ብስራት ወ/ሚካኤል
ህገመንግስት በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር የህግ የበላይነት ይሰፍን ዘንድ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ሆኖ የሚያገለግል ሰነድ ነው፡፡ ይህ ህግ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ዓይን ከህግ በታች አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የህግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ ለህግ የበላይነት መከበር ደግሞ የመንግስት ተቋማት ህዝባዊ አመኔታ ሲኖራቸውና ለህዝቡና ለሀገሪቱ ጥቅም የቆመ የመንግስት አስተዳደር ሲኖር ብቻ ነው፡፡
የህግ የበላይነት ከሌለ አንድ ህገ-መንግስት የቱንም ያህል ጥሩ ሐሳቦችን ያዘለ የመብት ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ የሚችሉ ቃላት ቢኖሩት እንኳ ተግባራዊ ሊደረግ ካልቻለ ዋጋ የለውም፡፡ በተለይ የህገመንግስት የበላይነት ካልተከበረ የመንግስት ለህዝብ ያለው ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከመግባቱም አልፎ ጥቂት ግለሰቦች የበላይነት ብቻ ከህግ በላይ ሆነው ዜጎችን እንዲጨቁኑ በር ይከፍታል፡፡
የህግ የበላይነት አለመከበር ደግሞ በዜጎች መካከል አድሏዊነትና የፍትህ መጓደልን ስለሚያስከትል ዜጎችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስዳቸዋል፡፡ ይህም በሀገር ላይ ስርዓት አልበኝነትን ከማስፈኑ በተጨማሪ የመንግስት የፍትህ ተቋማት በህብረተሰቡ ግብር የጥቂት ባለስልጣናትና ሃብታሞች የጥበቃ ተቋም በመሆን የሆዳቸው ባሪያ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የውጭ ኃይሎች በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ሁለንተናዊ ጥቅም ላይ ጣልቃ እንዲገቡ አዝና ለአደጋ እንዲያጋልጡ ዕድል መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው እንዳይሆን ደግሞ ህገ መንስቱን መሰረት በማድረግ ለዜጎች ከለላና ጥበቃ ሊያደርግ የሚችል አዋጅ ለወጣ ይችላል፡፡ ህገመንግስቱ በአዋጅ እስካልተሻሻለ ድረስ አዋጅ ደግሞ በምንም መልኩ ከህገመንግስቱ ጋር የሚቃረን አንቀጽም ሆነ አንዲት ቃል ሊኖር አይገባውም፡፡ ከህገመንግስቱ ሐሳቦችና አንቀፆች ጋር የሚጋጭ ሓሳብም ሆነ አንቀጽ በአዋጁ ላይ ካለ የህግ የበላይነት ሊኖር አይችልም፡፡
ኢትዮጵያና ህገመንግስቷ
ኢትዮጵያም እንደማንኛውም ሉዓላዊ ሀገር የራሷ ህገመንግስት አላት፡፡ ወጥ የሆነ የተፃፈ የህገመንግስት ሰነድ መጠቀምና በዚህም መተዳደር የጀመረችው ከዘመነ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ፣ በዘመነ ደርግ (የኢህዴሪ ህገመንግስት) እና አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ መንግስት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት የሀገሪቱን ህዝብ የሚመራበትም ሆነ የሚያስተዳድርበት ሰነድ ከመሆኑ በተጨማሪ ከአድሏዊነት በፀዳ መልኩ የዜጎችን መብትና ጥቅም አክብሮ ማስከበር የሚያማስጠበቅበት ገዥ ሰነድ ነው፡፡
ይህን ሰነድ ገዥውን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች አክብረው የሚያስከብሩበትም ጭምር እንጂ የጥቂት ግለሰቦች አሊያም ስራ አስፈፃሚ ባለስልጣናት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ የትኛውም ህግም ሆነ ሰነድ ለሁሉም ሰው ምሉዕ እና ፍፁም ምርጥ ነው የሚባል ባይኖርም የሚሻሻሉ ህጎች በህግ አግባብ እስኪሻሻሉ ድረስ ሁሉም ሰው በእኩል ላለው ህገመንግስት ተገዥ የመሆንና የማክበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህም በህገመንግቱ አዋጅ ቁጥር 1/1987 የህገ መንግስት የበላይነት በሚለው ስር አንቀጽ 9(2) ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ማንኛውም አዋጅ፣ ደንብና መመሪያም ሆነ ትዕዛዝ ከህገመንግስቱ የበላይ ሊሆኑ እንደማይችሉ ያሳያል፡፡ ይህም ማለት የትኛውም አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ተፈፃሚነት ሊኖራቸው የሚችለው የህገ መንግስት ጥሰት ከሌለባቸውና ህገ መንግስቱን ተንተርሰው ከወጡ ብቻ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ተግባራዊ ሊሆኑ እንደማይችሉ እና ሊሆኑም እንደማይገባ በግልፅ ተቀምጧልና፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በህገመንግስቱ አንቀጽ 9(1) ላይ “ህገ መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ነው፡፡ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፤ እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከዚህ ህገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡” ይላል፡፡ ነገር ግን ይህን ህገመንግስት የሚጥሱ በርካታ አንቀፆች እንዳሉት የሚነገርለት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ የህገመንግስት ጥሰት አለበት በሚል ከሚነሱት መካከል ጥቂቶቹን እንይ፡፡
የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ እና ህገ መንግስቱ
ሽብርተኝነት በምንም መመዘኛ በማንነኛውም ሰው ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡ ድርጊቱም የግለሰብን፣ የማኀበረሰብን፣ የህዝብንና የሀገርን ብሎም የዓለምን ህዝብ ህይወትና ንብረት አደጋ ላይ የሚጥል አሰቃቂ ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር በግለሰብ፣ በቡድን እና በህጋዊነት ጥላ ስር ባሉ የመንግስት ባለስልጣናት ሊፈፀም የሚችል የተወገዘ ተግባር ነው፡፡ ድርጊቱም አካል ማጉደልን፣ ንብረት ማውደምን ፣ ጤናን ማቃወስን እና የህዝብን ኑሮ ማናጋትን እንደሚጨምር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ያለችበት ቀጠና ለሽብር ተግባር ተጋለጠ ቢሆንም እጅግ ተመራጭ የሆነ የህገመንግስት ጥሰት የሌለበት የቆየ እና እየሰራ ያለ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቢኖራትም በገዥው ኢህአዴግ አማካኝነት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አውጥታ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከገዥው በኩል አዋጁ የወጣው የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ለመጠበቅ ነው ቢባልም በህግ ባለሙያዎች፣ በፖለቲከኞች፣ በጋዜጠኞች እና በበርካታ ሌሎች ዜጎች አዋጁ የህገ መንግስ ጥሰት ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ለማፈን እና የኢህአዴግ ሹማምንትን ስልጣን ለማራዘም ነው በሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል፤ እየቀረበበትም ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ በህገመንግስቱ አንቀጽ 55(1) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር በሚለው ስር “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ ህገ መንግስት መሰረት ለፌደራሉ መንግስት በተሰጠው የስልጣን ክልል ህጎችን ያወጣል፡፡” ይላል፡፡ አዋጁም በዚህ መሰረት ከመውጣቱ በስተቀር ህገ መንግስቱን የሚጥስም ቢሆን ተግባራዊ እንደሚደረግ የሚገልፅ ድንጋጌን አያሳይም፡፡ ስለሆነም አዋጁ መውጣት የነበረበት ህገመንግስቱን መሰረት አድርጎ እንጂ ከህገመንግስቱ ተቃርኖ ያላቸው ድንጋጌዎችን ማውጣት አይችልም፤ ቢወጣ እንኳ ተፈፃሚነት ሊኖረው እንደማይችል እራሱ ህገ መንግስቱ ያስቀምጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ታዋቂው የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ አሁን መንግስት እየተጠቀመበት ያለው የፀረ-ሽብርተኝነት የህግ ካሉት የህገመንግስት ጥሰቶች በተጨማሪ ሁሉም የወንጀል ድርጊቶች የሀገራችን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ላይ ስለተጠቀሱ አስፈላጊነቱ አይታየኝም ይላሉ፡፡ይሄንንም ሐሳብ አንድነት ፓርቲ እና አመራሮቹም በተደጋጋሚ ሲገልፁት ይሰማል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር(መድረክ) ቀደም ባሉት ጊዜያት ሁሉ አዋጁ የኢህአዴግን ለረጅም ጊዜ በስልጣን ለመቆየት ከለላ በመሆን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችን ለማፈን ሆን ተብሎ እንደወጣ ሲቃወሙ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ እውን ህገመንግስቱን ጥሷል? ወይስ አልጣሰም? የሚለውን መረዳት እንዲያስችል ጥቂት አንቀፆችን እንመልክት፡፡
በህገመንግስቱ አንቀጽ 26(1) የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት በሚለው ስር “ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ፣ግላዊነቱ፣የመከበር መብት አለው፡፡ ይህ መብት መኖሪያ ቤቱ፣ ሰውነቱና ንብረቱ፣ ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረቱ ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡” ይላል፡፡
በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 21 ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ በሚለው ስር ደግሞ “ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሑፉን፣የጣት አሻራውን፣ ፎቶግራፉን፣ የጸጉሩን፣ የድምፁን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን( የዘር ፈሳሽን ሊጨምር ይችላል)፤ ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ (ለተጠርጣሪው ጤንነት አይደለም) ሊያዝ ይችላል፡፡ ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል፡፡” ይላል፡፡ በዚህ ፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ መሰረት ፖሊስ አቅሙ በፈቀደ ደብድቦ ማሳመን ባይችል እንኳ በእጁ ባለ በጦር መሳሪያ በመታገዝ በሚወስደው እርምጃ የተጠርጣሪውን በህገመንግስቱ የአካል ደህንነት እና ግላዊ ህይወቱ የመጠበቅ መብትን በመግፈፍ አካል ጉዳተኛ እንዲያደርግ ሁሉ እድል ይሰጣዋል፡፡ ነገር ግን ተጠርጣሪው ከተከሰሰበት ወንጀል ነፃ ተብሎ ቢለቀቅ እንኳ በፖሊስ በተፈፀመበት የኃይል እርምጃ ጤነኛው ሰው አካል ጉዳተኛ ሆኖ ይወጣል ማለት ነው፤ ለዚህ ደግሞ የጉዳት ካሳም ሆነ ይቅርታ የለውም፡፡
ሌላው በህገመንግስቱ አንቀጽ 26(2) ማንኛውም ሰው በግል የሚፅፋቸውና የሚጻጻፋቸው፣ በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌኮሚኒኬሽንና በኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም፡፡” ይላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29(1-2) የአመለካከትና እና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት በሚለው ስር “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል፡፡ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለፅ ነፃት አለው፡፡ ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በፅሑፍ ወይም በህትመት፤ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡” ይላል፡፡
በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 14(ሀ-ሐ) መረጃ ስለማሰባሰብ በሚለው ስር ደግሞ “በሽብርትኝነት የተጠረጠረን ሰው(የተፈረደበት አይልም) የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬዲዮ፣ የኢንተርኔት፣የኤሌክትሮኒክስ፣የፖስታና የመሳሰሉ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል ፤ ጠለፋውን ለማስፈፀም ወደ ማናቸውም ቤት ውስጥ በሚስጥር ለመግባት (የመንደር ሌቦች ተግባር ዓይነት)፤ይህንኑ ለመፈፀም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት፤ ይችላል፡፡” ይላል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሰረት ደግሞ ዜጎች ከላይ በተጠቀሰው በህገ መንግስቱ መረጃ የማግኘት፣ የመቀበልና የማሰራጨት መብትን ጨምሮ የፈለጉትን አመለካከት ይዘው በፈለጉት የመረጃ ማሰራጫ ዘዴ ሐሳባቸውን እንዲገልፁ የተደነገገውን መብት በግልፅ ይጥሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ግለሰብ የሚለዋወጣቸው መረጃዎች በሙሉ እንዲጠለፉ፣ በቤተሰብ መካከል የሚደረግ ጨዋታና ሌሎች የፆታዊ ፍቅር ግንኙነቶች ጭምር በደህንነት ኃይሎች መሳሪያ እንዲቀረፁ እና የግል ምስጢር በቀላሉ እንዲባክን በማድረግ ተፈጥሯዊና ከላይ የተጠቀሰውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 26(2) እና 29(1-2) ጋር በግልፅ ይቃረናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት መብትንም እንዲሁ የሚገድብ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የአዋጁ መኖር ለህዝቡ ምን ጠቀመ?
በስራ ላይ የዋለው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖው ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ በአዋጁ ስም በዋነኝነትም በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዳይከበርና የገዥው አመራሮች እንዳሻቸው እንዲናኙ ዕድል ሰጥቷል በሚል ውግዘት እየገጠመው ነው፡፡ በዋነኝነት ደግሞ የህገ መንግስት ጥሰት ስላለበት ተፈፃሚ መሆኑ በራሱ ህገወጥ ነው የሚሉ የህግ ባለሙያዎችም አልታጡም፡፡ከዚህም በተጨማሪ ገዥዎች ዜጎችን ፈሪ በማድረግና በማሸማቀቅ በራሳቸውም ሆነ በሀገራቸው ጉዳይ ጉልህ ሚና እንዳይጫወቱ በማድረግ የወደፊት የሀገሪቱን ደህንነትና አንድነት ይንዳል ሲሉ የሰጉም አልጠፉም፡፡
ከላይ እንዳየነው ከሆነ ደግሞ ጎልቶ የሚታይ የህገ መንግስት ጥሰት እንዳለ ያሳያል፡፡ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ህግ ያወጡ፣ የተረጎሙና ያስፈፀሙ አካላት ሁሉ ህገ መንግስቱን እንደናዱ ይቆጠራል፡፡ ይሄ ደግሞ በሀገሪቱ ከፍተኛውን የወንጀል ድርጊት በመፈፀም የሚያስቀጣ ቢሆንም በዚህ የተቀጣ ህጉን አውጥቶ ያፀደቀው የፓርላማ አባል፣ አዋጁን ተንተርሶ ውሳኔ የሰጠ (የፈረደ) ዳኛ፣ አዋጁን ተንተርሶ ክስ ያቀረበ አቃቤ ህግ፣ አስፈፃሚው ፖሊስ፣ሚኒስትርና ጠቅላይ ሚኒስትር የለም፡፡ ይልቁንም አዋጁ ህገመንግስታዊ መብቶችን የሚጥስ በመሆኑም የህገመንግስት ጥሰት ነው በሚል ሲቃወሙ የነበሩና በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን መብት ሲጠቀሙ በአዋጁ ወንጀል ናቸው በሚል ለእስር፣እንግልትና ስቃይ እንዲሁም ለስደት የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየተበራከተ እንደሚገኝ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎች እንደሚገኙበት ይጠቀሳል፡፡
አዋጁ የዜጎችን ሰላምና ደህንነትን ለመጠበቅ ነው ቢባልም እስካሁን በአዋጁ የቅጣት ሰለባ የሆኑት ኢትዮጰረያውያን እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከውጭ ዜጎች ሁለት ሲውድናውያን ጋዜጠኖች የእስር ሰለባ ቢሆኑም በስውዲን መንግስትና በአውሮፓ ህብረት ጫና ከአንድ ዓመት እስር ቆይት በኋላ በይቅርታ ተለቀው ወደ ሀገራቸው ሲገቡ በተመሳሳይ ወቅት ታስሮ የነበረው ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ የይቅርታ ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን በእስር መማቀቁ ህጉ ዜጎችን ለማፈን የወጣ ነው በሚል በአስረጂነት መቅረቡ አሌ አያስብለውም፡፡
መንግስት እስካሁን ጠረጠርኳቸው ያላቸውን ገና ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ሳይበይንባቸው አሸባሪዎች በሚል በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን መስኮት ቢናገርም የሚከሳቸው ሰዎች ፈፀሙት የተባለውን የሽብር ተግባር ግን በግልፅ ሊያሳይ አልቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተከሰሱት ሰዎች በሀገሪቱ በተለያየ መስክ በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው በመታየታቸው መንግስት በተለይም ገዥው ኢህአዴግ የራሱን የስልጣን ስጋት የሀገር ስጋት አድርጎ ከማቅረቡ ውጭ እስካሁን አሳማኝ ነገር አለማቅረቡ መንግስት በህዝቡ ዘንድ እምነት እንዲያጣ አስችሎታል በሚል እየተብጠለጠለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አዋጁ ለህዝቡ ጠቅሟል የሚባል ተጨባጭ ነገር ባይታይም ዜጎችን በፍርሃት ድባብ ውስጥ ከትቶ በማሸማቀቅ፣ ለእስርና እንግልት በመዳረግ ጉዳቱ በግልፅ ይታያል፡፡
ለአብነትም በነ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ክስ ላይ ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት “አኬልዳማ “በሚል ዘጋቢ ፊልም የ1984/85 ዓ.ም. ኢህአዴግና ኦነግ ሀገሪቱን በጋራ ሲያስተዳድሩ የተፈፀመን ወንጀል በወቅቱ ያልነበሩትን እነ አንዱዓለምን አያይዞ በማቅረቡ እና በቅርቡ ደግሞ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮቴዎች ጋር በማያያዝ “ጅሃዳዊ ሃረካት” በሚል የግብፅና የሌሎች መካከለኛ ምስራቅ ሀገሮችን ድርጊት በማሳየቱ የበለጠ መንግስት ተዓማኒነት እንዳያገኝ አድርጎታል፡፡ እስካሁንም ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች( አንዱዓለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣…) ፤ ከጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት ዓለሙና የሱፍ ጌታቸው፣… ከኃይማኖት አባቶችና የኃይማኖት ነፃነት ይከበር ከሚሉት መካከል የዋልድባ ገዳም መነኮሳትና የሙስሊሙ ማኀበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች፣ ከዩኒቨርስቲ ተማሪና ወጣቶች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ሴና መረራ፣ ይገኙበታል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ የህገ መንግስት ጥሰት ነው፣ አዋጁ ሰለባ ያደረገውም ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና የኃይማኖት ነፃነት ጠያቂዎችን በመሆኑ ሊዘረዝ ይገባዋል ሲል ፒቲሽን እያስፈረመ ይገኛል፡፡ ከ4 ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ዙሪያ የኢህአዴግ፣ የመድረክ፣ የአንድነት/መድረክ፣ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ ተወካዮችን በቴሌቪዥን መስኮት አወያይቶ ነበር፡፡ ውይይቱ ይብዛም ይነስም የኢህአዴግን ዜጎችን አምታቶ ለመኖር ያለውን ምኞት በግልፅ ያሳየ ይመስላል፡፡ነገር ግን በአዋጁ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ለማካተት ቢሞከር ጥሩ ቢሆንም፤ አልተደረገም፡፡ አሁንም ቢሆን አዋጁ ዜጎችን በማፈን የኢህአዴግን ያለአግባብ ስልጣን ለማራዘም ካልሆነ እስካሁን ይሄ ነው የሚባል ጠቀሜታ ሊታይ አልቻለም፡፡