ከዛሬ 3 ሺህ ዓመታት በፊት የጠቢቡ ንጉስ ሰሎሞን ልጅ በሆነው ቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የሙሴ ፅላት መዘረፉን በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች እና መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ የርዕሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ማርያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ እና ማዕከላዊ አክሱም ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ንብረእድ አባ ገ/ህይወት ገ/ሚካኤል በበኩላቸው የተባለው ጉዳይ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለፖሊስም ሆነ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ለፓትርያርኩ ጽ/ቤት ይህን መሰሉን ሪፖርት አላቀረብንም ያሉት አስተዳዳሪው፤ ወሬው ከየት መጥቶ እንደተወራ አናውቅም ብለዋል፡፡
የአክሱም ጽዮን ማርያም ታቦት በቤተክርስቲያኒቱ ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ማንም ሊያየው በማይችለው እና በጥንቃቄ ቦታ እንደሚቀመጥም አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ አስተዳዳሪው ጉዳዩንም ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስልክ ደውለው እንደነገሯቸው ተናግረዋል፡፡
ጽላቱ በቤተክርስቲያኒቱ ጠባቂዎች እና በመንግስት የፖሊስ ሃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት ነው ያሉት አስተዳዳሪው ህዝቡ በቀጣይ የሚከበረውን አክሱም ጽዮን ክብረ በአልን በተረጋጋ መንፈስ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ምንጭ፡- ድሬ ቲዩብ