መብራት ለኤርትራ በነፃ ከተሰጠ ለእኛስ?

 

ብስራት ወ/ሚካኤል

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመችው በዘመነ ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ አባ ሳሙኤል በሚባል ስፍራ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ጊዜው በ1890 ዓ.ም. ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከውሃ ኃይል ማመንጨት የተጀመረው ግን በ1904 ዓ.ም. ከአቃቂ ወንዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በአሁን ሰዓት ግን አድጎ በርካታ ግድቦች በአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን ተሰርተው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

ከውሃ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ግድቦች እየተሰሩ ቢሆንም የአቅርቦት እጥረትና የጥራት አገልግሎቱ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል፡፡ በተለይ አሁን አሁን መብራት ድንገት የመጥፋቱ ነገር ከምን የተነሳ እንደሆነ እስካሁን ባይገለፅም አዲስ አበባን ጨመሮ በተለያዩ የክልል ከተሞችም በተደጋጋሚ ይቋረጣል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ተጠቃሚዎች መብራት እንደሚጠፋ በኮርፖሬሽኑ ቀድሞውኑ የተነገራቸው ባለመሆኑ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪዎች ከጥቅም ውጭ እየሆነ ለወጭ የተዳረጉ ቢኖርም ከድርጅቱ የተሰጠም ሆነ የሚሰጥ ካሳ የለም፡፡ በዚህም የንግድ ተቋማት ሆቴሎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ሱቆች፣…ወዘተ ይገኙበታል፡፡power1

አመራሮቹም ቢሆኑ አልፎ አልፎ ድንገት የመብራት መቋረጥ ችግር ከለኃይል አቅርቦት የተፈጠረ ሳይሆን በቴክኒካል ችግር መሆኑን ሲገልፁ ቢሰማም ችግሩ ግን አሁንም ድረስ እንዳለ አለ፡፡ ተቋሙ ምንም እንኳ ከሀገሪቱ አንጋፋ ተቋማት አንዱ ቢሆንም ከዚህ በፊት ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት በኢንቨስትመንቱ እንቅስቃሴ ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ቢጠበቅም በተደጋጋሚ ከሚሰጡ ተመሳሳይ የቴክኒክ ችግር ከሚል መልስ ውጭ የተጠቀሰ ችግር የለም፡፡

በነ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የቦርድ ሊቀመንበርነት፣ በነ አቶ ምህረት ደበበ ዋና ስራ አስፈፃሚነትና እና በነ ብርጋዴር ጄነራል ክንፈ ዳኘው የቦርድ አባልነት የሚመራው ይህ ተቋም በውስጡ 12,172 ሰራተኞችን እንደያዘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ካሉት ሰራተኞች መካከልም በቅርቡ ከአስራ አንድ ያላነሱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በሙስና ተግባር ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ ይገኛል፡፡ እንደ አቃቤ ህግ ክስ ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ ከ 25 ሚሊዮን ዶላር (ከ 471 ሚሊዮን ብር) በላይ የህዝብና የመንግስትን ጥቅም ማሳጣታቸውን ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ የኃይል ማመንጫፕሮጀክቶች እየተመረቁ መሆኑ በተደጋጋሚ ቢገለፅም አሁን ለሀገሪቱ ጥቅም እየሰጠ ያለው አቅም ግን ከ2000 ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ የተቋሙ የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

ዋና መስሪያ ቤቱን አዲስ አበባ ፒያሳ ደጎል አደባባይ ፊትለፊት ያደረገው ይህ ተቋም እስከ ፊታችን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሀገሪቱን የመብራት ኃይል ፍጆታ ወደ 10,000 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ቢያቅድም አሁን በቀሩት አራት ዓመታት ውስጥ ግን ቀሪውን 8,000 ሜጋ ዋት ከየት አምጥቶ ጥቅም ላይ እንደሚያውለው እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ምናልባት የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ከፊታችን በቀሩ 4 ዓመታት ውስጥ ቢጠናቀቅ እንኳ የኃይል ፍጆታውን ሊያሳድገው የሚችለው ወደ 8,000 ሜጋ ዋት ሲሆን ግድቡም ወዲያው አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፣ የግድቡ ውሃ ሙላት በራሱ እረጅም ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፡፡

በሀገሪቱ ያለውን የኢቨስትመንት ሴክተር ከማስፋፋት አንፃር የመሰረተ ልማቶች በአግባቡ መሟላት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ቢታወቅም የህዝቡ ፍላጎትም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ከአሁኑ ሌሎች የኃይል አቅርቦት አማራጮችም ካልተወሰዱ ነገ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ችግር መግጠሙ የማይቀር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እንደ ከዚህ በፊቱ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሰራተኛ ቅነሳ በር በመክፈት የስራ አጥ ቁጥርንም አሁን ካለው ከእጥፍ በላይ ሊያሳድግ እንደሚችል ይገመታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ለውጭ ምንዛሪ ሲል የዜጎችን ፍላጎትና አቅርቦት በአግባቡ ሳያሟላ ለጎረቤት ሀገሮች በተለይም ለጅቢቲ 200 ሜጋ ዋት በይፋ መሸጡን መረጃዎች ሲጠቁሙ፣ ለሱዳን 200 ሜጋ ዋት ደግሞ ለመሸጥ የመስመር ዝርጋታው ተጠነቆ ሙከራ ላይ እንዳለ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በቀጣይም መንግስት ለኬንያም 500 ሜጋ ዋት ለመሸጥ ስምምነት ላይ መድረሱ የተጠቆመ ሲሆን ይህ መቼ እና እንዴት እንደሚተገበር ወደፊት አብረን የምናየው ነው፡፡ ምክንያት የአሀገሪቱ የኃይል አቅርቦትና ፍላጎት አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተሟልቷል ማለት አይቻልምና፡፡እንደ መንግስት ከሆነ ግን ወደፊትም ለሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካ የመብራት ኃይልን በመሸጥ ከቡና ንግድ በተሻለ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ማቀዱ አይዘነጋም፡፡ ምክንያቱም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ኢትዮጵያ የነፋስና ከእንፋሎት ኃይል ውጭ ከውሃ ግድብ የሚገኝ ብቻ 45,000 ሜጋ ዋት  የመብራት  ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ያሳያልና፡፡

ከሰሞኑን በተለይ ባለፈው ሐምሌ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. በተለያዩ መረጃዎች እንደተገለፀው እና ይህንም የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳህል በለንደን ለኤርትራ ማኀበረሰብ ገለፁት እንደተባለው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ 250 ሜጋ ዋት የመብራት ኃይል በነፃ ለመስጠት በራሺያ፣ በኳታር እና በቱርክ በኩል ድርድር መጠየቁ ተጠቁሟል፡፡ ይሄ ደግሞ መንግስት የራሱን ዜጋ ፍላጎት ሳያሟላ ከደሃ ህዝብ አንጡራ ሃብት የሚገነቡ ግድቦችን ለኤርትራ ለምን በነፃ መስጠት እንደተፈለገ እስካሁን አልተገለፀም፡፡ይህ እውን የሚሆን ከሆነ በኢትዮጵያ ህዝብ በጀትና ሃብት እራሷን ችላ እንድትገነጠል የተደረገችው የኤርትራ ዜጎች በነፃ ከሚሰጣቸው የትምህርት ዕድል ተጨማሪ መሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች ዓይነት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት 250 ሜጋ ዋት በነፃ የመብራት ኃይል ለኤርትራ ለመስጠት እንደ ድርድር መነሻ አንስቶታል ስለተባለው ጉዳይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጠይቀናቸው “ውሸት ነው፣ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አላቀረበም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እና በየከተሞቹ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ደስንገት እየጠፋ ስላለው የመብራት መጥፋት እንዲሁም ለጅቡቲና ሱዳን

ተሸጧል ስለተባለው የመብራት ኃይል ጉዳይ ምላሽ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደሆኑት አቶ ምስክር ነጋሽ ጋር ብንደውልም በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው ምላሻቸውን ማግኘት አልቻልንም፡፡መንግስት ለኃይል ማመንጫ ግድቦች መስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት እሰየው ከዚህ በተሻለ ይቀጥል እያልን አሉ በሙባሉ እና ከላይ በተነሱ ችግሮች ዙሪያ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎችም ሆኑ ሌላ የሚመለከተው አካል ምላሽ ለመስጠት ቢፈልግ የዝግጅት ክፍሉ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች በተደጋጋሚ ድንገት የመብራት መጥፋት በንብረትም ሆነ በዕለታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር ምንነት እስካሁን ከሚመለከተው አካል የተሰጠ ምላሽ ባለመኖሩ በኃይል አቅርቦትና አገልግሎት ላይ ነገ ምን ሊከሰት እንደ ሚችል ለመተንበይም ሆነ ለመዘጋጀት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ እዚህ ላይ ኮርፖሬሽኑም ሆነ ሌላ የሚመለከተው የመንግስት አካል ከወዲሁ ለደንበኞቻቸው የቅድመ ማስጠንቀቂያም ይሁን የእርምት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ መጠቆም እወዳለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግስት የመብራት ኃይልን ለውጭ ምንዛሪ መሸጥ እንኳ ቢፈልግ ቅድሚያ የሀገር ውስጥ ፍጆታን በአግባቡ መሸፈን ያለበት ይመስለኛል፡፡

 

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: