በአዲስ የሙዚቃ ስልት “ሸማመተው” በሚል የሙዚቃ አልበሟ ከህዝብ የተዋወቀችው ድምፃዊት ሚኪያ በኋሉ ባደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ ትናንት ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌሊት 36 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡ ድምፃዊቷ ወደ ሙዚቃው ኢንዱስትሪ ከመምጣቷ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ስነ ፅሑፍ” በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቃ በስኩል ኦፍ ቱሞሮ እና በአዲስ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግላለች፡፡
ድምፃዊቷ ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው “ኮራ” የአፍሪካ ሙዚቃ ውድድር ላይ ደለለኝ ደለለኝ በሚል ዘፈኗ ተወዳድሯ ምርጥ ስድስት ውስጥ ገብታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ትናንት በሞት እስክትለይ ድረስም “በዶመስቲክ ካልቸር” ጥናት የማስተርስ ትምህርቷን የመመረቂያ ፅሑፍ እየሰራች እንደነበርም ታውቋል፡፡
የድምፃዊቷ የቀብር ስነስርዓትም ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ቤተሰቦቿ፣ ወዳጅ ዘመድ እና አድናቂዎቿ በተገኙበት በለቡ ቅዱስ ገብርኤል የቀብር ስነስርዓቷ ተፈፅሟል፡፡ ሚካያ በኃይሉ የአንዲት ሴት ልጅ እናት ነበረች፡፡ አዲስ ሚዲያም ለሚኪያ የነፍስ እረፍትን፤ለወዳጅ ቤተሰቦቿ እና አድናቂዎቿ መፅናናት ይመኛል፡፡