ቴዎድሮስ ባልቻ
አቶ መለስ ዜናዊ የእረፍታቸው ዜና ከተነገረ በኋላ በህይወት ሳሉ የሌላቸውን ባህርይ ሳይቀር በመግለፅ ደጋፊዎቻቸው ጣዖት ማምለክ እስኪመስል ድረስ እንዲመለኩ ይፈልጋሉ፡፡ እውነታው ግን አቶ መለስ የኢህአዴግ ደጋፊዎች የሚያወሩላቸውን ያህል ግለሰብ ስላለመሆናቸው የማይረሱ በርካታ ስራዎቻቸው ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን አንዳችም ጥሩ ስራ የላቸውም ማለት ሳይሆን በንፅፅር ሲቀርብ ግን ጥሩ መሪ ነበሩ ማለት በገለልተኛ አካላት ሰፊ ጥናት መደረግ ያስፈልገዋል፡፡
አመራሮቹማ ከቤተ መንግስት እስከ ገጠር ቀበሌ የእሳቸውን ሞት ተከትሎ ምስላቸውን የያዙ ፖስተሮች መለጠፋቸው ሰውየውን ‹‹ቅዱስ›› ለማስመሰል ከመሞከር ባለፈ ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀሙባቸው መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ይህንን ለማርከስም ሆነ ህዝቡ ስለ እሳቸው ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቅ አማራጭ የሀገር ውስጥ ነፃ ሚዲያ ያለመኖር በመጋረጃ ውስጥ ያሉት መለስ ተዘንግተዋል፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ ስለሳቸው ትክክለኛ ማንነት የተወሰኑ ተግባራቸው የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም እሳቸው ከሚያደንቋቸው የውጭ ሚዲያ መዳሰሱ የተሻለ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በቅርቡ የዓለም መሪዎችንና ባለሃብቶችን ሃብትና የግል ታሪክ በማስነበብ የሚታወቀው ድህረ ገፅ ስለእሳቸው በአጭሩ ያስቀመጠውን እንመልከት፡፡ የመረጃው መረብ ሰውዬውን ከልደት ዘመን እስከሞታቸው ከመግለፁ በተጨማሪ አንድ አስደንጋጭ (ለኢህኢዴግዎች) መረጃም አክሎበታል፡፡ ይህም ያላቸውን የሃብት መጠን ከዓለም ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከከል ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትርና የታወቁ ባለሃብት ከሆኑት ሲልቪዮ በርሎስኮኒ በመቀጠል በ3 ቢሊዮን ደላር (56 ቢሊዮን ብር ገደማ) 2ኛ ደረጃን እንደያዙ www. therichest.org በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም http://www.therichest.org/celebnetworth/politician/minister/meles-zenawi-net-worth/ መጎብኘት ይቻላል፡፡
በተለይ ነገሩን አስደንጋጭና አሳፋሪ የሚያደርገው በህይወት ያሉት ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን በባህርዳሩ የኢህአዴግ ጉባዔ ሳይጠየቁ የአቶ መለስን ድህነት ሲናገሩ ነበርና፡፡ ያኔ ባለቤታቸው ከመንግስት መደበኛ 6 ሺህ ብር ደመወዛቸው ላይ ተቆራርጦ 4 ሺህ ብር ያህል እንደሚደርሳቸውና በዚህም ይተዳደሩ እንደነበር መግለጣቸው አይዘነጋም፡፡ በርግጥ ያኔ ባለቤታቸው የተናገሩትን ህዝቡ ተቀብሏቸዋል ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም 21 ዓመታትን ሙሉ ያለመላከ ሞት ከቤተመንግስት አልወጣም ብለው የመሸጉትን የህዝብና የሀገርና የወገን ፍቅር ኖሯቸው እንዳልነበረ እንቅስቃሴያቸው ያሳብቅ ነበርና፡፡
‹‹ደሃው ›› አቶ መለስ
ዛሬ እንደጣዖት ፎቶአቸውን በየቦታው ተለጥፎ የምናገኛቸው አቶ መለስ ዝናዊ ምናልባት በመሪ አስተሳሰብ ካልሆነ በቀር በገንዘብ በኩል ደሃ ነበሩ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ያለባህርበር ከማስቀረት አልፈው በታሪክ የኢትዮጵያ እንደሆነ የሚታወቀውን አሰብ ወደብንና አካባቢውን ትውልዱ ያንን እንዳያስብ በማድረግ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ተስተውለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስንቶች የሞቱለትን የሀገሪቱን ሰንደቅዓላማ ‹‹ጨርቅ ነው›› ብለው አራክሰዋል፡፡ የአክሱም ሐውልት ለወላይታ ምኑ ነው ሲሉም ከመናገር ያለፈ የአስተሳሰብ ድህነት የለም፡፡
እሳቸውም በአንድ ወቅት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው እንደድሮ (ጫካ ሳሉ) እንደማይርባቸውና የቆሸሸ እንደማይለብሱ ከማስታወስ ውጭ በገንዘብ በኩል ያኔ ደሃ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ እውነታው ግን ያ ስለመሆኑ ህዝቡ መርምሮ እንዲያውቅ ዕድል አልሰጡትም፡፡ ዛሬ ግን ተከታዮቻቸው ከእራሳቸው አልፈው መላው ህዝብ ንፁህና ቅዱስ አድርጐ እንዲመለከታቸው በየመድረኩ የሚነገረው አሰልቺ ወሬ ገመናቸውን ሊደብቅ እንደማይችል የተረዱት አይመስልም፡፡
በተለይ በገንዘብ ደረጃ ምንም ያልነበራቸውና ይሄንንም ራሳቸው የተናገሩ ቢሆንም ስለ እሳቸው ዝርዝር የህይወት ታሪክ በግልፅ በማስቀመጥ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ መሆናቸውን ግን በህይወታቸውም ሆነ በሞታቸው አላስተባበሉም፡፡ ስለዚህ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በባዶ እጃቸው ጫካ ገብተው የወጡት አቶ መለስ ነግደው ሳያተርፉ ቢሊየነር ባለጠጋ የሆኑት ከህዝብ ሃብት ዘርፈው ካልሆነ ከየትም ሊያመጡ እንደማይችሉ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም ሰውዬው ይወራ እንደነበረው ዓይነት እንዳልሆኑ ውሎ ሲያድር እየጠራ ነው፡፡
የግል ማኀደራቸው በአጭሩ
አቶ መለስ (ለገሰ) ዜናዊ በወርሃ ግንቦት 1947 ዓ.ም. በአድዋ ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአድዋ ንግስት ሳባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲከታተሉ የሁለተኛ ደረጃን አዲስ አበባ በሚገኘው ጀነራል ዊንጌት ተከታትለው በመጨረስ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀድሞ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገብተዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በሁለተኛው ዓመት አቋርጠው ወደጫካ ከመግባታቸው ውጭ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ማጠናቀቃቸውን የሚገልፅ የምስክር ወረቀት የላቸውም፡፡
ነገር ግን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በምን ዘርፍ፣ ከየትና መቼ እንዳገኙ የሚያሳይ ማስረጃ እስካሁን ባይገለፅም ከእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርስቲ በህዝብ አስተዳደር ማስተርስ ዲግሪ ማግኘታቸው ተገልጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኔዘርላንድስ ሮተርዳም ከሚገኘው ኤራስመስ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ዲግሪ ባለቤት ከመሆን ውጭ በትምህርት ሌላ ደረጃ እንደሌላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አቶ መለስ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ጋብቻ በመመስረት ሰናይ፣ ሰመሃል እና ማርዳ የሚባሉ የሶስት ልጆች አባት እንደሆኑም በመካነ ድሩ የመረጃ መረብ ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በመጨረሻም ለ21 ዓመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ በተወለዱ 57 ዓመታቸው ነሐሴ 14 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም (እንደ መንግስት ገለፃ) መሞታቸውን፤ የ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደነበሩ ደግሞ http://www.therichest.org›› የተሰኘው ድህረ- ገጽ በግልፅ አስፍሯል፡፡
ሌላው ደቀመዝሙሩ ከመምህሩ እንደሚማር ሁሉ የታችኞቹ ሙሰኞች መሰረት የላይኞቹ ባለስልጣናት ልምድና ተሞክሮ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች›› እንዲሉ የታችኞቹ ሙሰኞች (ከቀበሌ እስከየ መስሪያ ቤቶች ባለስልጣን) ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስን እና መሰሎቻቸውን ፈለግ ተከትለው ባይተማመኑ እነ አቶ ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስ በቤታቸው የዶላርና የብር ክምችት ባልተገኘ ነበር፡፡
ስለዚህ በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ተግባር በእጅጉ ለመቀነስ ከተፈለገ ወኔውና ድፍረቱ ካላቸው አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝና የፌደራሉ የስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ በ3 ቢሊዮን ዶላር ባለጠጋ እንደሆኑ ከተነገረላቸው ከቀድሞው የቤተመንግስት የስልጣን ባህታዊ ከሆኑት ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን እስከ ሚኒስትሮችና የጦር ጀነራሎች መዝለቁ የግድ ይላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው አቶ መለስ አላቸው ከተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር ውጭ የሃብት ምንጫቸው ያልታወቁ ጊዜ አመጣሽ ከበርቴዎችን መዳሰሱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ በዚህም አለ የተባለው ሃበት እውነትነት መርምሮ ለህዝብ የማሳወቅም ግዴታ አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሀገሪቱ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የፕሬስ ነፃነት በወረቀት በህገመንግስቱ ከማስፈር ውጭ በተግባር የሚረጋገጥ ከሆነ በርካታ የሙስና ተግባራትንና ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጥ የኮሚሽኑንና የሌሎች የፍትህ ተቋማትን ስራ ያቀላል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከመካላከያ ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች)፣ የከተማ መስተዳድሮች ውስጥን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉ የብልሹ አሰራሮች ምን ያህል ለሙስና እንደተጋለጡም የፌዴራሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት የመረጃ ዘገባዎችን /ሪፖርቶቹን / እንደግብዓት መጠቀም አስፈላጊ ቢሆንም እስካሁን በተግባር የታየ እርምጃ ግን የለም አለበለዚያ እንደ ዳዊት ‹‹ሙስና›› እያሉ መደጋገሙና ትናንሾቹ ላይ ብቻ ጃስ ማለት የህዝብን የትኩረት አቅጣጫ ከማስቀየር ባለፈ ለሀገርና ለህዝብ ሃብት ተቆርቋሪነትን አያሳይም፡፡
እሳቸውስ ሞቱ 3 ቢሊዮን ዶላሩስ?
በተለይ ወደ ፖለቲካው የሀገር አስተዳደርነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የሳይንሱን ትምህርት በርቀት ሳይሆን በመደበኛ ተከታትለው የህግ ምሁሩና ድምፃዊ የነበሩት የኤሲ ሚላኑ እግርኳስ ክለብ ባለቤት ከሆኑት ከ76 ዓመቱ የጣሊያኑ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲልቪዮ በርሎስኮኒ የ6 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ቀጥለው ከጫካ በትጥቅ ትግል ወደ ስልጣን የወጡት አቶ መለስ በ3 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛነትን ይዘዋል፡፡ በመቀጠልም የሊባኖሱ የሐርቫርድና የቤሩት ዪኒቨርስቲ ምሩቅና ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የተለያዩ ኩባንያዎች ባለቤት የሆኑት የ57 ዓመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ አዝሚ ሚካቲ በ 3 ቢሊዮን ዶላር 3ኛነትን ይዘው ይከተላሉ፡፡
አቶ መለስ ግን ከጫካ ወደ ፖለቲካ ስልጣን ከመውጣት ውጭ የተጠቀሰው ሃብታቸው ከየት መጣ? የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ከሚያውቀው እውነታ ውጭ እሳቸውም ምንም እንደሌላቸው ከመሞታቸው በፊት ተናግረዋልና፡፡ በጣም የሚገርመው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ዊሊያም ዶናልድ ካሜሩን እንኳ ያላቸው ሃብት ሲታይ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብቻ እንደሆነ እና የዚህም ሃብታቸው ምንጭ ፖለቲካ እንደሆነ ድህረ-ገፁ ሲጠቁም የአቶ መለስ ዜናዊ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ምንጭም ፖለቲካ እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በዚህም ሟቹ አቶ መለስ ይህን ያህል ሃብት በፖለቲካ ስራ ባለቤት ከሆኑ የሌሎቹ ባለስልጣናት ቢጣራ ስንት ይሆን የሚል ጥያቄን ከማስነሳቱ በተጨማሪ ሀገሪቷ ምን ቀራት ያሰኛል፡፡
በርግጥ የአቶ መለስንና ባለቤታቸውን ከፍተኛ ባለጠግነትን (ቢሊየነርነትን) በተመለከተ ምስጢራዊ መረጃዎችን በመልቀቅ የሚታወቀው ‹‹wikleaks›› የተሰኘው ድህረ- ገፅ ‹‹Ethiopian Super rich persons›› ሲል የተለያዩ የቅርብ ወዳጆቻቸውን የቃለመጠይቅ ምስክርነት ማስረጃ ሳይቀር አስደግፎ ማስነበቡ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ‹‹therichest›› ድህረ – ገፅ ያላቸውን የገንዘብ መጠን 3 ቢሊዮን ዶላር ብሎ ባይገልፅም ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለጠጋ መሆናቸውን አልሸሸገም ነበር፡፡
በአሁኑ ሰዓት አቶ መለስ ሞተዋል፤ አላቸው የባለው 3 ቢሊዮን ዶላርስ የት ገባ? ምን እየሰራስ ነው? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ቢሆንም እዚህ ላይ ቀን ከሌት ስለመለስ ሙገሳና አድናቆት አውርተው የማይጠግቡት የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያ ደሳለኝ ከባድ የቤት ስራና ፈተና ነው፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ የፌደራሉ የሥነ – ምግባርና ፀረ – ሙስና ኮሚሽን ቁርጠኝነትንና ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የአቶ መለስ አላቸው የተባለው 3 ቢሊዮን ዶላር የት እንዳለና ምን እየሰራ እንደሆነ ከነምንጩ ከመረጃ መረቦቹም ሆነ በራሳቸው ዘዴ አጣርተው የመግለፅ ትልቅ ፈተና ይጠበቅባቸዋል፡፡
የገንዘቡ መገኘት ከተረጋገጠ በኋላም ገንዘቡ ከድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ተነጥቆ የተዘረፈ ስለመሆኑ ማንም ሊጠራጠር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከራስ በላይ ምስክር የለምና ሁለቱም የህወሐት ኢህአዴግ እና የሀገሪቱ የስልጣን ቁንጮዎች በገንዘብ አቅም ድሃ ስለመሆናቸው ተናግረዋልና፡፡ ስለዚህ እነኛ ታማኝ የመረጃ ምንጮች የገፁት በተለይ ‹‹therichest›› ያሰፈረው 57 ቢሊዮን ብር (3 ቢሊዮን ዳላር ) ወደ ተዘረፈው ህዝብ ተመልሶ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል፡፡
‹‹ ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው››
አበው ሲተርቱ ‹‹ዓሳ የሚገማው ከጭንቅላቱ ነው ›› ይላሉ፡፡ ዓሳ ከምግቦች ሁሉ የተሸለና ሁሉንም ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ተወዳጅ ምግብ ቢሆንም ለምግብነት ከመሰናዳቱ በፊት ከመኖሪያው ውሃ ውስጥ እንደወጣ የማይወደድ ሽታ አለው፡፡ የዚህ ‹‹መጥፎ ሽታ›› መነሻው ደግሞ ጭንቅላቱ እንጂ ሌላው አካሉ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ በዚህም ዓሳ ከውሃ ውስጥ ከወጣ በኋላ ያለው መጥፎ ጠረን ጭንቅላቱ ስለሆነ ተቆርጦ መጣል እንዳለበትና ያኔም ሌላው አካሉ ከመጥፎ ሽታ እንደሚፀዳ አመላካች ንግግር ነው፡፡
በኢትዮጵያ ስላለው ቅጥ ያጣ የሙስና ተግባርም ሆነ ብልሹ አሰራር መነሻው ገዥው ኢህአዴግና ቁንጮዎቹ እንደሆኑ የሰሞኑ መረጃ በራሱ በቂ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ከሚኒስትር አቶ መላኩ ፈንታና ረዳታቸው የሙስና ተግባር መጠርጠር በተጨማሪ በወ/ሮ አዜብ መስፍን ‹‹ድሃ›› ስለመሆናቸው የተመሰከረላቸው ግን በዓለም 2ኛው ባለጠጋ ጠቅላይ ሚኒስትር(በ3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር) እንደሆኑ የተነገረላቸው ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ አለ የተባለው ሃብት ምንነት ካልተጣራና ካልተመለሰ የመንደር ሌቦችን ብቻ ማሳደድ ሙስናን ሊገታ አይችልም፡፡
ምንጭ፡- ኢቦኒ መፅሔት(ሰኔ በ2005ዓ.ም.)
It is so important info..thanks!!