-ምትክ ቤት እንዲሰጣቸው የጠየቁ 12 የኮሚቴ አባላትም መታሰራቸው ተጠቁሟል
በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ ሃዲስ ሰፈር በሚባለው አካባቢ ይገነባል በሚባለው ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ከታህሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በመፍረስ ላይ ከሚገኙት 534 ቤቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች አባሎቹ መሆኑን መኢአድ እንዳስታወቀ ኢትዮ ምህዳር ባሬ እትሙ ዘግቧል፡፡
የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ የኢዮብዘር ዘሪሁን ለኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ እንደገለፁት ፤ነዋሪዎቹ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በካርታ ላይ የሰፈረ ፕላን ያላቸው ሲሆን የከተማ ቦታ ሊዝ ስርዓቱ ሲታወጅም የክፍለ ከተማው እና የወረዳው አመራሮች፤ነዋሪዎቹ ከቦታው ላይ ሲነሱ ምትክ እንደሚሰጣቸው የገቡትን ቃል በማጠፍ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲፈናቀሉ መደረጉ አግባብነት የለውም ማለታቸውን ጋዜጣው ለንባብ አብቅቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የወረዳው አስተዳደሮች ነዋሪዎቹ ያላቸውን ህጋዊነት ወደ ጎን በመተው መሬትን በመውረር ህገ ወጥ ቤት ገንብተዋል የሚል ምላሽ መስጠቱም ተጠቁሟል፡፡
የተፈናቃዮችን ቅሬታ ለከተማው ከንቲባ እና ለሚመለከተው አካል ለማድረስ 12 አባላት ያቀፈው ኮሚቴ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ቢታሰሩም፤ እስካሁን ህጋዊ የዋስ መብታቸው አለመጠበቁን እና ከቤተሰቦቻቸውም ጋር እንዳይገናኙ መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ዋቢ አድርጎ ጋዜጣው ጨምሮ ገልፅዋል፡፡