና ይግባኙን ሲመረምሩ የቆዩት ዳኛ ሽመክት አሰፋ፣ ዳኛ በላቸው አንሺሶ እና ዳኛ ዳኜ መላኩ ሲሆኑ የፍርድ ውሳኔውን በንባብ ያሰሙት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ናቸው፡፡ ውሳኔው በንባብ ከመሰማቱ በፊት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ ተከሳሾችና የችሎት ታዳሚዎች ውሳኔው በሚሰማ ሰዓት ስነስርዓት እንዲይዙ ማስጠንቀቂያ በመስጠት  የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡ በችሎቱ ላይ ውሳኔውን ያነበቡት የመሐል ዳኛው ዳኜ መላኩ በተደጋጋሚ የመጨናነቅ ስሜት የታየባቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ፊታቸውን በመሃረም እየጠራረጉና ያነበቡትን አረፍተ ነገር በመደገሃገም ይቅርታ ያዘወተሩ ሲሆን የግራና ቀኝ ዳኞች የነበሩት ሽመክት አሰፋና በላቸው አንሺሶም በከፍተኛ ትካዜ ላይ ሆነው ተከሳሾችን በመመልከት የተለመደው የፊታቸው ገፅታ በወቅቱ አልነበረም ነበር፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ከፍተኛ የሚለውን ወደመካከለኛ ያወረደው መሆኑን፣ በተከሰሱበት 2ኛው ክስ ላይ ደግሞ ተከሳሾቹ በነፃ ያሰናበተ መሆኑን በመግለፅ ነገር ግን የቅጣት ውሳኔ ዓመቱ ላይ ምንም ለውጥ እንደማይኖረው አስታውቋል፡፡

በችሎቱ ላይ የተገኙት ተከሳሾች አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን እና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ አቶ አንዱዓለም አያሌው ፣ አቶ ዮሐንስ ተረፈ እና ሻምበል የሺዋስ ይሁንዓለም ረቡዕ ሚያዚያ 23 ቀን 2005ዓ.ም. ይግባኝ ቀጠሮ እንዳላቸው እየታወቀ ወደ ዝዋይ ወህኒ ቤት በመወሰዳቸው ሊገኙ ባይችሉም በሌሉበት የይግባኝ ውሳኔው ተሰጥቷል፡፡ በሰዓቱ ከአቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ብቻ የተገኙ ሲሆን ከተከላካይ ጠበቆች አቶ አበበ ጉታ፣ አቶ ደርበው ተመስገን እና አቶ ሳሙኤል አባተ ተገኝተዋል፡፡

በመጨረሻም በውሳኔው ዙሪያ ከተከሳሾቹ መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ”እውነት ተደብቆ አይቀርም፣ይህን ህዝብ እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ…”፤ አቶ ናትናኤል መኮንን “መጀመሪያም ቢሆን የተከራከርናው ፍትህ እናገኛለን ብለን አይደለም” ሲል ባለቤቱ ወይዘሮ ፍቅርተ በበኩላቸው “እኔ ቀድሞውንም ለውጥ ይኖራል ብዬ አልጠበኩም” ብለዋል፡፡ አቶ አንዱዓለም አራጌ በበኩላቸው “…ፍትህ በኢትዮጵያሞተ ይህንንም ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ሊያውቀው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ችሎቱን ለመከታተል በርካታ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችና ወዳጆች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች፣ የተለያዩ ፖለቲከኞችና አድናቂዎቻቸው እንዲሁም የዓለም አቀፉ ዲፕሎማቶች የተገኙ ሲሆን ወደ ችሎት የገቡት ግን ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ በነበረው ሁኔታና በውሳኔውም በተለይ እጅግ ማዘናቸውንም ያነጋገርናቸው  የታሳሪ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: