በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የኤልክትሪክ ገመድ ተበጥሶ የ13 ዓመት ልጅ ህይወት ማጥፋቱ ተገለፀ፡፡ አደጋው የደረሰው በጎፈር ሜዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ቦቢቾ በተባለ ቀበሌ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት ለረጅም ጊዜ ምሰሶው ሊወድቅ የደረሰ የኤሌክትሪክ ገመድ ተበጥሶ አንድ የ13 ዓመት ልጅ ከመኖሪያ ቤቱ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደ ሳለ በደረሰ አደጋ ወዲያው ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡
አዲስሚዲያ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት ከሆነ ምሰሶው በመንገድ ጥገና ቁፋሮ ምክንያት በመላላቱ የኤሌክትሪክ ገመዱ ረግቦ እንደነበርና ይህንንም በመፍራት በተደጋጋሚ ለከተማው መስተዳደርና በከተማው ለሚገኝ የመብራት ኃይል ዲስትሪክት ቅሬታ ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው አደጋው መድረሱን አስታውሰዋል፡፡ ከሟቹ ልጅ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ላደረሰው የቸልተኝነት አደጋ ምን ምላሽ እንዳለው ለማጣራት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወደ ሆኑት አቶ ምስክር ነጋሽ ደውለን ለማጣራት ብንሞክርም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡