ለብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አቀባበል ተደረገ፤ ፍቅረ ንዋይን በማሸነፍ ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ በመመካከር እንዲሠሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

  • ‹‹የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት የአገር ነው፤ ቤተ ክርስቲያንን ልናስቀድም ይገባል›› ፓትርያርኩ  
  • ‹‹ገንዘብን አሸንፉት፤ መቃብርን አትርሱት›› /ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ
  • ‹‹ሕዋሳት ድርሻ አላቸው፤ ሕዋሳቱ ካልታዘዙ ግን ችግር ይፈጠራል›› /አቡነ ቀሌምንጦስ
  • ‹‹ሀገረ ስብከቱን የሚያመሰቃቅለው አሉባልታና ሐሰት መወገዝ አለበት›› //ሥራ አስኪያጁ
  • ‹‹ያልምዶት እንጂ እንኳን ደስ ያለዎት አንልዎትም›› /አስተያየት ሰጭ የደብር አለቃ
  • ‹‹ንግግር ከማብዛት ይልቅ ወደፊት በየሥራችን ብንመዘን›› /ሌላው የደብር አለቃ

abune kelemintos

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የከምባታ ሐዲያ ጉራጌና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ

ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኃ ጥቅምት የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው፣ የከንባታ ሐዲያ ጉራጌና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ መድቧቸዋል፡፡ በምደባ ውሳኔው መሠረት ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሀገረ ስብከቱ የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነ መርሐ ግብር ለብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

 

‹‹የመጣነው ሥራቸውን በቡራኬ ለማስጀመር ነው፤ብፁዕነታቸው ደግ አባትና ጠንቃቃ መነኵሴ በመኾናቸው ይህን ከተማ ያስተካክሉታል ብለን እናምናለን፤ ኹላችኁም ትተባበሯቸዋላችኹ፤ ኹሉም መሪውን ይከተላልና፡፡››/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋራ ስምንት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከቱ እና የሰባቱም ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ከ160 በላይ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ጸሐፊዎች የተገኙበት ይኸው የአቀባበል መርሐ ግብር፣‹‹ለብፁዕነታቸው በተደራቢነት የተሰጠውን ሥራ በቡራኬ ለማስጀመር››የተዘጋጀ መኾኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ደግ አባትና ጠንቃቃ መነኵሴ መኾናቸው እንደሚታወቅ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ ‹‹ትልቅና ጥንቃቄ የሚፈልግ ከተማ›› ያሉትን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደሚያስተካክሉት እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሮች ሲፈጠሩ ከሐሜትና መነቃቀፍ ይልቅ ግራና ቀኝ አስፍቶ በማየት እየተወያዩ መሥራት ቅድስትና ልዕልት ለኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚበጅ ቅዱስነታቸው አመልክተው÷ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት የአገር ሓላፊነት በመኾኑ ከኹሉም በፊት ቤተ ክርስቲያንን ልናስቀድም ይገባል፤ የተሠየምነው ቅድስናዋንና ሕጓን ጠብቀን ለመኖር ነው፤›› በማለት አስገንዘበዋል፡፡ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የተቸገሩ የገጠር አብያተ ክርስቲያንን ለመርዳት ቅርበት እንዳላቸውና ሊኖራቸውም እንደሚገባ በመግለጽ ስለ አስተዋፅኦዋቸው አመስግነዋቸዋል፤ ‹‹አዲስ አበባ ሰላም ከኾነች ኹሉም ሰላም ይኾናል›› ያሉት አቡነ ማትያስ የአህጉረ ስብከት ኹሉ ማእከል በኾነው አዲስ አበባ ለሰላም፣ ለልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሊቀ ጳጳሱን በመደገፍና ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ በመመካከር መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል – ‹‹ኹላችኁም ትተባበሯቸዋላችኹ፤ ኹሉም መሪውን ይከተላልና፡፡››abune matiyas

‹ለኹለት ጌቶች መገዛት አይገባም፤ ገንዘብን ወድዳችኹ አይታችኁታል፤ እስኪ ደግሞ ንቃችኹ እዩት›› /የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/

ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳንና መመሪያ ቀደም ብሎ የመርሐ ግብሩን ትምህርት የሰጡት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ናቸው፡፡ አንድ ሰው ወይ ለእግዚአብሔር ወይ ለገንዘብ እንጂ ለኹለት ጌታ መገዛት እንደማይችል የጠቀሱት ብፁዕነታቸው÷ ገንዘብን ንቀው ለእግዚአብሔር የተገዙ አባቶች ግን ማትረፋቸውን በዋቢነት አስረድተዋል፡፡ እነቅዱስ እንጦንስን እነጻድቁ ገብረ ክርስቶስን ለምኑልን፤ አማልዱን ብለን የምንጸልየውም ገንዘብን ንቀው ለእግዚአብሔር ስለተገዙ ነው፡፡ ‹‹ገንዘብን አሸንፉት፤ መቃብርን አትርሱት፤ ሰው ገንዘብ ቆጥሮ ሥልጣንም አግኝቶ ትቶት ይሔዳልና፤››ሲሉም በአጽንዖት መክረዋል፡፡

የዓለም መናኸርያ፣ የአፍሪቃ መዲና፣ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት አዲስ አበባ÷ ትንሽ ጉድፍ ጎልቶ የሚታይባት በመኾኑ አመራሯ ጥንቃቄን እንደሚጠይቅ በ፳፻፫ ዓ.ም. በንቡረ እድ አባ ገብረ ማርያም ገብረ ሥላሴ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ሀገረ ስብከቱን በሊቀ ጳጳስነት የመሩት ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የተጣለባቸው አደራ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን እንዲረዱ እና አዲስ አበባን እንዲያስተካክሉ መኾኑን ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አስታውቀዋል፡፡ አዲስ አበባ ብዙ ችግሮች ቢኖሩባትም ሕግ ፈጻሚዎች መኾን እንዳለብን በአጽንዖት ያመለከቱት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ አበክረው እንዳሳሰቡት፣ እያንዳንዱ የራሱን ጉድፍ ካጸዳ አዲስ አበባ በአንድ ቀን ልትጸዳ ትችላለች፤ ኹሉም የየራሱን ድርሻ ከተወጣና በቅንነት ከሠራ ልትስተካከል ትችላለች፡፡

abune kewestosብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት መዋቅር በአዲስ አበባ በስብከተ ወንጌል ለብዙ ጊዜ ሲያገለግሉ እንደነበር ብፁዕነታቸው አስታውሰዋል፡፡ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በጸባቴነት፣ በደብረ ከርቤ ደብረ ጽጌ ማርያም እና በደብረ ብርሃን ሥላሴም በእልቅና ባገለገሉበት ወቅትም በርካታ ነገሮችን በማስተካከላቸው አኹን ፓትርያርኩን እንዲረዱ ሲመደቡ ፈተናውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ ለዚኽም ‹‹እርሳቸው ፓትርያርኩን ሲረዱ እኛ [የሀ/ስብከቱ፣ የክፍላተ ከተማና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ሠራተኞች] ደግሞ ብፁዕነታቸውን መርዳት ይጠበቅብናል›› ብለዋል፡፡

‹‹በአሉባልታና በሐሰት አሸናፊ ለመኾን አይቻልም፤ ሀገረ ስብከቱን የሚያመሰቃቅለው አሉባልታና ሐሰት መወገዝ አለበት›› /የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን/

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ኾነው የተመደቡበትን የሹመት ደብዳቤ በንባብ ያሰሙት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የሀ/ስብከቱንና የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን በመወከል ባሰሙት ንግግር÷ ‹‹እኛ የቅዱስ ሲኖዶሱን ትእዛዝ እናከብራለን፤ በዚኹም መሠረት ብፁዕ አባታችንን ተቀብለናቸዋል›› ብለዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ አዲስ አበባ መልካም ነገሮች የሞሉባትን ያኽል ውስብስብ ነገሮችም አሉባት፤ የውስብስቡ ቋጠሮ ሊፈታና ሊስተካከል የሚችለውም ኹሉም የድርሻውን ሲወጣ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች በአሉባልታና በሐሰት አሸናፊ ለመኾን እንደሚሯሯጡ ያስታወቁት ሊቀ አእላፍ ቄስ በላይ፣ በሀ/ስብከቱ ነገሮችን የሚያመሰቃቅለው አሉባልታና ሐሰት መወገዝ እንዳለበት ከመግለጻቸውም ባሻገር ‹‹በክርስትና አሸናፊነት ሰላምና ቸርነት ማድረግ ነው፤ በጎውን ብናደርግ መልካሙን ብንሠራ መልካም ስም ማትረፍ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡ ለዚኽም ‹‹የብፁዕነታቸውን መመሪያ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ለማስፈጸምና በትእዛዙ መሠረት ለመጓዝ ቃል እንገባለን፤›› በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ከተገኙት ከአምስት መቶ ያላነሱ የገዳማትና አድባራት ተወካዮች መካከል የአራት አድባራት አስተዳዳሪዎች በሰጡት አስተያየት፣ ከብፁዕነታቸው መመሪያ እየተቀበሉ በመታዘዝና በመመካከር ተግተው ለመሥራትና የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡

‹‹እንኳን ደስ ያለዎት ሳይኾን ያጽናዎት፤ ያልምዶት ማለት እፈልጋለኹ›› ያሉት የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ፀጋይ ግደይ፣ በሀገረ ስብከቱ አገልግሎታቸው ብዙ ሊቃነ ጳጳሳትና ሥራ አስኪያጆች ተመድበው ማለፋቸውን ገልጸው ‹‹ብፁዕ አባታችን ረዥም ጊዜ እንዲቆዩ እኛ ሰላማውያን መኾን ይገባናል፤ ምእመናን ከእኛ መልካም ነገር ይሻሉ፤ እኛም በጎና መልካም እንኹን›› ብለዋል፡፡ አዲስ አባቶች ተመድበው በመጡ ቁጥር የተወሰኑ ግለሰቦች ከሌላው ጎልተው የሚታዩበትና ለሌሎች ትኩረት የሚነፈገበት ኹኔታ መታረም እንደሚገባው ያሳሰቡትም ‹‹ትንሽ አለቃ፣ ትልቅ አለቃ የለም፤ ኹላችንም የቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴዎች ነን፤ በቅዱስ ሲኖዶስ ነው የተሠየምነው›› በማለት ነው፡፡

‹‹ችግሮች እንዲወገዱ እኛም ጥረት እናደርጋለን›› ያሉት የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ሊቀ ሊቃውንት፣ ሀገረ ስብከቱም ለጉዳዮች አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት፣ ጉዳዮች በተገቢና በተቀላጠፈ አሠራር ከታዩ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚፈታተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ÷ የመናገር/የአነጋገር ችግር እንደሌለና የሔደውን መውቀስ የመጣውን ማወደስ ልማድ መኾኑን ተችተው፣ ‹‹ንግግር ከማብዛት ይልቅ ወደፊት በየሥራችን ብንመዘን፤ ይህን ብፁዕነትዎ በሒደት ይለዩት፤ አኹን ግን ብፁዕነታቸውን ተቀብለናልና በዚኹ ብናበቃ›› ሲሉ የአስተያየቱ ክፍለ ጊዜ ተጠቃሎ ወደ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ቃለ ምዕዳንና መመሪያ ሽግግር ተደርጓል፡፡

ተስማምቶና ተግባብቶ፣ ምስጢር ጠብቆና ምስጢራውያን ኾኖ መሥራት የብፁዕነታቸው ንግግር ዋነኛ ትኩረት ነው፡፡ ‹‹ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ይህችን ጊዜ ስለሰጠን እናመሰግነዋለን›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ወደ ታላቁ ከተማ ተመድቤ ስመጣ ቅዱስ ፓትርያርኩን እንድረዳ ነው፤›› ካሉ በኋላ ዓላማቸው ሰላምን ማስፈንና ቤተ ክርስቲያንን ማስፋፋት እንደኾነ አስታውቀዋል፤ ኹላችንም የቤተ ክርስቲያን እንደራሴዎች ስለኾን ሕጉን ጠብቀን መጓዝ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም ‹‹ኹሉም የአካላችን ሕዋሳት ልዩ ልዩና የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፤ ሕዋሳቱ አልታዘዝም ካሉ ግን ችግር ይፈጠራል፤ ተግባብተን ተደማምጠን መሥራት አለብን፤ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምስጢር ነው፤ ምስጢር ጠብቀንና ምስጢራውያን ኾነን ልንጓዝ ይገባል፤ ሥራ በምንሠራበት ወቅት መሰናክል፣ መውደቅና መነሣት ይኖራል፤ ይህንንም በመተባበርና በመከባበር ማረም ይገባል፤ ከቅዱስ አባታችን መመሪያ እየተቀበልን እንሠራለን፤››ብለዋል፡፡

ወደፊት በሥራ መተያየትና መመዘን እንደሚገባ በቀበና መሥራቀ ፀሐይ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የተሰጠውን አስተያየት የተጋሩት ብፁዕነታቸው፣ ንግግራቸውን የቋጩት ለተሰብሳቢው ኹሉ መነጋገርያ ኾኖ በዋለው ተከታዩ ቃል ነበር – ‹‹የቅድሙ ተናጋሪ እንዳሉት ለወደፊቱ በሥራ መተያየት ያስፈልጋል፤ የሥራ መርሐ ግብር እናወጣለን፤ ኹሉንም በየድርሻውና በየደረጃው እናስተናግዳለን፤ በሥራው ሰዓት በቢሮ እንድትስተናገዱ እንጂ ወደ መኖርያዬ እንድትመጡብኝ አልፈልግም፡፡››

ከሰባት መቶ ያላነሱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እና የገዳማትና አድባራት የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት በዚኹ የአቀባበል መርሐ ግብር÷ ለሰባቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች የአስተያየት መስጫ መርሐ ግብር አለመያዙ ቅሬታ አሥነስቷል፡፡ በአንዳንድ ተሳታፊዎች ዘንድም ሀገረ ስብከቱ ለክፍለ ከተማ የሥልጣን መዋቅር ነፍጎታል ለሚሉት ትኩረት ቀጣይ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡

ለሀገረ ስብከቱ የገዘፈና የተመሰቃቀለ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደ አንድ መንሥኤ የተወሰደው፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች በቃለ ዐዋዲው የተደነገገው ሥልጣን ተከፍሎ አለመሰጠትና ሥራቸውን አለመሥራታቸው እንደነበር ያስታወሱት ሓላፊዎቹ፣ የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስችል ችግር ፈቺ አደረጃጀት ቢዘረጋም በአፈጻጸም/በተግባር ደረጃቸው ተጠብቆ የሥራ ድርሻቸውን የሚያከናወኑበት ሥልጣን አላቸው ለማለት አዳጋች እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ከሀገረ ስብከቱ ጋራ ሽሚያ በሚመስል አኳኋን የሠራተኛ ምደባ፣ ዝውውርና ዕድገት እንዲኹም ሌሎች መንፈሳዊና ልማታዊ ተግባራት ባለመናበብ ሲፈጸሙ የነበረበትን ኹኔታ በመገምገም፣ በሀገረ ስብከቱ እና በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች መካከል ግልጽ የሥራ ክፍፍል የሚያስቀምጥ ጊዜያዊ መመሪያ በጋራ ስምምነት ተዘጋጅቶ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ይኹንታና የአፈጻጸም አቅጣጫ የሰጠበትና የብዙኃኑን ካህናትና ምእመናን ተቀባይነት ያረጋገጠው የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት በሥራ ላይ እስኪውል ድረስ በሀገረ ስብከቱና በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶቹ የተስማሙበት ይኸው ጊዜያዊ መመሪያእንዲሠራበት ተደጋጋሚ ውሳኔ ቢተላለፍም ባለመተግበሩ በአኹኑ ወቅት በክፍላተ ከተማ /ቤቶቹ ተሟሙቶ ለሚታየው የአሠራር ኹኔታበመንሥኤነት ተቀምጧል፡፡

ኹሉንም በየድርሻውና በየደረጃው በማስተናገድ ሰላምን ለማስፈንና ቤተ ክርስቲያንን ለማስፋፋት ቃል የገቡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ÷ በሀገረ ስብከቱ እና በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች መካከል ተፈጥሮ ለቆየው የአሠራር ክፍተት ተገቢውን ትኩረት ከመስጠት ባሻገር ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለሚያስገኘውና ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገር ሲገባው በእጅጉ የዘገየውን የመዋቅር የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት አፈጻጸም በመምራት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን የተቋማዊ ለውጥ አርኣያ እንደሚያደርጉት ተስፋ አለን፡፡ የኾኑ ግለሰብ ሓላፊዎች ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ብቻ ሳይኾን በጥናት የተደገፈውና የብዙኃኑን ተቀባይነት ያረጋገጠው የተቋማዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ ፡-ሐራ ተዋህዶ

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: