መንግሥት ያስተላለፈውን ጥብቅ ትዕዛዝ በመተላለፍ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጣስ ሙከራ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ከሰባት እስከ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው ከዘጠኝ ፓርቲዎች የተውጣጡ አመራሮችና አባላት፣ ታኅሣሥ 1 እና 2 ቀን 2007 ዓ.ም በመታወቂያ ዋስ ከእስር ተፈቱ፡፡
የሰማያዊ ፓርቲና የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ፣ በአምስት ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰባት፣ አሥርና 14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው 84 እስረኞች በሁለቱ ቀናት ውስጥ የተፈቱ ሲሆን፣ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ ለሰላማዊ ሠልፉ ወጥተው ታስረው የነበሩ ሰዎች ሁኔታቸው እየተጣራ ኅዳር 28 እና 29 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈታታቸውም ታውቋል፡፡
ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ኅዳር 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ለ24 ሰዓታት፣ የዘጠኙ ፓርቲዎች ጥምረት ሊያደርግ ለነበረው ሰላማዊ ሠልፍ ቅስቀሳ ወጥተው የታሠሩ ሦስት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ግን አለመፈታታቸው ታውቋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ ማቲያስ መኩሪያ፣ የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ባህሩ እሸቱና አቶ ሲሳይ ዘርፉ ናቸው፡፡
ሦስቱ የፓርቲው አባላት የታሰሩት ለሰላማዊ ሠልፉ ቅስቀሳ ወጥተው በመሆኑ ሌሎቹ ሲፈቱ መፈታት ቢኖርባቸውም፣ ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ የሰባት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቆባቸው አለመፈታታቸው ተገልጿል፡፡
የታሰሩት የፓርቲዎቹ አመራሮችና አባላት በወቅቱ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸውና እንደተጎዱ የተገለጸ ቢሆንም፣ የሰማያዊ ፖርቲ አባላት ከሆኑት አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድና ወ/ሪት እየሩስ ተስፋው በስተቀር፣ ሌሎቹ ደህና መሆናቸው ታውቋል፡፡ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ሰውነታቸው ጉዳት እንዳለውና ሕመም እንደሚሰማቸው ከመናገራቸው ውጪ የከፋ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈይሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- ረፖርተር