ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ማብዛት ምን ይፈይድላቸዋል?

 

ብስራት ወ/ሚካኤል

የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግብዓተ መሬት ከተፈፀመ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሀገሪቱን የስልጣን መሪ እየዘወሩ ይገኛሉ፡፡ ምንመ እንኳ በህግ ሙሉ ስልጣን የተሰጣቸው ቢሆንም በፓርቲያቸው ይሁን አሊያም በራሳቸው ፈቃድ የስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ እየሸረሸሩት የሚገኙ ይመስላል፡፡ ለዚህም መንበረ ስልጣናቸውን በይፋ ከተረከቡ በኋላ የብአዴኑን አቶ ደመቀ መኮንንን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሾመው አፀድቀዋል፡፡ በመቀጠልም በትናው የመንግስት መዋቅርና በየትኛው የህግ አግባብ እንደሆነ እስካሁን ባይታወቅም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በሚል የኦህዴዱን አቶ ሙክታር ከደርን የመልካም አስተዳደርና የሲቭል ሰርቪስ እንዲሁም የህወሓቱን ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የኢህአዴግ ዋነኞቹ አራቱ ድርጅቶች መካከል ከደቡብ ደኢህዴን ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከአማራው ብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ከኦሮሞው ኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙክታር ከድር እና ከህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የስልጣን መዘውሩን ይዘውታል፡፡ ይህ የሚያሳየው የስልጣን ቅርምቱ በኮታ እንደሆነ እና በመካከላቸው የስልጣን ሽኩቻ እንዳለ፤ አቶ ኃይለማርምም በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት የመወሰን አቅማቸው የመነመነ መሆኑን ነው፡፡ ሌሎች አጋር ተብለው የሚጠሩት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐረሪ፣ የቤኒሻንጉልና የጋምቤላ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ የድሬዳዋና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደሮች ከታች ሆነው ትዕዛዝ ለመቀበልና ለማስፈፀም ብቻ ዝግጁ እንዲሆኑ በተጠንቀቅ ላይ ጠብቁ የተባሉ ይመስላሉ፡፡

አቶ መለስ በህይወት ባሉ ሰዓት ብቻቸውን የስልጣን ማማው ላይ ሲጋልቡ ከሚኒስትሮች በተጨማሪ በሚኒስትርነት ማዕረግ አማካሪዎች እና ዳይሬክተሮችን ሾመው ነበር፡፡ያኔ በሚኒስትርነት ማዕረግ አማካሪ አድርገው ከሾሟቸው መካከል ዶ/ር ፋሲል ናሆም ህግ፣ አቶ ንዋይ ገ/አብ የኢኮኖሚ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን የማኀበራዊ፣አቶ አርከበ እቁባይ የኢኮኖሚና ትራንስፎርሜሽን እና ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ሁሉን ነገር  በራሳቸው ፍላጎት እና አካሄድ ከመከወን በቀር ሰውየው ምክር ይቀበላሉ ተብሎ ባይታመንም፡፡

hail

በአሁን ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ አማካሪ አድርገው ከሾሟቸው መካከል አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና በአዲስ መልክ እንደተቋቋመ የሚነገርለት የፕላንና ኮሚሽን ሚኒስትር አቶ መኮንን ማንያዘዋል አዳዲሶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞዎቹ አቶ ፀጋዬ በርሄ(የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት አማካሪ)፣ አቶ አባይ ፀሐዬ (የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ)፣ ዶ/ር ፋሲል ናሆም(የህግ ጉዳይ አማካሪ)፣፣ አቶ ንዋይ ገ/አብ(የኢኮኖሞ ጉዳይ አማካሪ)፣ አቶ አርከበ እቁባይ(የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አማካሪ)፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ(እስካሁን የስራ ድርሻቸው አይታወቅም፤ግን አማካሪ) በይፋ ተነስተዋል እስካልተባሉ ድረስ አሁንም አማካሪዎቻቸው ናቸው፡፡

ምንም እንኳ አቶ ሬድዋን ከአማካሪነት ተነስተው በአቶ በረከት ስምዖን ቦታ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ተደርገው ቢሾሙም አቶ በረከት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ተደርገው ተሸመዋል፡፡

በዚህም መሰረት አቶ ኃለማርም ደሳለኝ 3 ምክትሎች ጠቅላይ ሚኒስትሮችን እና 7 አማካሪዎችን በብዛት በመሾም ሪከርድ እየሰበሩ ይገኛሉ፡፡ አመራራቸውም በአቶ ኃይለማርያም በበላይነት ሳይሆን በቡድን እየተከናወነ መሆኑን አመላካች ነገሮች ይጠቁሟሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአማካሪዎቻቸው ብዛት ምናልባትም ከምክር ይልቅ ከፍርሃት ስነ ልቦና ጫና አሊያም ፓርቲው በብቃትና በአግባቡ ይመራሉ የሚል እምነት አጥቶባቸው በአስገዳጅ ሁኔታም ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ስለዚህ ከአቶ ኃይለማርም ፖለቲካ አስተላለፍ ለውጥ (political reformation) ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ስለሆነም እስካሁን ከቀድሞው ሟቹ  ጠቅላይ ሚኒስትር በአሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማየት አልተቻለም፤ በአንድ ጀምበር ለውጥ ይመጣል ተብሎ ባጠበቅም፡፡

በርግጥ የአማካሪ መኖርና ምክርንም በአግባቡ አመዛዝኖ የሚጠቅመውን ተቀብሎ ስራ ላይ ማዋል ጥሩ ቢሆንም ከብዛታቸው አንፃር በስነ ልቦና አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ግን አያጠያይቅም፡፡ በተለይ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ካሉባት በርካታ ውስብስብ ችግሮች አንፃር የፖለቲካ አስተላለፍ ለውጥን ጨምሮ የፖሊስ አሊያም የስርዓት ለውጥ ካልመጣ በአማካሪ ብዛት ብቻ ወደ ተሸለ ደረጃ መሄድ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ ፖለቲካ፣ የመኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤው ስርዓቱ በመሆኑ፡፡

ምናልባት አቶ ኃይለማርያም ችግሮችን ለመቅረፍ የማኀበራዊና ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለውጥ ላድርግ ቢሉ በኢህአዴግ አሰራር የፓርቲው የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የውሳኔ ሰጭው የበላይ አካል የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢህዴግም ሆነ መሪው አቶ ኃይለማርያም እንደማያደርጉት አስቀድመው ስለተናገሩ ከፓርቲው መፍረክረክ በስተቀር አሁን ባለው ሂደት የባሰ ካልሆነ የተሻለ ለውጥ ሊኖር አይችልም፡፡

ከዶ/ር ፋሲል ናሆም በስተቀር አማካሪዎቻቸውም ሆኑ ምክትሎቻቸው ከሙያ ብቃትና ልምድ ይልቅ በፖለቲካ ወገንተኝነት የተሰበሰቡ አጀቦች በመሆናቸው ይሄ ነው ሚባል የተለየ መልካም ነገር እንዳይጠበቅ ከማድረጋቸው በተጨማሪ በሀገሪቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ከአንድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ወንዝ የተቀዱ ናቸውና፡፡ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለ ደግሞ የራሱ የኢህአዴግ አባላት (ተገደው ለስራ ቅጥርና ለማዳበሪያ አባል የሆኑትን ሳይጨምር) የሀገሪቱን ነባራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በማጤን የመሻሻያ ለውጥ እንዲደረግ ደፍረው መጠየቅ ከቻሉ የበላይ አመራሮቹ እንዲነቁ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ አመራሮቹ በተናጥል ከኢህአዴግ አባልነት እራሳቸውን እያገለሉ አሊያም ለበላዮቹ ፍፁም ተገዥ በመሆን እንዲቀጥሉ ቢፈቅዱ “ከኑግ ያለህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” አይነት ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

 

ስለዚህ አሁን ያለውን የአቶ ኃይለማርያምን አስተዳደር ወደ ተሸለና ቀና ጎዳና ለመውሰድ የኢህአዴግ የፖለቲካ ለውጥ (political reformation) ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የህዝቡ የነቃ ተሳትፎ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢህአዴግ በሟቹ አቶ መለስ ጥላና መንፈስ ካልሆነ በስተቀር አይቻልም የተባለ ይመስል አመራሮቹ ተረጋግተው ለመምራት የተዘጋጁ አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውሳኔ በሚቸገሩበት ሁኔታ ምክትልና አማካሪ ማብዛታቸው የስነ ልቦና ጫና ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡ እስካሁን ከሚታየው ሁኔታ እንኳ ተነስተን የነገውን ካሰብን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትሎች፣ አማካሪዎችን በሚኒስትርነት ማዕረግ ሹመት በእስካሁኑ የሚያበቃ አይመስልም፡፡

የሹመት አሰጣጣቸውም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እና የመሪነትም ሆነ የሚያ ብቃትን መሰረት ከማድረግ ይልቅ አንችም እንዳይከፋሽ፣ከጠበሉ ቅመሽ ይይነት ነገር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ነገ ከራሳቸው ከኢህአዴግ አልፎ በሀገሪቱ ላይ የሚያመጣው መዘዝ ቀላል ነው አይባልም፡፡ ምክንያቱም መሪ ስልጣንን ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም አስቀድሞ ግላዊና ቡድናዊ አስተሳሰብ ውስጥ ከተዘፈቀ ቀጣዩ ሂደት የስልጣን ሹክቻ ይሆናልና፣ ቢረጋጉ ሳይሻል አይቀርም፡፡

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: