በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የጋዜጠኞች ማኀበር ዛሬ በይፋ ተመሰረተ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አዲሱ “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” የተሰኘው የሙያ ማኀበር ዛሬ ጥር 22 ቀን 2006 ዓ.ም. በይፋ ተመሰረተ፡፡ ማኀበሩ አስታራ ሆቴል ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ የበጎ አድራጎትና ማኀበራት ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ኤምባሲን ጨምሮ የተለያዩ ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበ መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ አመራሮችንም መምረጡ ታውቋል፡፡ የማኀበሩ መመስረት ዋነኛ ዓላማም የጋዜጠኞችን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ የጋዜጠኞችን አቅም ማጎልበት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የህክምና እና የህግ አገልግሎት ድጋፍ መስጠት፣በጋዜጠኞች መካከል ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ማኀበሩን በተመለከተ ከጠቅላላ ጉባዔ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች የተንሸራሸሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ማኀበራት ሳይሆን የተሻለ በመስራት ለጋዜጠኞች መብትና ጥቅም መስራት እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡ ስለሆነም የማኀበሩን ዓላማ የመተዳደሪያ ደንቡ በሚያዘው መሰረት ለማስፈፀም ለጠቅላላ ጉባዔ ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ ሰብሳቢ፣ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ምክትል ሰብሳቢ እና ጋዜጠኛ ብሩክ ከበደ ፀሐፊ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በስራ አስፈፃሚነት ደግሞ ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ ፕሬዘዳንት፣ ስለሺ ሀጎስ ምክትል ፕሬዘዳንት፣ ዘሪሁን ሙሉጌታ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ነብዩ ኃይሉ ፀሐፊ፣ ሀብታሙ ስዩም (የገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም ታናሽ ወንድም) ገንዘብ ያዥ፣ ብስራት ወ/ሚካኤል የትምህርት እና ስልጠና ኃላፊ እንዲሁም ኤልያስ ገብሩ ሒሳብ ሹም በመሆን መመረጣቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ማኀበሩ ከላይ ከተጠቀሱት አመራሮች በተጨማሪ ጋዜጠኛ ብዙዓየሁ ወንድሙን የማኀበሩ ኦዲተር አድርጎ መምረጡም ታውቋል፡፡ ማኀበሩ የአባላት መደበኛ ወርሃዊ መዋጮን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ከመከረ ማኀበሩ በይፋ መመስረቱን ይፋ ማድረጉ ታውቋል፡፡ በአሁን ወቅት ለጋዜጠኞች መብት እና ጥቅም አልሰሩም ተብለው የሚወቀሱና በፌደራሉ የበጎ አድራጎትና ማኀበራት ኤጀንሲ ተመዝግበው የምስክር ወረቀት እንዳላቸው የሚነገርላቸው 5 ማኀበራት ቢኖሩም፤ እስካሁን በተግባር ለሙያውም ሆነ ለባለሙያው ያከናወኑት ተግባር የለም በሚል ከፍተኛ ወቀሳ እንደሚቀርብባቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲሱ የጋዜጠኞች ማኀበር ከሌሎች በተለይ በተግባር በርካታ ስራዎች ይሰራል ተብሎ በባለሙያዎቹ ብዙ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: