በኢትዮጵያ በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ በርካታ የሰላማዊ ትግል ሙከራ ቢደረግም እስካሁን ለውጤት የበቃበት ጊዜ የለም፡፡ በአሁን ወቅት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ከጊዜውና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከኢትዮጵያ ጋር በማያያዝ እንዴት ለውጤት መብቃት ይቻላል በሚል ሰፊ ጥናቶችን ያካተተ “ሰላማዊ ትግል 101” መፅሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በግርማ ሞገስ ተፅፎ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሐፉ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ስልትን ተጠቅመው ህዝቡን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ እና ወደፊት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል ስልቶችንም አካትቶ መያዙ ተጠቁሟል፡፡
ደራሲው ነዋሪነታቸው በሰሜን አሜሪካ ሲሆን፤ መፅሐፉን ከማዘጋጀታቸው በፊት የኢትዮጵያን ቀደምት፣ መካከለኛ እና ዘመናዊ ታሪክ፣ በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውና ለውጤት የበቁ የተለያዩ የሰላማዊ ፖለቲካ ትግል ስልት ተሞክሮዎችን፣ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እና የገዥው ኢህአዴግን ባህሪ በማጥናት ዓመታትን የፈጀ መፅሐፍ መዘጋጀቱን ከደራሲው መረዳት ተችሏል፡፡ በተለይ በሀገሪቱ የተሻለ የመንግስት ስርዓት እንዲፈጠር የሚሹ እና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲመጣ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞችን ጨምሮ ማንኛውም ዜጋ ቢጠቀምባቸው ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ታምኖበታል፡፡ “ሰላማዊ ትግል 101“ መፅሐፍ ለአንባቢያን በ50 ብር የቀረበ ሲሆን፤ በመፅሐፍት መሸጫ መደብሮች እንደሚገኝምምንጮች ጠቁመዋል፡፡