ዛሬ ሰኞ መስከርም 19 ቀን 2007 ዓ.ም. አሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተኩስ ተከፈተ፡፡ በዋሸንገተን ዲሲ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የፈፀመውን እና እየፈፀመ ያለውን ድርጊት የሚገልፅ ደብዳቤ እና ኮከብ የሊለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ይዘው ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ሲገቡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጥበቃ ኃላፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አቶ ሰለሞን ወዲ ወይኒ ሁለት ጥይት መተኮሳቸውን እና አንዱ ጥይት ከኤምባሲው ውጭ በሚገኝ አንድ ተሸከርካሪ መኪና ላይ ጉዳት ማድረሱ ተጠቁሟል፡፡
በኤምባሲው የጥበቃ ኃላፊ በግቢው የህወሓት ተወካይም ሆነው በኤምባሲው የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችንም በተጓዳኝ እንደሚቆጣጠሩ የተነገረላቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያኑ ተቃውሞ አቅራቢዎች ላይ በፈፀሙት ተኩስ አካባቢውን በመረበሻቸው የከተማው ፖሊስ ወደ ኤምባሲው ኢንተርናሽናል ድራይቭ የሚባለውን መንገድ ለተወሰነ ጊዜ የዘጋ ሲሆን ፤ በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ም አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉ የተለያጠዩ ዓለም አቀፍ የዜና ምንጮች ከአካባቢው ዘግበዋል፡፡ እንደሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ደግሞ ጥይት የተኮሱት አቶ ሰለሞን በአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተጠቅሷል፡፡
ወደ ኤምባሲው ገብተው የነበሩት ኢትዮጵያውያንም በአሁን ወቅት የኢህአዴግ መንግስት የሚጠቀምበትን ባለኮከብ ሰንደቅዓላማ በማውረድ የቀድሞውን ታሪካዊ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ለተወሰነ ጊዜ ሰቅለው ከግቢ እስኪወጡ ማውለብለባቸው በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ጠቁመዋል፡፡ የኤባሲው ባለሙሉ ስልጣን አምባሰደር ግርማ ብሩ ተኩስ የከፈቱትን ግለሰብ ለመደበቅ ሲሚክሩ የሚያሳይ የካሜራ ምስልም ታይቷል፡፡ ክስተቱንም ሮይተርስ፣ ፎክስ ኒውስና ኢሳትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስፍራው የዘገቡት ሲሆን፤ የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፅመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እስር፣ ግድያና እንግልት ተቃውሞ በተለያየ የአውሮፓና አሜሪካ ከተሞች በተከታታይ መከናወኑ የሚታወስ ነው፡፡