ወጣቱ ወዴት እየተመራ ነው?

ብስራት ወ/ሚካኤል

ልማት ትርጓሜው እጅግ ሰፊ ቢሆንም ጥቅል ሐሳቡ ግን ለሰው ልጆችም ሆነ የተፈጥሮ ሚዛንን በመጠበቅ በማኀበረሰቡ ዘንድ ይሁንታን ያስገኘ ለኑሮ ተስማሚ ሁኔታን በመፍጠር ውጤታማ የሆነ ተጨባጭ እውነታን ያዘለ ክንውን ነው፡፡ ይህም ሰብዓዊና ቁሳዊ ይባላል፡፡ ይህን በተመለከተ በተለይ ሰብዓዊ ልማት የሚባለው ቁሳዊ የሚባለውን ልማት ሊያመጣ የሚችል የሰው ልጆች የባህሪ አስተሳሰብ አዎንታዊ ለውጥ ነው፡፡ ይህ ለውጥ የማኀበረሰቡን በጎ አሴቶችን አጠናክሮ በመቀጠል አሉታዊ የሚባሉትን በማረምና አዳዲስ አዎንታዊ ለውጦችን ከልማዳዊ አኗኗር ጋር በማስማማት በስልጣኔ ቀላልና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው፡፡ ያኔ ቁሳዊ ልማቱን በሚፈለገው ደረጃ ማምጣት ይቻላል፡፡ የዚህ ልማት ውጤታማ ተግባርና የስልጣኔ ዝመና ሽግግር ትልቁን ሚና የሚጫወተው ወጣቱ ሲሆን ለዚህም አበረታች የሞራል ስንቅ ያስፈልጋል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ከሀገሪቱ አብላጫው የህዝብ ቁጥር ልቆ የሚታየው ወጣቱ ነው፡፡ የዛን ያህል ደግሞ ከምርታማነት ይልቅ ጥገኛ እንዲሆን የተፈረደበት ይመስላል፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን ተስኖት ሌሎች የሚመርጡለትን፣ የመረጡለትን በመጠበቅ ጊዜውን ሲያባክን ይታያል፡፡ ይህ ማለት ግን አኩሪ ተግባር እየፈፀሙ ያሉ ወጣቶች ጭራሽ የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ከለው ቁጥር አንፃር ሲታይ አብዛኛው ወጣት በብዙ ነገሮች ጥገኛ እንዲሆን በመገደዱ እራሱን እንዳይመለከት ጋርዶታል፡፡
ድሮ ድሮ እንኳን ስለራሱ፣ ስለሀገሩ ከዛም አለፍ ሲል ስለሌሎች ይጨነቅ የነበረው ወጣት ዛሬ ስለራሱ በራሱ መወሰን ተስኖት የተመረጠለት ካልተስማማው የመጨረሻ ምርጫውን ስደት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሐል ህጋዊና ህገወጥ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለስደት የዳረገውን ምክንያት ግን ደፍሮ የሚገልፅ አካል አልተገኘም፡፡ እንግዲህ እንዲህ የተፈረደበትን ወጣት ሀገር እያሳጡት ሀገር ተረካቢ እየተባለ ይቀለድበታል፡፡
ወጣትነት እጅግ ፈተና የበዛበት የተፈጥሮ የእድሜ ሂደት አካል ቢሆንም በርካታ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ግን ከየትኛውም የዕድሜ ክልል የተሻለ ነው፡፡ የመኖሪያም ሆነ የመዋያ ምርጫው በሌሎች መልካም ፈቃድ ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ክስተት ወጣቶች ሆን ተብሎ ምርታማ እንዳይሆኑ የሚሰራ ይመስላል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆነን ዘንድ ጥቂቶቹን እንይ፡፡
የወጣት ማዕከላት
ቀደም ባለው የደረግ ስርዓት ግልፅና ቀጥተኛ ሶሻሊስት የነበረ ቢሆንም ወጣቱን በእስፖርትና በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ለማጎልበት ይረዳ ዘንድ በርካታ የተለያዩ የወጣት ማዕከላት ነበሩ፤ አሁን በነበሩ ቀረ እንጂ፡፡ በወቅቱ በተለያዩ ከተሞች ከስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ እስከ ሙዚቃና ቴአያትር (ድራማ መለማመጃ) በየከተማ ቀበሌው ይገኝ ነበር፡፡ለወጣቶቹ ታስቦ በተሰሩት ሜዳዎችና አዳራሾች ወጣቱ በአግባቡ ይጠቀምበት የነበረ ቢሆንም ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነፃ የሐሳብ መንሸራሸርን በተመለከተ ግን ከስርዓቱ ውጭ እንደማይፈቀድ በግልፅ ስለሚታወቅ ጎጅ ቢሆንም ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡
ዛሬ ደግሞ በአንፃሩ የነበሩ ሜዳዎች ዳግም ባናያቸውም በወጣቱ መዝናኛ ሰም የኢህአዴግ ካድሬ መመልመያ ሆነው አርፈዋል፡፡ የወጣት ማዕከል ተብሎ በተሰሩ አዳራሾች ምንም ከቀድሞ የተለየ ነገር የለም፡፡ ምክንቱም ዛሬም በአዳራቹ ስለ ኢህአዴግ ጥሩነት ለማውራትና የርካሽ ባዶ ፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን ውጭ ወጣቱ ነፃ የሆነና ያመነበትን ርዕስ አንስቶ መወያየት አይችልም፡፡ ይህ የሆነው ግን በህግ ሳይሆን ከመጋረጃ በስተጀርባ ባልተፃፈው ትዕዛዝ ነው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ በርካታ የቀበሌ አዳራሾች ቢገነቡም እየሰጡት ያለው አገልግሎት ግን ሁሉንም ወጣት ሊያካትት በሚችል የተለያዩ ሐሳቦች ሊንሸራሸሩ በሚያስችል ሁኔታ ሳይሆን በኢህአዴግ ጥላ ለተሰበሰቡት ብቻ ነው፡፡ እንዲህም ቢሆን የሚሰጡት አገልግሎት ቢበዛ ቤተመፅሐፍ፣ ጂም እና የገላ መታጠቢያ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህም የወጣቱ ፍላጎት በሁሉም የአዲስ አበባ ከተማም ይሁን በሀገር አቀፍ ምርጫው ሁሉን ያሳተፈ የወጣቱ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ ወጣቱ በፍላጎቱ በልማት ላይ ተሳታፊ ነው ማለት አይቻልም፡፡ምክንያቱም ቁሳዊ የአዳራሽ ግንባታ የወጣቱን አስተሳሰብ በመቀየር ሰብዓዊ ልማት ማምጣት አልቻለምና፡፡
አስተሳሰብን ያህል ነገር ሁሉም በሌሎች ፍላጎትና ምርጫ ተፈጥሮን በሚሽር መልኩ አንድ እንዲሆን እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎዓዊ የተደረገበት አሳታፊ ቁሳዊ ልማትን ማምጣት አይቻልም፡፡ ሰርተናል እየተባለ የሚዘፈንለት ቁሳዊ ልማትም ቢሆን የወጣቱን የመንፈስ ልዕልና ሊገነባ ባልቻለበት ሁኔታ በሀገሪቱ ላይ ሁለንተናዊ እምርታ ለውጥ ማየት ይናፍቃል፡፡ ቀድሞ በየአካባቢው የነበሩ ሜዳዎችም ቢሆኑ አንዳንዶቹ በነበሩበት ቢቀጥሉም አብዛኞቹ ባለመኖራቸው፣ አዳዲስ የመኖሪያ ቤት ግንባታ የተደረገባቸውም ሆነ እየተደረገባቸው ያሉ አካባቢዎች የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያዎች ባለመታየታቸው ዋቱን ወደ አልባሌ ቦታ እንዲውል እያስገደዱት ይገኛሉ፡፡
ጎጂ የደባል ሱስ ግብዣ
በአሁን ሰዓት ወጣቱ በራሱ ጉዳይ እራሱ እንዲወስን ከማድረግ ይልቅ በደባል ሱስ ጥገኛ እንዲሆን የሺሻና ጫት ግብዣ እየቀረበለት ይገኛል፡፡ ይሄም በፊት እንደ ነውር ይታይባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሳይቀር ዛሬ ዛሬ እንደመልካም እየታየ እስከ ዩኒቨርስቲዎች መዝለቁ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነኚህን ድርጊቶች የሚያበረታታ የመንግስት አካል ባይኖር ኖሮ መኖሪያ መንደር ድረስ ዘልቀው ባልታዩ ነበር፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም የተመረቁና የሚመረቁ ወጣቶችም ቢሆኑ ከ15ዓመታት በላይ በእውቀት ግብይት በትምህርት ቢያሳልፉም ዛሬ ግን 15 ቀናት በማይፈጅ ስልጠና ያውም ጥቂቶችን በኮብል ስቶን ድንጋይ ጠረባ ስራ እንዲሰማሩ ይደረጋል፡፡ በርግጥ ማንኛውም ሙያም ሆነ ስራ የሌሎችን ሰዎች መብትና ጥቅም እስካልነካ ድረስ የሚናቅ ባይሆንም ለዘመናት ያካበቱት እውቀት ግን ሜዳ ላይ ሲወድቅ የሀገር ሀብት በከንቱ መባከኑን ማሳየቱ አይቀርም፡፡ በአሁን ወቅትም የያዝነው 2005ዓ.ም.ን ጨምሮ በየዓመቱ ከ 80 ሺህ በላይ የሀገሪቱ ወጣቶች በተለያየ የትምህርት ዘርፍ ቢመረቁም በሙያቸው የሚሰማሩት ግን 10ሺህ እንዳማይሞሉ ይገለፃል፡፡ ይሄ ደግሞ የእውቀት፣የገንዘብና የጉልበት ብክነት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
በሙያቸው ተደራጅተው የስራ ዕድል እንዳይፈጥሩም ስርዓቱ እና የስነ ህዝብ ፖሊሲው ዜጎችን ሙሉ በሙሉ የመንግስት ኢኮኖሚ ጥገኛ ስላደረገ በሚፈልጉት ሙያ መሰማራት አይችሉም፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ የገንዘብ ብድር ቢፈልጉ እንኳ የግድ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ተቀብለው በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በኢህአዴግ አባልነት ቅድመ ሁኔታ በየቀበሌ ያሉ ተራ ካድሬዎች ከላይ በሚወርድ መመሪያ መሰረት ለማደራጀት ይሚክራሉ፡፡ ውጤቱ ግን ወጣቱን አምራች ኃይል ከማድረግ ይልቅ የሙያና የኢኮኖሚ ነፃነት ስለሌለው ጥገኛ እንዲሆን አስችለውታል፤እያስቻሉትም ነው፡፡ ይሄ ካልተቀየረ ደግሞ የሀገሪቱ ወጣት ጊዜውን፣እውቀቱንና ጉልበቱን በከንቱ እንዲያባክን ያደርጉታል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በየመንደሩ እየፈሉ ያሉት የአልኮል መጠጥ ቤቶችና ጭፈራ ቤቶች አንዱ የልማት አካል እንጂ የሰብዓዊ ልማትን ወደ ኋላ የሚያስቀር ተደርጎ አልተወሰደም፡፡ በዚህ ምክንያት ወጣቱ ሰርቶ ከመለወጥ ይልቅ የሰራበትንም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል ምቹ ሁኔታ እንኳ ሲፈጠርለት አይታይም፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ለወጣቱ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆኑ የሚታወቁት የሐሳብ የበላይነት ላይ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ቦታ ባለመሰጠታቸው እንደ ሚዩዚክ ሜዴይ የመሳሰሉት የንባብን ባህል ለማዳበር የሚረዳው የመፅሐፍ ሐሳብ መወያያ አዳራሽ አጥተው አምስት ኪሎ በሚገኘው በጠባቧ ብሔራዊ ሙዝየም አዳራሽ ማየት ልማት ወዴት ወዴት ያሰኛል፡፡ ባንፃሩ አብዛኛውን ጊዜ የገዥው ኢህአዴግ ካድሬዎች መፈንጫ እየሆነ ያለውና በህዝብ አንጡራ ሃብት የተገነቡት የቀበሌ/የወረዳ አዳራሾች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ከኢህአዴግ ስራና ካድሬዎች በስተቀር ኸረ የሰው ያለህ እያሉ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ለሰብዓዊ ልማት ትኩረት ባለመሰጡ ነገ ሀገር ተረካቢ በሚባለው ወጣት ላይ ይነገድበታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፊት የወጣቶች መዝናኛ የነበሩ የስፖርት ሜዳዎችና የመናፈሻ ቦታዎች አንዳንዶቹ የህንፃ ግንባታ ሲሰራባቸው እንደነ ሂልተን አዲስ ሆቴል ፊትለፊት የነበሩ መናፈሻዎች ደግሞ ተከልለው ወጣቶች ዝር እንዳይሉባቸው ተደርገዋል፡፡
ከሌሎች መጠበቅንና መቀበልን መምረጥ
የተሻለ ነገርን በራስ ከመወሰን፤ እንዲሳካም ከመጠየቅ ይልቅ በሌሎች ላይ ጥገኛ በመሆን በሁሉም ነገር የመጠበቅና የመቀበል ብቻ አዝማሚያ በስፋት በወጣቱ ያስተዋላል፡፡ በዚህም የራሱን ጉዳይ ሌሎች እንዲወስኑለት በመፍቀዱ የራሱን ሚና አሳልፎ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ምርጫውን ከመፈለግ ይልቅ የመጣውን ብቻ የመቀበል ጉዳይ በስፋት ይስተዋላል፡፡
አማራጭ ሐሳቦችን ከራስ ጋር አስማምቶ ለመያዝም ሆነ የራስን ምርጫ ለማስተናገድ ይረዳ ዘንድ ነፃ የሆነ የሐሳብ ፍጭት ዕድል በመነፈጉ አሉታዊም ቢሆን ተቀብሎ የራስ ማድረግ እንደ አዋቂነትና ብልህነት እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ የትውልድ የአስተሳሰብ ብክነትንና ምክነትን በማንፀባረቅ ተተኪው ትውልድ ከማለት ይልቅ ጠባቂው ቢባል የሚስማማው ይመስላል ፡፡
ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ደግሞ በተለይ በወጣቶች ላይ እየተሰራ ያለው ሰብዓዊ ልማት በቁሳዊ በመሸፈኑ የሚመጣ ኋላቀር እሳቤ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ስርዓት የልማትን አስፈላጊነትና ምንነት በቅጡ ካለመረዳት የሚመጣ ደጋማ እሳቤ ሲሆን እራሱ ወጣቱም ቢሆን በእራሱ ላይ አሉታው ድርሻ እንዳለው ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ስለዚህ እምርታዊ |የሀገር ዕድገትና ለውጥ ለማምጣትና ሁሉን አቀፍ ገቢራዊ ልማት ለማስመዝገብ ቅድሚያ ሰብዓዊ ልማት መቅደም ይኖርበታል፡፡ ያኔ ቁሳዊ ልማትን በሚፈለገው መጠንና ዓይነት ማምጣት ይቻላል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: