የህዝብን ጥያቄ ማጣጣል የሚያመጣው መዘዝ

ቴዎድሮስ ባልቻ

በዓለም ላይ ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው መሪዎች ሁልጊዜ ዜጎቻቸውን እንደሚጨቁኑ ይታወቃል፡፡ እነኚህ ወደስልጣን ሲመጡ የነፃ አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን በውስጣቸው ያለው አምባገነንነታቸው ስለሚጫናቸውና በህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል ሲኖር ሁልጊዜ የሚመሩትን ህዝብ ያፍናሉ፡፡ ይህ እየበረታ ሲሄድ ደግሞ የፈራው  ህዝብ ድንገት ተነስቶ የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰማ አሸማቃቂ ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ ያኔ ህዝቡም ለጥያቄው ምላሽ እንደማያገኝ ሲገባው ወደ ህዝባዊ አመፅ መግባቱ ግድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነፃነትን ይሻልና፡፡

ጨቋኞች ደግሞ በባህሪያቸው ሁልጊዜ ፈሪዎች ናቸው፤ ለዛም ነው ለህዝብ ድምፅ ጆሮአቸውን የማይሰጡት፡፡ ለዚህም እንደ ቱኒዚያ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን እና ሶሪያን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይሄ ደግሞ አሁን ባለንበት ሁኔታ በኢትዮጵያም መከሰቱ የማይቀር ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የህዝብ ድምፅ ሊዘገይ ቢችልም ዋጋ አለው፡፡

በተለይ ባለፈው ሰኔ ወር በፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ዓለምን እያስደመመች ያለችውን ለህዝቡም የዴሞክራሲ ስርዓትን በመዘርጋት እየታወቀች ያለችው ብራዚል መሪዎች ለህዝብ ድምፅ እንዴት ዋጋ እንደሚሰጡ ትልቅ ምሳሌ ናት፡፡ የሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዘዳንት የሀገራቸውንና የህዝባቸውን ጥቅም ለማንም አሳልፈው ያልሰጡት ሉላ ዳ ሲልቫ ብራዚልን በዓለም የምጣኔ ሀብት ከእንግሊዝ አስቀድመው ስድስተኛ ደረጃ ቢያደርሷትም አዲሷ መሪ ከህዝባዊ አመፅ ሊታደጓት አልቻሉም፡፡

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የብራዚል መንግስት አስተዳደር በነዳጅ ዋጋ ላይ ድንገት የ 20 ሳንቲም የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ ሳይታሰብ የህዝቡ ለ ተቃውሞ ፈንቅሎ ይወጣል፡፡ ይሄኔ ፕሬዘዳንቷ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የህዝቡን ድምፅ መስማታቸው በማረጋገጥ የተደረገው ጭማሪ እንደተነሳ አስታወቁ፡፡ ህዝቡ ግን ድሮም በኑሮ ውድነቱ ሆድ ብሶታልና ያለውን ችግር በመጠቆም ሰልፉን በመላ ሀገሪቱ ከተሞች በስፋት አቀጣጠሉት፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዘዳንቷ ለተቃውሞ የወጡትን ሰዎች አመስግነው ህዝቡ ያነሳቸው ችግሮች በአፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡ አስታወቁ፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም ቢሆኑ ድንገት ፈንቅሎ የወጣውን ህዝብ ከመጠበቅ በስተቀር ዜጎቻቸው ላይ ጉዳት ለማድረስ አልሞከሩም፡፡

በኢትዮጵያም ሰኔ 1966 ዓ.ም. በነዳጅ ዋጋ ላይ በተደረገው የ5 ሳንቲም የዋጋ ጭማሪ ሰበብ ህዝቡ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጣም ንጉሱ አጼ ኃ/ስላሴም የህዝቡን ድምፅ መስማታቸውን በማረጋገጥ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ አንሰተናል አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ የአዲስ አበባ ህዝብ ከነዳጅ ጭማሪው በስተጀርባ የነበረው ጭቆና ስላለ የተቃውሞ ሰልፉን እንደማያቆሙ በማስታወቅ በወቅቱ እንደ መምህራን ማኀበር ያሉ ነፃ የሙያ ማኀበራትና መከላከያ ሰራዊት ከንጉሱ ይልቅ ከህዝቡ ጎን መቆማቸውን አረጋገጡ፡፡በወቅቱ ግን ንጉሱ ለተቃውሞ የወጣውን ህዝብ ጣያቄም ሆነ ድምፅ አላጣጣሉም ነበር፡፡ የዚህ እርሾ ንጉሱን መስከረም 2 ቀን 1967ዓ.ም. ከስልጣናቸው አወረዳቸው፡፡

በቅርቡ የመሐመድ ቡዓዚዝ እራሱን ማቃጠሉና አረቡ አብዮት መከሰቱን ተከትሎ የቱኒዚያ ህዝብ በቤን ዓሊ ላይ ተቃውሞ ሲያሰማ ፕሬዘዳንቱ ህዝቡን በክፉ ከመፈረጅ ይልቅ ከስልጣን ወርደው በሳውዲ ዓረቢያ ጥገኝነት ሊጠይቁ ችለዋል፡፡ ነገር ግን በግብፅ፣ በሊቢያ፣ በየመንና በሶሪያ መሪዎች ላይ ህዝቡ ተቃውሞ ሲያሰማ መሪዎቹ ከማጣጣላቸው በተጨማሪ ህዝቡን አሸባሪ፣ የአልቃይዳ ተላላኪ፣…እያሉ ይፈርጁ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ተቃውሞ ያቀረበውን ህዝብ አሸባሪ ካሉት መሪዎች መካከል የሶሪያው በሰር አላሳድ በጦራቸው ህዝብን ለመጨረስ ቢሞክሩም እሳቸው እስካሁን ሰላም አላገኙም፡፡ በአንፃሩ በአፍሪካ መሪዎች እጅግ የተፈሩና የተከበሩ የነበሩት የሊቢያው መሪ ሙዓሙር ጋዳፊ ከአማረው ቤተመንግስታቸው አምልጠው ለፍሳሽ ማስወገጃ በተውልድ አካባቢያቸው ቤንጋዚ ላይ ባሰሩት ቱቦ ተደብቀው ለማምለጥ ሲሞክሩ የውርደት ሞትን ተከናንበዋል፡፡

የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ ደግሞ 1.2 ሚሊዮን ልዩ ደህንነት እንዳላቸው ቢታወቅም የህዝቢ ቁጣ ፈንቅሎ በመውጣቱና ለህዝብ ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ከመስጠት ይልቅ ማስፈራራትና ዛቻ ቢፈፅሙም ከሞቀና ከተከበሩበት ቤተመንግስት በውርደት ተባረው ቆመው መሄድ እንኳ ሳይችሉ በህመምተኛ አልጋ ላይ ሆነው ለፍርድ መቅረባቸው የማይረሳ ነው፡፡ የየመኑም ቢሆኑ ከስልጣኔ አልወርድም ፣ ወይፍንልች እኔ አብደላ ሳላ ያሉት ፕሬዘዳንት የህዝቡን ድምፅ ከመስማትና በጎ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ፍረጃና ማስፈራራቱን ቢያያዙትም አልሆነላቸውም፡፡ በመጨረሻም  ለተቃውሞ የወጣውን ህዝብ በድጋሚ ለማስፈራራትና ደጋፊዎቻቸውን ከጎን በማሰለፍ ህዝቡን ለስልጣናቸው ሲሉ ሊከፋፍሉ ሲሞክሩ በአደባባይ ንግግር ላይ ሳሉ የጥይት እሩመታ አስተናግደው ከሞት ቢተርፉም ሳይወዱ በግድ ስልጣን በቃኝ ብለው ከሀገራቸው ውጭ በስደት ጥገኝነት ለመኖር ተገደዋል፡፡

በዘመነ ኢህአዴግ በኢትዮጵያም የታመቀ ህዝባዊ ብሶት እንዳለ የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጥናት ያረጋገጠ ቢሆንም እውነትነት ስለመኖሩ ለኢትዮጵያውያን ነጋሪ አያሻም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ያለው ችግር እስከዛሬ በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቀው  የዘረኝነት ከፋፍለህ ግዛ የቅኝ አገዛዝ ስልት ከጥቂት ለስርዐሳቱ ከቀረቡ ቡድኖች በስተቀር ያለው የፖለቲካ፣ምጣኔ ሃብትና ማኀበራዊ ችግር እንዲሁ በቀላሉ የሚቀረፍ አይመስልም፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ህዝብ መስርዓቱ ምንደኛ በሆኑ በመንደር ካድሬዎች የአፈና ቋፍ ውስጥ በመውደቅ በጓዳ ሲያጉረመርም ደፋሮች ደግሞ በአደባባይ ተቃውሟቸውን በአደባባይ ማሰማታቸው አልቀረም፡፡

መንበረ ስልጣኑን በህዝብ ተመርጬ ስልጣን ይዣለሁ የሚለው አካል  በህዝብ ተመርጦ ዛሬም ድረስ ሀገርና ህዝብ ይጎዳሉ የሚሏቸው ተግባራት በገዥው ስርዓት ሲፈፀሙ ልክ እንደ ደቡብ አፍርካ አፓርታይድ ስርዓት አሊያም እንደነ ሆስኒ ሙባረክና ሙዓሙር ጋዳፊ አስተዳደር የሚቃወሟቸውን አሸባሪ ብሎ መፈረጅና ማሰር እንደ ፋሽን እየታየ ሲሆን ይህም በስልጣን ላይ ያለው አካል ህዝባዊ ይሁንታ አለኝ ብሎ ስልጣን የመያዝ ምንነት አልገባውም፣ አሊያም ለማወቅም የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ህዝባዊ እውቅና ያለው ፤ ያውም በምርጫ ይሁንታ አግኝቻለሁ የሚል አካል በተለይም በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ 96.9 % የህዝብ ድምፅ አግኝቻለሁ የሚል እንዴት ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚፈራ ሲታሰብ እጅግ የሚደንቅ ተግባር ነውና፡፡

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታም በርካቶች የዚህ ሰለባ የሆኑ ሲሆን አሁን አሁን ግን ሰው ከፍርሃት ወጥቶ ኢህአዴግን ደግፎ ካልሆነ ተቃውሞ ማሰማት ባልተፃፈ ህግ የተከለከለ ቢሆንም ህዝቡ ግን ተቃውሞ ለማሰማት የሚታገስ አይመስልም፡፡ ስለሆነም የራሱ አባላትን ጨምሮ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርጉ የፍትህ መጓደል፣ የኑሮ ውድነት፣ ስራ አጥነት፣ የዜጎች በግፍ መፈናቀል፣…ሰውን ሰላም የነሳው ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት በመላ ሀገሪቱ በሚባል ደረጃ የታፈኑ ድምፆች በስፋት መስተጋባት ጀምረዋል፡፡

በተለይ በቅርቡ በግንቦት 2005 ዓ.ም. ሰማያዊ ፓርቲ በአዲሳ አበባ የተቃውሞ ሰላማዊ ማድረጉ፣ አንድነት ፓርቲ ደግሞ በያዝነው ሐምሌ 2005 ዓ.ም. በጎንደርና በደሴ ያደረገው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ከአፈናው አንፃር ሲታይ መቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ በተለይ በሰልፎቹ ላይ ፓርቲዎቹ ካዘጋጁት መፈክር በተጨማሪ በሀገራችን ሰላም አጣን፣ፍትህ አጣን፣…የሚሉ ድምፆች መበራከት የነገውን ቀን ለመተንበይ አስቸጋሪ አያደርገውም፡፡

በስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ እነኙህ ድምፆች እንዳይሰሙ የመንደር ካድሬዎች በየቤቱ እየሄዱ ሰው ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይወጣ እንዲያስፈራሩ መደረጉን ከደሴና ከጎንደር ነዋሪዎች በስፋት የተሰማ ሲሆን ህዝቡን ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከመውጣት ያገደው ግን አልነበረም፤ ያውም በደሴ ወደ 50 ሺህ በጎንደር ደግሞ ወደ 40ሺህ ሰው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም መንግስት የህዝቡን ድምፅ ከመስማትና ከማሳዳመጥ ይልቅ ለሰልፉ የወጡትን ሰዎች የሙስሊም አክራሪዎች ናቸው፣ በሰልፉ የወጣው ህዝብ ትንሽ ነው እያለ ለማጣጣል መሞከሩ አሁንም ለህዝብ ያለውን አመለካከትና አምባገነኖች መውደቂያቸው ሲደርስ የሚፈፅሙትን ቅደም ተከተል ተግባር ከማንፀባረቅ ይልቅ የሚፈይደው አንዳች ነገር የለም፡፡ ይህ አካሄድ ለነ ሙባረክና ለነ ጋዳፊም አልሰራምና፡፡

በተለይ አንድነት ፓርቲ አሁን በያዘው አቋም እና እቅድ የሚቀጥል ከሆነ ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩና ሰማያዊ ፓርቲም በነሐሴ ወር ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱ በቅርቡ ከወጣው ህዝብ በብዙ ሺህ እጥፍ ሊወጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ መንግስት የህዝቡን የተቃውሞ ድምፅና ጥያቄ ከመስማትና እርምት ለመውሰድ ከመሞከር ይልቅ ለማጣጣል መሞከሩ ህዝቡን የበለጠ ለተቃውሞ እንዲነሳሳ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ምናልባት መንግስት ከዚህ በኋላ እንደባለፉት 8 ዓመታት ለተቃውሞ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት እውቅና አልሰጥም ቢል እንኳ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያላቸው ፓርቲዎች የመሪነት ሚናቸውን መወጣት ከቻሉ ህዝቡን ከመውጣት የሚያግደው አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የታፈኑ ድምፆች እያየሉ ሲሄዱ በድንገት አንድ ቀን መፈንዳታቸው አይቀርምና፡፡

አንድነት ፓርቲ ሐምሌ 7 ቀን 2005ዓ.ም. እንዳካሄደው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ከሆነ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በህዝቡ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ቢያዝ እንኳ የፀጥታ ኃይሉ እሱም የማኀበረሰቡ አካል በመሆኑ በመጨረሻ ህዝባዊ ወገንተኝነት ማሳየቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህ የህዝብን የተቃውሞ ሰልፍ እና አቤቱታ ማጣጣል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እጅግ ማመዘኑ የማይቀር ስለመሆኑ በያዝነው ዓመት የምናየው እውነታ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

ከ1997ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ ኢህአዴግ ከወሰዳቸው የጭካኔ እርምጃ በኋላ ሰው በመኝታውና በጓደው ካልሆነ በቀር የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ይፈራ የነበረ ሁላ አሁን አሁን ግን በተለያየ የትራንስፖርት መስክ (በየታክሲ፣ አውቶቡስ ውስጥ፣…)፣ በየንግድ ተቋማትና በየቢሮ የቅሬታ ድምፆች በድፍረት መደመጥ ጀምረዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የታፈኑ ድምፆች ቀስበቀስ መውጣታቸው ይበል የሚያሰኝ ሲሆን በዚህም የመንግስት ግትር አቋም የሚቀጥል ከሆነ ባልታሰበ ሰዓት አንድ የለውጥ ክስተት መፈጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ በባህሪው እንደተጨቆነ እና እንደታፈነ ዘለዓለም የሚኖርበት የህይወት ሂደት የለውምና፡፡

Leave a comment