በቅርቡ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 4ኛ ዙር የሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሚውል 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሰጠው ብድር እስካሁን የገባበት አለመታወቁ ተሰማ፡፡ በተለይ የዓለም ባንክ ቦርድ ዋና ዳይሬክተሩ እ.አ.አ. መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የባንኩ ዓለም አቀፍ የልማት ማኀበር (IDA) ለኢትዮጵያ መንግስት ብድሩን መስጠቱን እና ሀገሪቱም በተፈቀደው ብድር ተጠቃሚ መሆኗን አረጋግጧል፡፡ ባንኩ ብድሩን የሰጠው 4ኛው ዙር የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ውጤታማ ለማድረግ በሚል ሲሆን፤ ይህም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ የሴፍቲኔትን ለማዳረስ፣ድርቅን ለመቋቋም የሚደረግ ስርዓትን ለማገዝ፣ የምግብ ዋስትና ላልተረጋገጠላቸው እና የገቢ መጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን በመግለፅ፤ ባንኩ በቅርቡ እ.አ.አ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በድህረ-ገፁ ላይ አስነብቧል፡፡
ባንኩ የሰጠውን ብድር አስመለክቶ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዧንግ ዠ ቺን ቀደም ሲል በሀገሪቱ ይተገበር የነበረው የሴፍቲ ኔት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፉን የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማገዝ ከሚደረገው ጥረት ውጭ የተራቆተ መሬትን መልሶ ማቋቋም አብሮ ተግባራዊ አለመደረጉን ገልፀዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አሁን የተሰጠው 600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 10 ሚሊዮን የሚሆኑ የገጠር ነዋሪዎችን ተደራሽ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የተራቆተ መሬትን መልሶ ለማቋቋምም ታሳቢ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ኃይለማርም ደሳለኝ ባለፈው ግንቦት 20 ቀን 2006 ዓ.ም. የኢህአዴግን 23ኛ ዓመት የድል በዓል አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን አረጋግጣለች ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ከ10 ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵውን የምግብ ዋስትና ችግር ስለገጠማቸው ራሱ የኢትዮጵያ መንግስት በጠየቀው መሰረት የዓለም ባንክ የምግብ ዋስትናን ችግር ለመቅረፍ እንዲያግዝ የ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር መሰጠቱን ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ገንዘብና ብድርን የሚመለከት ስምምነቶች በቀጥታ የሚመለከተው የገንዘብ፣ ኢኮኖሚና ልማት ሚኒስቴር የዓለም ባንክ የሰጠውን ብድር አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ ፤እንደማንኛውም ሰው ከሀገር ውስጥ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከመስማት ባለፈ የዓለም ባንክ ስለሰጠው የ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር መንግስት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መናገሩን ድሬ ቲዩብ አስነብቧል፡፡ ይህ እስከተዘገበ ድረስ ባለፈው ወር መስከረም መጨረሻ 2007 ዓ.ም. የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሰጠው 600 ሚሊዮን ዶላር ብድር እስካሁን ያለበት አልታወቅም፡፡