የሴቶች ጉዳይ ይመለከተናል የምትሉ ከወዴት ናችሁ? የእህታችን የሐና ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው!!

ብስራት ወልደሚካኤል

በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ አንዲት የ16 ዓመት ባለ ብዙ ተስፋዋ የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው  እህታችን ሐና ላላንጎ ለክፉ ድርጊታቸው ቃላት በማይገልፃቸው 5 ጨካኝ ወንዶች ከሰብዓዊነት በራቁ አረመኔ ወንዶች ያውም በቀን ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቷ በተሳፈረችበት ታክሲ ስትሄድ  ሾፌር፣ረዳትና ሌሎች ግብር አበሮቻቸው ታግታ ለቀናት በመፈራረቅ ተደፍራ ህይወቷ አልፏል፡፡ ዜናው እጅግ ዘግናኝ ከመሆኑ የተነሳ ለመግለፅ ያስቸግራል፡፡ የልጆቹን ድርጊት አንዳንዶቹ ከሌሎች የቤትና የዱር እንሰሳ ድርጊት ጋር ሊያይዙ ይሞክራሉ፡፡ እውነታው ግን የትኛውም እንሰሳ ምስያውን ያውም ተስፈኛ የስንት ታናሽ እህቱን፣ ልጁን ወይንም ወገኑን በጅምላ አግቶና አስገድዶ ደፍሮ የሚገል ፍጡር የለም፡፡

ሐና ላይ  አረመኔዎች የፈፀሙት ድርጊት በምንም የሚገለፅ አይደለም፡፡ እጅግ ልብን የሚናካና አሳዛኛ ተግባር ነው፡፡  የድርጊቱ ፈፃሚዎችም የማያዳግም እርምጃ ወይም ቅጣት  በአደባባይ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ያቺ ተስፈኛ ለግላጋ ወጣት በህይወት ኖራ የአረመኔዎችን ቅጣት በዓይኗ ለማየት ባትታደልም  ለሌሎች አረመኔዎች ማስተማሪያ እንዲሆን እና ሌሎች እህቶቻችንም ቀና ብለው በሀገራቸው በኩራትና በነፃነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ለሐና ተብሎ የሚሰጠው ፍትህ የሁሉም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

በርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ በሌለበት ፍትህ መጠየቅ ህልም ቢሆንም፤ እነኚህ የድርጊቱ ፈፃሚ አረመኔዎች ግን በምንም መልኩ ተገቢውን ለሰሩት አሰናዋሪ ጭካኔ ለተሞላበት ተግባር ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

እዚህ ላይ በጣም የገረመኝ  ጥያቄ የፈጠረብኝ ነገር አለ፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያ ያሉ የሲቪክ ተቋማት በተለይም የሰቶች ጉዳይ ቅንጅት፣ ማኀበራት፣ …የሚባሉ ተቋማት ባለፈው 2004 ዓ.ም. የበረራ አስተናጋጇ (ሆስተሷ) አበራሽ ኃይላይ ላይ በቀድሞ ባለቤቷ ተወሰደ በተባለው የበቀል እርምጃ የአካል መጉደል ደርሶባታል በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ከማድረግ በተጨማሪ በቅንጡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ተደጋጋሚ መግለጫ እስከመስጠት ደርሰው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለዚህም እኔው ራሴ ከዚህ ቀደም በምሰራበት ጋዜጣ ለጉዳዩ ከ2 ጊዜ ያላነሰ የዜና ሽፋን በመስጠት በመግለጫዎቹና ተቃውሞዎቹ ላይ ልክ እንደሌሎቹ የሙያ አጋሮች በተደረገ ጥሪ ተገኝቼ የታዘብኩት እውነታ ነበር፤ከሙያ በተጨማሪ በግሌም ጥቃቶችን የምቃም ነኝና፡፡ ያኔም ሆነ አሁን በካሚላት፣ በአበራሽ ላይም ሆነ በማንኛውም ሴትም ሆነ ወንድ ላይ በአጠቃላይ በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትን አጥብቄ የምቃወመው ተግባር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተማሪ ሐና ላይ በተፈፀመው አሰቃቂ ተግባር ያኔ ለነ አበራ ኃይላይ ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ዛሬ የት ሄደ? ለምን?

ሀሀሀእኔ እስከሚገባኝ ሐናም አበራሽም ሆነች ካሚላት ሁሉም ሴቶች፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሁሉም ወገኖቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ ሌሎች ተቋማትም ሆኑ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት ከሐና ጎን ሲቆሙ አላየሁም፤ ወይም አልተገነዘብኩም፤ ለምን? ሁሉም ላይ የሚፈፀም ጥቃት እኩል ድጋፍ ሊደረግ ይገባል፤ ቢቻል ያኔ መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን ሲጨቀጭቁ የነበሩ ይመለከተናል የሚሉ  የሴቶች ማኀበራትና ተቋማት ዛሬ ከወዴት ናችሁ? ማንኛውም ሴት ላይ የሚፈፀም ጥቃት በእኩል ትኩረት በመስጠት ከጎናቸው መሆናችንን ልናሳይ የሚገባ ይመሰለኛል፡፡

በርግጥ ይህን ስል ጉዳዩ ወንዶችን አይመለከትም ማለቴ አይደለም፤ በደንብ ይመለከተናል፡፡ ምክንያቱም ሰው በመሆናችን ብቻ ሴትም ሆነ ወንድ ላይ የሚፈፀም ጥቃት የሰው ልጅ ላይ በመሆኑ ይመለከተናል፡፡ ግዴታችንም ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ እስኪ ማነው እናቱን የሚጠላ? ማነው እህቱ ላይ ሌላ ሰው የዚህን ዓይነት አሰቃቂ ድርጊት እንዲፈፀም የሚፈቅድ? እስኪ ማነው ልጁ ላይ እንዲህ እንዲፈፀም የሚፈቅድና ቢፈፀም ደስተኛ የሚሆን? ማንም ያለ አይመስለኛም፤ሊኖርም አይገባም፡፡ ጉዳዩ የሁላችንም ነው የምላው ለዚህ ነው፡፡

በሀገሪቱ ተመሳሳይ ድርጊት ከእንግዲህ እንዳይፈፀም  ተገቢውን ፍትህ ከመስጠት በተጨማሪ ለሌሎች እህቶቻችን ቢያንስ ድርጊቱን እናወግዛለን ፣ ከጎናችሁ ነን፤ ተገቢው ፍትህ መሰጠት አለበት የሚሉ የተቃውሞ ድምፆች በጋራ በወድሞቻችን እና እህቶቻችን ሊዘጋጅ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አለበለዚያ ድርጊቱ ነገም ሊቀጥል ይችላል፡፡ አሁንም ይሄ የሐናም ሆነ የነ ካሚላትና አበራሽ ላይ የተፈፀሙ ድርጊቶች አዲስ አበባ በመሆናቸው ለአደባባይ በቁ እንጂ…በየ ክልል ከተሞችና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ከተጠቀሱት የሚልቅ ድርጊቶች እንደሚፈፀሙ ይታመናል፡፡ ይህ ሁሉ እንዲቀር ሴት ወንድ በሚል የፖለቲካ ፍጆታ መድረክ ከማድመቅ በዘለለ በእውነት ለሁሉም ልንደርስላቸው ይገባል፡፡

ንፁሃንን አሸባሪ እያለ በግፍ የሚያስረውና የሚያሰቃየው መንግስትስ የህፃናትና ተማሪዎችን ደህንነት ያውም በአዲስ አበባ እንዴት መታደግ አቃተው; ስንቱን የግለሰብ ምስጢር እየበረበረ የሚከታተል ደህንነትስና ፖሊስስ ንፁሃንን ከማደን ተላቆ ወንጀለኞችን በማደን እና ለፍርድ ከማቅረብ ረገደ እንዴት ነው?

ሐና…ፈጣሪ ነፍስሽን በገነት ያኖረው ዘንድ ተመኘሁ…

አሁንም…ፍትህ ለሐና ! ፍትህ ለሐና!!….ፍትህ ለሐና…!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: