የነፃነት ትግል እና ሽብርተኝነት በኢትዮጵያ

ብስራት ወልደሚካኤል

afrosonb@gmail.com

የሽብር ትርጉም እና ድርጊት እጅግ ሰፊና እንደየሀገሮቹ መንግስታት ተጨባጭ ሁኔታና ስርዓት እንዲሁም ፍላጎት ይለያያል፡፡ በርግጥ የሽብር ተግባር መቼም በማንም ይፈፀም የሚወገዝና ትክክል ያልሆነ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አምባገነን ስርዓት ያለባቸው ሀገሮች ገዥዎች የስልጣን ዘመናቸውን ዜጎችን በማሸማቀቅ ለማስቀጠል ሲሉ የነፃነት ታጋዮችን አሸባሪ ብለው እንደሚጠሩ፤ በኋላም የነፃነት ታጋይ መሆናቸው የተመሰከረላቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ለዚህም በደቡብ አፍሪካ ዘረኛውን የአፓርታይድ የግፍ አገዛዝ በመቃወም በይፋ ለህዝቡ ነፃነት ይታገሉ የነበሩት እንደ ኔልሰን ማንዴላ ያሉ መሪዎች እና ሌሎች የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ አባላት በጊዜው በነበረው አገዛዝና እንደነ አሜሪካ ያሉ ዘረኝነት የነገሰባቸው ምዕራባውያን ሀገሮች ጭምር አሸባሪ ተብለው ተፈርጀው ነበር፡፡

መሪው ኔልሰን ማንዴላን ጨምሮ ሌሎች አጋሮቻቸው ከ27 ዓመታት እጅግ ቀዝቃዛ ከሆነው አሰቃቂ የሮበን ደሴት እስር በኋላ በደቡብ አፍሪካውያን እና በዓለም አቀፍ የነፃነት ደጋፊዎች ጫና ከእስር ተለቀዋል፡፡ የዓለም የነፃነት አባት ከመባል አልፈው እስካሁን ባለው የዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የትግሉ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ ሲሞቱ እስከዛሬም ድረስ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በርካታ የዓለም አቀፍ መሪዎች በስፍራው በመገኘት ሀዘናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለማንም የሰው ልጅ ያልተደረገ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተከታተለው ከፍተኛ አድናቆትና ሀዘኑን መግለፁ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በአንፃሩ የተለያዩ አምባገነን መሪዎች ሲሞቱ አብሮ ያልሞተው የገዥው ስርዓት ህዝቡን በግድ ልቅሶ እንዲወጣ ከፍ ሲልም የሙት ዓመት ልደቱን በአዞ እንባ ሙሾ እንዲያዝን ቢያደርግም፤ አብዛኛው ህዝብ ግን ከላዩ ላይ አንድ ትልቅ በሽታና ሸክም ከጫንቃው ላይ እንደወረደለት ያሰቡም አልታጡም፡፡

ራሳቸውን የነፃነት ታጋይ የሚያደርጉ በተለይ በኢትዮጵያ “የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” በ2001 ዓ.ም. በአሸባሪነት የተፈረጁት አምስት ታጣቂ ቡድኖች ሲሆኑ፤3ቱ ከኢትዮጵያ፣ 2 ቱ ደግሞ ከውጭ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነኚህም ዋና መቀመጫቸውን መካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገራት ያደረገው አልቃይዳ እና የሶማሊያው ታጣቂ አል-ሻዕባብ ከውጭ አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ታጣቂ አማፂያን መካከል ደግሞ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ)፣ግንቦት 7 ለዴሞክራሲና ለነፃነት ንቅናቄ (ግንቦት 7) እና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ይገኙበታል፡፡ ይሁን እንጂ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት ተግባርን በመቃወም የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉት በርካታ አመፂያን ሲሆኑ፤ እነኚህም ከሐረሪ ክልል፣ ከድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በስተቀር በሁሉም ክልሎች ታጣቂዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡

ከኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጋር እየተዋጉ እንዳለና ሊዋጉ “ኸረ ጥረኝ ጫካው፣ ኸረ ጥራኝ ዱሩ” ብለው የሚታገሉትና እስካሁን በአሸባሪነት ያልተፈረጁት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(አርዱፍ)፣የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር (አርበኞች ግንባር)፣የሲዳማ አርነት ግንባር (ሲአግ)፣የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጭ ድርጅት፣የጋምቤላ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር፣የቤኒሻንጉል ነፃ አውጭ ድርጅት እንዳሉ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲገለፁ ይስተዋላል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን ላይ ያለውና በትጥቅ ትግል በሌሎች የውጭ ኃይሎች ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጣው ህወሓት/ኢህአዴግም ያኔ ታጣቂ አማፂ እንጂ ሰላማዊ የዴሞክራሲ ታጋይ ድርጅት አልነበረም፡፡ ያኔ ቀዳሚ ዓላማውም ቢሆንም የትግራይን ህዝብ ከእናት ሀገሩ መገንጠል ለዚሁም ኤርትራ እንድትገነጥል ድጋፍ ማድረግ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራ እንድትገነጠል ማድረጉ ቢሳካም፤ የትግራይን ህዝብ ለመገንጠል በተደጋጋሚ የተደረገው ሙከራ ግን በትግራይ ህዝብ በተለይም በአዛውንቶቹ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስነሳቱ ዓላማው ከመሪዎቹና ጠንሳሾች ህሊና ባይጠፋም ቀስ በቀስ መክሰሙ ይነገራል፡፡ ዓላማውን ለማሳካትም በርካታ ኢ-ሰብዓዊ የሆኑ የሽብር ተግባራትን መፈፀሙም ዛሬም ድረስ በዓለም አቀፉ የሽብርተኝነት መረጃ ድርጊቱ ከነ ጊዜው ተቀምጧል፡፡

በተለይ አሁን በስልጣን ላይ ያለውና የኢህአዴግ አስኳል በመሆን ሀገሪቱን እየመራ እንዳለ የሚታወቀው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ያኔ ከደርግ መራሹና ከኢሕዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጋር በሰሜን የሀገሪቱ በረሃ መሽጎ ሲፋለም በዓለም አቀፉ የሽብርተኝነት መረጃ ቋት(Global Terrorism Database/GTD) በአሸባሪነት ተመዝግቦ ነበር፡፡ በወቀቱ በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊና ግብር አበሮቻቸው ሚመራው ታጣቂ አማፂ ቡድን “ህወሓት” ከሚፋለመው ከቀድሞው የኢትዮጵያ መካላከያ ሰራዊት በተጨማሪ በርካታ ንፁሃን እንደገደለ፣ እንዳቆሰለ፣ንብረት እንዳወደመ ዛሬም ድረስ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ ለዚህም ህወሓት በአሜሪካ መንግስት በአሸባሪነት ጥቂር መዝገብ ዝርዝር ውስጥ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬም ያ ስሙ ከመረጃ ቋቱ ውስጥ ከፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት ጋር ለአስረጅነት ቀርቧል፡፡

meles tplfህወሓት የሽብር ተግባሮች ፈፅሟል ተብሎ ከተመዘገበበት መካከል እ.አ.አ. ነሐሴ 2 ቀን 1990 ዓ.ም. በራያ ቆቦ 17 የኃይማኖት ተፅዕኖ ፈጣሪ አባቶችን በመግደልና ተቋማትን ማውደሙ፣እ.አ.አ. ጥቅምት 19 ቀን 1984 ዓ.ም. በላሊበላ 200 ንፁሃን ዜጎችን እንደገደለና 200 ያህል አቁስሎ ንብረት እንዳወደመ፣እ.አ.አ.የካቲት 18 ቀን 1988 ዓ.ም. በትግራይ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ንፁሃን ላይ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ አደጋ እንዳደረሰ ተጠቅሷል፡፡ ሌላው እ.አ.አ. በሚያዝያ 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በትግራይ ኮረም እና እ.አ.አ. ነሐሴ 3 ቀን 1983 ዓ.ም. በጃሪ የሞቱትና የቆሰሉት ቁጥራቸው በግልፅ ባይታወቅም ለትርፍ ያልተቋቋሙና ግብረሰናይ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ጥቃት ማድረሱ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

ለናሙና የተጠቀሱና ከላይ ተፈፀሙ የተባሉት አሰቃቂ የሽብር ተግባራት በህወሓት/ኢህአዴግ ስለመፈፀማቸው በይፋ ሲቀመጥ፤ ገዥው ስርዓት ግን እስካሁን በአደባባይ ተቃውሞም ሆነ ይቅርታ ያቀረበበት መረጃ የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ድርጊቱን አምኖ መቀበሉና እስካሁንም ትክክል ነው ብሎ እንደሚያምን ያሳያል፡፡ ስለሆነም ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ሌሎች አማፂዓንን አሸባሪ ብሎ መፈረጁና ሌሎች የመብት ጠያቂ ኢትዮጵያውያንን አብሮ የመፈረጅ የሞራል ጥያቄን ማስነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድም ሆነ በትጥቅ ኃይል ለነፃነት በሚል የሚታገሉ እንደ ወንጀለኛ የሚታዩ ከሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ በወንጀል ተከሶ ሒሳቡን ማወራረድና ተገቢውን ቅጣት አግኝቶ አርዓያ መሆን ያለበት በትጥቅ ትግል ወደ ሀገሪቱ መንበረ ስልጣን የመጣው ኢህአዴግ ነበር፤ ግን አልሆነም፡፡ አለበለዚያ መብትን መጠየቅና የነፃነት ትግል ማድረግ ለሌሎቹ ወንጀልና ስህተት ሆኖ ለኢህአዴግ ትክክልና ቅዱስ ተደርጎ ከበሮ የሚደለቅበት አግባብ ሚዛን ሊደፋ አይችልም፡፡

አሁን በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ በደርግ “ገንጣይና አስገንጣይ ወንበዴ” በሚል ቀለል ያለ ስያሜ ሲሰጠው፤ በምዕራባውያን በተለይም በዓለም አቀፉ የሽብርተኝነት መረጃ ቋት አሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ ከመስፈር ያገደው አልነበረም፡፡ አንባቢው ከላይ የተጠቀሰውን ለማረጋገጥ  www.globalterrorismdatabase.org/TPLF (Tigray Peoples Libration Front) በሚል ህወሓት/ኢህአዴግ አሸባሪ እንደነበርና አሁንም ስሙ እንዳልተሰረዘ የበለጠ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ኢትዮጵያ እየተመራች ያለችው በአሸባሪ ቡድን ነውን የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡

ሌላው በሽብርተኝነት የተፈረጁ ድርጅቶችስ በአሰቃቂ ድርጊትና ገደል ኑሮዓቸውን ገፍተው እንዲፋለሙ ያስገደዳቸው ምክንያት በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ካልሆነ መቼም ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው አካል ከተሻለ ኑሮ የሰቀቀን የቀበሮ የዱር ገደል ኖሮን የሚመርጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ በየትኛውም የዓለም ሀገሮች ታሪክ እንደሚያስረዳው በሀገሮች ላይ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ከገዥ ስርዓት ጋር የሚፋለሙት ዋና ምክንያት ገዥዎች በፖለቲካ ኃይሎች ላይም ሆነ በህዝቡ ላይ የሚፈፀሙ ኢ-ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ተግባራት መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህም ያኔ የአመፅ የትጥቅ ትግል ይደረግባቸው የነበሩት ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ጋና፤ ከላቲን አሜሪካ ብራዚልና አርጀንቲና፤ከሰሜን አሜሪካ ኩባና ራሷ ተባበሩት አሜሪካ፤ከአውሮፓ አየርላንድ፤ከእስያ ህንድን ብንጠቅስ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እና የዜጎቻቸውን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በገዥዎችም ሆነ በህብረተሰቡ በተግባር የተረጋገጠባቸው ሀገሮች በመሆናቸው ስለ ትጥቅ ትግል አይወራም፤የለም፡፡

በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ገዥዎች በዜጎች ላይ እየተፈፀሙ ያሉት አሰቃቂ ድርጊቶች ዛሬም አለመቆማቸው ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ኢህአዴግ አሸባሪ ብሎ የጠራቸው ድርጅቶች ህወሓት/ኢህአዴግ በጫካ እያለ ከፈፀመው ተግባር ጋር ልዩነቱን እና አንድነቱን ህዝብ እንዲያውቅ ነፃ መድረክ አላመቻቸም፡፡ በዚህም አሸባሪ ብሎ የሰየማቸው የኢትዮጵያውያን ታጣቂዎች፤ ሽብርን በእጅጉ በሚኮንኑና በሚዋጉ ሀገሮች ቢሯቸውን መክፈታቸው እውን ኢህአዴግ እንዳለው አሸባሪ ናቸው? ወይስ የነፃነት ታጋይ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን በስልጣን ላይ ያለው አካል ከዚህ ቀደም በጫካ እያለ ከሚፈፅመውና በዓለም አቀፍ ደረጃ አሸባሪ ከተባሉ አማፂዓን ያልተለየ እና ያልተናነሰ ተግባር በአዲስ አበባ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል “ማዕከላዊ” እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እንደተፈፀሙ፣ እየተፈፀሙ እንዳሉ ይነገራል፡፡

Ter picከላይ የተጠቀሰውን ድርጊት ስንመለከት ህወሓት/ኢህአዴግ እውን የነፃነት ታጋይ ነበርን? ብለን መልሱን አዎን ካልን፤ በአሁን ሰዓት የሰላማዊ ትግል በር በመዘጋቱ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የታጠቁ ኃይሎችን እንዴት አሸባሪ እንበላቸው? ታጣቂዎቹን አሸባሪ የምንላቸው ከሆነስ፤ለዚህ ተግባር ግፊት በማድረግ በቀዳሚነት ተባባሪ የሆነው ራሱ ገዥው ስርዓት እጁ የለበትምን? ምላሹን ለራሱ ለኢህአዴግ አባላትና አመራሮች እንዲሁም ለህዝብ መተው ነው፡፡ ሌላው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እጅግ በጠበበው መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን መሪዎች በተለይም ወጣቶችን በሽብር እየወነጀሉ ማሰሩስ ሽብርተኝነትን ትርጉም አልባ አያደርገውም ወይ? የሚለውንም መልሱን ለአንባቢው እተዋለሁ፡፡ በተለይ የሀገሪቱ ዜጎች የሆኑ በርካታ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮችስ እስካሁን በተፈረደባቸውም ይሁን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ተጠርጣሪዎችን አሸባሪ ብሎ መፈረጅ በፍትህ ስርዓትና በአሰቃቂ የሽብርተኝነት ድርጊት ላይ መቀለድ ይመስላል፡፡ ስለዚህ የነፃነት ትግልና ጋዜጠኝነት ከሽብርተኝነት ጋር ምንም ቁርኝትም ሆነ ግንኙት ስለሌላቸው ተለይተው መታየት አለባቸው፡፡ ለገዥዎች በስልጣን ለመቆየት አስጊ ተደርገው የተገመቱ ተዋናዮች እና ድርጊቶች የሀገሪቱና የዜጎች ስጋት ተደርገው ሊወሰዱ አይገባም፡፡

በአንፃሩ በሽብርተኝነት የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የተፈረደባቸው ግለሰቦች ፍላጎታቸው፣ ዓላማቸውና ግባቸውን ህዝቡ እውነታውን ያለማንም ጣልቃ ገብነትና ቅንብር ተረድቶ ፍርዱን እንዲሰጥ ነፃና ገለልተኛ መድረክ መኖር ነበረበት፡፡ አለበለዚያ የገዥ ቡድኖችን ፍላጎትና ፍርሃት በማንፀባረቅ ዜጎችን አሸባሪ ማለቱ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ከ1928-1935 ዓ.ም. ድረስ በፋሽቱ ጣሊያን ወረራ ወቅት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ብሎም ለራሳቸው ነፃነት ሲታገሉ የነበሩ አርበኞች አሸባሪ ተብለው በወቅቱ በነበረው የጣሊያን ገዥ ስርዓት በተቋቋመው ነፃና ገለልተኛ ባልሆነው ፍርድ ቤት እንደነ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ያሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህ የነፃነት ታጋዮችን አሸባሪ የምንል ከሆነ የቀድሞ የሀገራችን አርበኞች እና ኔልሰን ማንዴላ ዛሬም ድረስ አሸባሪዎች ናቸው ልንል ነው፡፡ እነሱን እና አሁን በስልጣን ላይ ያለውን የኢህአዴግ አመራሮችን የነፃነት ታጋይ የምናደርግ ከሆነ ደግሞ፤ አሁን ለሀገራቸው፣ለህዝባቸውና ለራሳቸው ነፃነት የሚታገሉትን፣ ያመኑበትን እውነት በአደባባይ የሚናገሩ ዜጎችን ወንጀለኛ ማድረግ በየትኛውም አመክንዮ (Logic) ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት አይቻልም፡፡

tplf 2ሌላው ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ተቋም ወይም ፍርድ ቤት አለመኖር ደግሞ ገዥዎችንም ነገ ፍትህ ሊያሳጣ እንደሚችል ካለፈው የደርግ ስርዓት መማሩ ተገቢነት አለው፡፡ የግብፁ ፕሬዘዳንት የነበሩትና በህዝባዊ አመፅ ከስልጣን የተወገዱት ሆስኒ ሙባረክ በቻሉት መጠን ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤትና መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የፀጥታ ኃይል በመገንባታቸው በአስተዳደር ዘመናቸው በፈፀሙት ግፍ በክብር ታስረው ተገቢው ፍትህ ከማግኘት አላገዳቸውም፡፡ በአንፃሩ በዕድሜ ዘመናቸው ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት መገንባት ያልቻሉት የሊቢያው ሙዓሙር ጋዳፊ ግን ከክብር ቤተመንግስታቸው ወጥተው ለፍትህ እንኳ ሳይቀርቡ እንደ ጎዳና ውሻ ከተደበቁበት ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ አሰቃቂ ሞት የታደጋቸው ፖሊስ፣መከላከያ ሰራዊትም ሆነ የደህንነት ኃይል አልነበረም፡፡

በፍትህ መቀለድ መዘዙ ዛሬ ለስልጣኔ ያሰጋኛል ብለው የጠረጠሩትን ዜጋ ለማጥቃት ብቻ ሳይሆን ነገ ገዥዎች በድንገት ከስልጣን ሲወርዱ የሚጠብቃቸው ተመሳሳይ ከመሆን አያድንም፡፡ ስለዚህ ነፃና ገለልተኛ የፍትህ ስርዓት፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይል መገንባት ጠቀሜታው ነገ ለራስም ጭምር ከስልጣን ውጭ በህይወት ለመቆየት ትልቅ ዋስና ስለሚሆን ከወዲሁ መንቃቱ ብልህነት ነው፡፡ አለበለዚያ በቆፈሩት ጉድጓድ መቀበር አይቀርም የሚለው ተረት እንዲሰምር መስራት ዳፋው ለሁሉም መትረፉ ስለማይቀር ቢዘገይም ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ለሌላው ተብሎ የሚሰራው ክፉም ሆነ መልካም ነገ ለራስ መትረፉ አይቀርምና፡፡ ይህ ሁሉ እየተከናወነ ያለው የኢህአዴግ አስኳልና ዋነ ዘዋሪው ህወሓት ራሱ የመጣበት መንገድ በአሸባሪነት ስለሆነ ሁሉም እንደራሱ ስለሚመስለው ያንኑ ሽብር ተግባር በከተማም እየደገመው ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ ምናልባትም በቅርቡ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሌላው ዓለም በተለየ ህጋዊ ሽፋንን አስመስሎ የሚጠቀም አሸባሪ መንግስታዊ ቡድን መኖሩን ለኢትዮጵያውያን መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነው፡፡

ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል እንዲሉ፤ ኢህአዴግ በተለያየ የሀገሪቱ አካባቢ በተለይም በአዲስ አበባ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ምርጫ ውጤትን ተከትሎ፣ ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ ያለው የቀድሞ ትግራይ ሆቴል ላይ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጠገብ ታክሲ ውስጥ እና አዲስ አበባ ስታዲየም ላሊበላ አይቤክስ አካባቢ ራሱ የተለያዩ ቦንቦችን ማፈንዳቱን ከዊክሊክስና ከሀገሪቱ የደህንነት ምንጮችን መረጃ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው ለኢህአዴግ ነፃነት እንዲሁም የመብት ጥያቄን ማንሳት ወይንም የነፃነት ትግል ማለት ሽብር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንዲሉ መሆኑ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: