የደቡብ ሱዳን ቀውስ በቀጠናው ላይ ያለው ተፅዕኖ

Bisrat Woldemichael
afrosonb@gmail.com

ሱዳን በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ካሉት ሰፊ ግዛቶች መካከል ቀዳሚዋ ነበረች፡፡ ሱዳን ለረጅም ጊዜ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የወደቀች ብትሆንም፤ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ግን የአረብ ሊግ አባል ሀገር ከመሆን በተጨማሪ በሼሪአ የእስልምና አስተምህሮ ህግ መተዳደር ጀመረች፡፡ ይሁን እንጂ በዜጎቿ መካከል እኩልነትንም ሆነ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ማምጣት ባለመቻሏ ከ30 ዓመታት በላይ ለከፍተኛ የእርስ በርስ ግጭት ተዳርጋ መቆየቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በተለይ ሱዳን የአረብ ሊግ አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ማስወጣት እና ወደብ ማሳጣት ከየመን በስተቀር የግብፅና እና የሌሎች አረብ ሀገሮች የረጅም ጊዜ ዕቅድ እንድታስፈፅም ትልቅ ተልዕኮ ተሰጥቷት ነበር፡፡ በዚህም ተልዕኮ የኤርትራውን ህግአኤ (ሻዕብያ) እና የዛሬው ህወሓት/ኢህአዴግን ዋና ቢሮ በመከፍትና በተለያዩ የገንዘብና ቁሳቁስ በመደገፍ ሀገሪቱ እርስ በርስ እንድትታመስ ትልቅ ስራ ሰርታለች፡፡

ሱዳን ኢትዮጵያን ለመጉዳት እየወሰደች ያለችውን እርምጃ እንድታቆም እና እንደ ጥሩ ጎረቤት ሀገር በሰላም ተባብሮ መኖሩ እንደሚያዋጣ በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ለሱዳን አመራሮች መልዕክት እና የቀጥታ ውይይት ተደረገ፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳን ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ግብፅ እና ሌሎች የአረብ ሀገሮች የሰጧትን ተልዕኮ በመደገፍ አጠናክራ ቀጠለችበት፡፡ በዚህም መንግስቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪዎች ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ ለሱዳን ከመስጠት አልቦዘኑም፤ ሱዳን ግን ቀጠለችበት፡፡
በድርጊቱ የተበሳጩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ሌሎች አመራሮቻቸው ለሱዳን የሚሆን አፀፋ ለመመለስ ተግባራዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መውሰዱን የመጨረሻ አማራጭ አደረጉ፡፡ በዚህም በሱዳን ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት እና እራሳቸውን አረብ ነን የሚሉት የሰሜን ሱዳን ተወላጆች በተፈጥሮ ሃብት የበለፀጉ የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎችን መጨቆን እንደ ባህል መውሰዳቸው ለወቅቱ ኢትዮጵ መዎች እንደ አንድ የፖለቲካ ትርፍ ወሰዱት፡፡

sed በነዳጅና በሌሎች የተፈጥሮ ሃብት የበለፀጉት ደቡብ ሱዳኖች እንደ ሰሜኑ ሱዳን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም በራሳቸው ሰሜን ሱዳኖች የባሰ ባርነት ውስጥ መውደቃቸውን አምርረው የሚቃወሙ በዶ/ር ጆን ጋራንግ የሚመራ ጥቂት የደቡብ ሱዳን ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ የግብዣ ጥሪ ተደረገላቸው፡፡ በዚህም ከወቅቱ የኢትዮጵያ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ልኡካኑ ከሰሜን ሱዳን በመለየት የመብቶቻቸውና የተፈጥሮ ሃብቶቻቸው ተጠቃሚ ለመሆን ትግል ማድረግ እንደሚፈልጉ አረጋገጡ፡፡ ኮሎኔል መንግስቱም ኢትዮጵያ ለየትኛው ጭቁን የአፍሪካም ሆነ የዓለም ህዝብ ኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የተለመደ በጎ ዓላማዋ ስለሆነ፤ እናንተንም አቅም በፈቀደ እንረዳችኋለን ሲሉ አረጋገጡላቸው፡፡

እነ ዶ/ር ጆን ጋራንግም ወዲያው ወደ ሱዳን እንደተመለሱ ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን ለመለየት በሚደረገው ትግል ለመሳተፍ ፈቃደኛ ለሆኑ ደቡብ ሱዳኖች በምስጢር ጥሪ አደረጉ፡፡ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ወዲያውኑ ከ100 ሺህ በላይ ፈቃደኛ የደቡብ ሱዳን ወጣት እና ጎልማሳ ወንዶች ፈቃደኛነታቸውን አረጋገጡ፡፡ ያኔ የዛሬዋ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን የመለየቷ ጥንስስ እውን ሆነ፡፡ ከዚያም የደቡብ ሱዳን ንቅናቄን የሚመሩት ልኡካን በአዲስ መልክ አመራር እንዲመረት ከላደረጉ በኋላ የበላይ መሪ እንዲሆኑ ዶ/ር ጆን ጋራንግ ከሌሎች አመራሮች ጋር ተመርጠው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ወደ ትግሉ ለመግባት ፈቃደኛ እንደሆነ የተነገረላቸው 100 ሺህ ደቡብ ሱዳናውያንን ለማስታጠቅም ሆነ ለማሰማራት ምቹ ሁኔታም ሆነ የአቅርቦት ዝግጅት አልነበረም፡፡

ውጥናቸው እንዲሳካ የተለያዩ ሀገሮችን በተለይም ምዕራብ እና ምስራቅ አውሮፓ ሀገሮችን ከመማፀን ጎን ለጎን በቅድሚያ ቃል የገባችላቸው ኢትዮጵያን ተግባራዊ ድጋፍ ጠየቁ፤ ደቡብ ሱዳኖች፡፡ ኢትዮጵያም ለእሷ ሱዳንን ለመበቀል እና ጥሩ ወዳጅ የሆነች ጎረቤት ሀገርን ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሷን አሻራ ለማኖር የገባችውን ቃል በመጠበቅ ከ80 ሺህ የማያንሱ የደቡብ ሱዳን የትግል አባላት በተለያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስልጠና እና ሌላ ሙያዊ ድጋፍ ከነ አስተዳደራዊ ቢሮ ድጋፍ አደረገች፡፡ ይሄ ደግሞ ለደቡብ ሱዳኖች ያልተጠበቅ ትልቅ ስጦታ መሆኑን በማመን ለትግሉ ፈቃደኛ የሆኑት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል (ያኔ ኢሉባቦር እና ወለጋ በሚባለው ክፍለ ሀገር) በኩል ገብተው አስፈላጊው ድጋፍ ተደረገላቸው፡፡

ሱዳንም የራሷን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዲሉ፤ ኢትዮጵያ ለመጉዳት ብዙ ስትደክም ባልጠበቀችው ሁኔታ የደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች ተጠናክረው ሲቀጥሉ፤ ሌሎች እንደ ዳርፉር፣ ደቡብ ኮርዶፋ እና ብሉ ናይል በሚባሉ አካባቢዎች በርካታ ታጣቂዎች ትግል በማድረግ ሱዳንን ቁም ስቅል አሳዩ፡፡ በዚህም ሱዳን ከስህተቷ ሳትማር ኢትዮጵኝ ለመገነጣጠል ለሚደክሙት ድጋፏን መስጠት ቀጠለች፡፡ ኢትዮጵያም አፀፋውን አጠናክራ ቀጠለች፡፡

በመጨረሻም የደቡብ ሱዳን የትግል መሪው ዶ/ር ጆን ጋራንግ በሱዳን በመሪዎች ቅንብር በአውሮፕላን ከሱዳን ወደ ኬንያ አቅጣጫ ሲጓዙ ቢገደሉም፤ ትግሉ ግን ለፍሬ በቅቶ ከ3 ዓመት በፊት ደቡብ ሱዳን የአፍሪካ እና የዓለማችን አዲስ ሀገር ሆና ብቅ አለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤታቸው ከመቁጠር በተጨማሪ አዲስ አበባ እና ምዕራብ ኢትዮጵያ የራሳቸው ያሁል በነፃነት ተንቀሳቅሰው ህልማቸውን እውን አደረጉ፡፡

ሱዳንም ኢትዮጵያን ከታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ የባህር በር በተጨማሪ ልጆቿ ኤርትራውያንን ከነ ምድሯ እንድታጣ ለሰራችው ነዳጅን ጨምሮ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገችውን ደቡብ ሱዳንን በማጣት የሰሜን በረሃን ይዛ ቀርታለች፡፡ በዱብ ሱዳኖች የተጀመረው የትጥቅ ትግል አሁንም ሳያበቃ ዳርፉር፣ ደቡብ ኮርዶፋ እና ብሉ ናይል የተሰኙ ግዛቶቿም ከደቡብ ሱዳን መገንጠል በኋላ አሁንም ከሱዳን ለመገንጠል እየታገሉ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ደቡብ ሱዳን ህልሟ እውን ሆኖ ራሷን የቻለች ሀገር ብትሆንም፤ የተመኘችውን ሰላም እና የተፈጥሮ ሃብቷ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስትደክም፤ የስልጣን ጥም እና ሙስና ባናወዛቸው መሪዎቿ ከ2 ዓመት በላይ ሰላም ልትሆን አልቻለችም፡፡
በአሁን ሰዓት ገና ነፃነቷን ከተጎናፀፈች 3 ዓመታት ያላለፋት ደቡብ ሱዳን በፕሬዘዳንቷ ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶ/ር ሬክ ማቻር መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎቿ ህይወት ሲያልፍ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተሰደዋል፡፡ በተለይ ሱዳን ነፃነቷ ባወጀች በአመቷ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር በመሪዎቿ ከሀገሪቱ ካዝና በሙስና መዘረፉን ተከትሎ ፕሬዘዳንቷ ሳልቫ ኪር ሌቦቹ አመራሮች የወሰዱት የሀገርና የህዝብ ገንዘብ በአስቸኳይ እንዲመልሱ ማስጠንቀቃቸው አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ የተመለሰው ከተወሰደው ረብ ያህል እንኳ እንዳልሆነ በመገንዘብ ሚኒስትሮቻቸውን እና ምክትላቸውን ሙሉ ከሙሉ ከስልጣን በማባረር የሚኒስትሮቹ ምክትሎች ለተወሰነ ጊዜ እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡

ከሙስናው መዘዝ በተጨማሪ የስልጣን መቀናቀን እና ውክልና በማየሉ በፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር እና በምክትላቸው ዶ/ር ሬክ ማቻር መካከል ሰፊ ቅራኔ በመፈጠሩ፤ የተወሰኑ የሬክ ማቻር ደጋፊዎች ታሰሩ፡፡ ይሄም በሀገሪቱ የበለጠ ውጥረት በመፍጠሩ አለመግባባት ከግልሰቦች ይልቅ ወደ አመራሮቹ ጎሳ አመራ፡፡ በዚህም ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር የወጡበት ዲንቃ ጎሳ እና ምክትላቸው ሬክ ማቻር የወጡበት ኑዌር ጎሳ መካከል ከፍተኛ የእርስ በርስ የጎሳ ግጭት ተከሰተ፡፡ በዚህም በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ቆስለዋል፣ ሀገር ጥለውም ተሰደዋል፡፡

እስካሁን በይፋ ባይታወቅም ውስጥ ውስጡን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በስልጣን ያለው ኢህአዴግ ከግጭቱ ጀርባ ለኑዌር ተወላጁ ምክትል ፕሬዘዳንት ለነበሩት ሬክ ማቻር በተናጠል ድጋፍ እንደሚያደርግ መነገሩ ደግሞ ለቀጠናው አለመረጋጋት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ በዚህም ፕሬዘዳንት ሳልቫ ኪር ሁለተኛ ቤታችን ከሚሏት ኢትዮጵያ ይልቅ ፊታቸውን ወደ ግብፅ በማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አመካኝነት ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር የመከላከያ ጦር ስምምነት መፈራረማቸው ለኢትዮጵያ ትልቅ ስጋት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በቋንቋ ዘር እና ጎሳ ከፋፍሎ የሚገዛው ኢህአዴግ ጎረቤት ሀገር ላይም ተመሳሳይ የተሳሳተ ‹ፖሊሲ መከተሉ ነገ ሀገሪቱን ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ተገምቷል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት የአባይ ወንዝን መገደቧ በግብፅ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞና ጥርጣሬ ፈጥሮ ሳለ፤ የጎረቤት ሀገሮችን ማስቀየም ለግብፅ ጥሩ የፖለቲካ መጫወቻ መድረክ ሊፈጥር እንደሚችል የሰጉ አልታጡም፡፡ በተለይ የኢትዮጵያው ኢህአዴግ ለደቡብ ሱዳኑ የኑዌር ተወላጅ ለሆኑት ሪክ ማቻር ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ የሚጠረጠረው፤ በሀገራችን ጋምቤላ በኑዌርና አኝዋክ መካከል ሆን ብሎ ግጭት በመፍጠር ሀገረ ውስጥ ኑዌሮች በአኝዋክ ጋምቤላዎች ላይ የበላይ እንዲሆኑ ማድረጉን በማውሳት የበለጠ ጥርጣሬው እንዲታመን አስችሎታል፡፡ በሌላ በኩል የለም! ኢህአዴግ ድጋፍ እያደረገ ያለው ለፕሬዘዳንቱ ጄነራል ሳልቫ ኪር ነው የሚሉም አልታጡም፤ ምንም እንኳ ጥርጣሬዎች በገሃድ የታዩ አሳማኝ እርምጃዎችን ዋቢ ያደረጉ ናቸው ባይባልም፡፡

sudaበቅርቡ በሳልቫ ኪር እና በሬክ ማቻር መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑ ደግሞ ጥርጣሬው በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረጉ አልቀረም፡፡ በዚህም ግጭቱ እንዲበርድ እና መፍትሄ እንዲያገኝ ሁለቱም ተቀናቃኞች በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈራረሙም ወዲያው ተግባራዊ አላደረጉም ነበር፡፡ በተለይ የአማፂዓኑ መሪ ዶ/ር ሪክ ማቻር እና ሳልቫ ኪር ስምምነቱን ጨርሰው ወዲያው ሀገራቸው እንደገቡ፤ ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አስፈራርተውኝ ነው የሚል መግለጫ ለአንድ የኬንያ ሚዲያ ሰጥተዋል መባሉ፤ግጭቱ በዘላቂነት ሊበርድ እንደማይችል አመላካች ነው፡፡

በአሁን ወቅት በምስራቅ አፍሪካ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የደቡብ ሱዳን ግጭት የሚቀጥል ከሆነ በተለይ ለኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ተፅዕኖው ግብፅ እና የኢህአዴግም ሆነ የኢትዮጵያ ተቀናቃኞች አጋጣሚውን በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት ሊፈጠር እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ በስልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ የደቡብ ሱዳን ግጭት እንዲበርድ ለየትኛውም አካል መወገን እንደሌለበት እና ሁለቱም ተቀናቃኞች በመተማመን ላይ የተመሰረተና ተግባራዊ መሆን የሚችል የሰላም ስምምነት በመፈራረም ለቀጠናው ሰላም የበኩላቸው ሊወጡ እንደሚገባ ይመከራል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ምስራቅ አፍሪካ በሶማሊያ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ካሉት የእርስ በርስ ግጭቶች በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን መጨመር በቀጣይ ለአህጉሪቱ አፍሪካም ሆነ ለቀጠናው ሀገሮች ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማኀበራዊና አካባቢያዊ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: