ብስራት ወልደሚካኤል
የፖለቲካ ምርጫ ህዝብ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጥበትና ለዚህም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት አካል ነው፡፡ ሂደቱ የሚከናወነውም ሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በተዘጋጀላቸው እኩል መድረክ ተወዳድረው አማራጫቸውን ለህዝቡ በማቅረብ የመንግስት ስልጣን ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የፖለቲካ ምርጫን ከጀመረች የቆየች ቢሆንም፤እስካሁን በህዝቡ ተቀባይነትና መተማመን ላይ የደረሰ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውጤት ላይ ለስልጣን የበቃ የመንግስት ስርዓት ለማየት እንዳልተቻለ ይነገራል፡፡
የፖለቲካ ምርጫ ዓላማ፣ጠቀሜታና አስፈላጊነት ዜጎችን የሀገራቸው ስልጣን ባለቤት ከማድረግ ጎን ለጎን ሀገሪቱን የመምራት ዕድል ባጋጠማቸውና በህዝቡ መካከል መተማመን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው የነቃ ተሳትፎ የሚደርስባቸውን ግድያ፣ እስር፣ ስቃይ፣ ስደት፣አድሎና መገለልን ለማጥፋትና ለመቀነስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ስልጣን ምርጫ በቀረበ ቁጥር መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ዜጎች ላይ የሚወሰደው ጭካኔ የተሞላበት እምርምጃ ተባብሶ የሚቀጥል በመሆኑ፤በገዥው ስርዓት በሚወሰዱ ወታደራዊ የኃይል እርምጃዎች መቀነስ ሲገባቸው ይበልጥ ተጠናክረው በመቀጠል በርካታ ንፁሃን ዜጎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ፡፡ በሚፈጠሩ ስህተቶችም የድርጊቱ ፈፃሚዎችም ሆኑ አዛዦቹ ኃላፊነት ወስደው አያውቁም፤ ሲወስዱም አይታይም፡፡
ምርጫ በቀረበ ቁጥር ሌላው የሚስተዋለው ችግር የፍትህ ስርዓቱ በህዝብ ያለው ተቀባይነትና አመኔታ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ በተለይም ከገዥው ስርዓት ተቃራኒ ሐሳብ ያነሱት ላይ የሚመሰረተው ክስ፣ የፍርድ ሂደት እጅግ መዘግየትና ፍርዱ ምርጫ ሲመጣ ከመቼውም ቀናት በላቀ ፍርሃት ሲነግስበት ይታያል፡፡ ይሄ በገዥውም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በህዝቡ የሚስተዋል አውነታ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በስልጣን ላይ ያለው አካል የራስ መተማመን ያለመኖርና የህዝብ አመኔታና ቅቡልነት አለኝ ብሎ ባለማመኑ በሚፈጠር ፍርሃት ነው በሚል ሲተች ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በተለይም ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ምርጫ ሲቀርብና ሲመጣ ከበጎ ጎን ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖዎቹ ጎልተው ይወጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ
ኢትዮጵ ውስጥ የፖለቲካ ምርጫ መካሄድ የጀመረው በ1911 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይህም የዘውድ ምክር ቤት በሚል የንጉሱ አማካሪዎች ምርጫ እንጂ የህዝብ የሉዓላዊ ስልጣኑ ባለቤት የሚሆንበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አልነበረም፡፡ ተመራጮችም የህዝብ ወኪሎች ሳይሆኑ የዘውድ አማካዎች ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡ በመቀጠልም በ1923 ዓ.ም. በሀገሪቱ የተፃፈ የመጀመሪያው ህገ መንግስት በቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን መፅደቁን ተከትሎ እኩል ቁጥር ያለው ሁለት ምክር ቤት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ምክር ቤቶቹም የህግ መወሰኛ እና የህግ መምሪያ የሚባሉ ሲሆን፤ አባላቱ የተመረጡት በህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሳይሆን በንጉሰ ነገስቱና በመኳንንቱ ነበር፡፡ ምክር ቤቶቹም ከ1923-1928 ዓ.ም. የጣሊያን ወረራ ድረስ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ከወረራው ድል በኋላ በ1935 ዓ.ም እንደገና የህግ መምሪያና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ያሉት ፓርላማ ተቋቋመ፡፡ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም በንጉሠ ነገሥቱ የተመረጡ ሲሆን የህግ መምሪያ አባላት ግን እንደቀድሞው በንጉሡና በባለሟሎቻቸው አማካይነት የተመረጡ መሆናቸው ቀርቶ የአገር የሽማግሌዎች በየወረዳቸው ተሰብሰበው የሚመርጡዋቸው ባላባቶች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እነዚህ የምርጥ ምርጥ ተወካዮች ከ1935 እስከ 1948 ዓ.ም ድረሰ ሳይለወጡ ለ15 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በመቀጠልም ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ህዝቡ ራሱ ወኪሎቹን በቀጥታ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ በዚህም መሰረት ከ1948-1967 ዓ.ም በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱም ምርጫውን የሚያካሂደው የምርጫ ቦርድ የተቋቋመ ሲሆን፤ስራውም ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይሰራ ነበር፡፡
በ1967 ዓ.ም. በሀገሪቱ በወታደራዊ ኮሚቴ “ደርግ” በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሥልጣኑን ጨበጠ፡፡ በሥራ ላይ የነበረው ፓርላማ ተበትኖ በምትኩ በ1967 ዓ.ም በጥቅምት ወር ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 6ዐ ሰዎችን ያቀፈ የመማክርት ጉባኤ ተመሠረተ፡፡ ይህ የመማክርት ጉባኤ እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ሲሰራ ቆይቶ ተበተነ፡፡
በኋላም በ1979 ዓ.ም 835 አባላት ያሉት የሥራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት የሆኑ ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ ተሰየመ፡፡ በወቅቱ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገሪቱ ቢኖሩም፤ዕጩ ተወዳዳሪ የሚጠቁመውምና የሚያስመርጠው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ “ኢሠፓ” ነበር፡፡ ኢሠፓ ይከተለው የነበረው የሶሻሊስት ርዕዮት ዓለምን በመሆኑ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ዝግጁነቱም ሆነ ፈቃደኝነቱ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም በነበረው ምርጫ ጠቋሚው፣ አስመራጩ እና ተመራጩ ራሱ “ኢሠፓ” ነበር፡፡
በግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በትጥቅ ትግል ኢሠፓን በኃይል ከተወገደ በኋላ ወደ ሥልጣን በወጣው ኢህአዴግና አጋሮቹ የሽግግር መንግስት ተመሰረተ፡፡ በሽግግር መንግስቱ በየካቲት 1984 ዓ.ም የወረዳና የቀበሌ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ምርጫመደረጉን እና ብዙ ሳይቆይ በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም ሀገር አቀፍ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ መደረጉን የአሁኑ የምርጫ ቦርድ ድርሳን ያመለከታል፡፡
በወቅቱ የነበረው ምርጫ ኮሚሽን ሥራውን አጠናቆ ሲጨርስ በምትኩ የዛሬው “ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ” በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም መሠረት ተቋቋመ ፡፡ በተለይ በህዳር 1987 ዓ.ም. በሀገሪቱ ታሪክ 4ኛ ተደረጎ የሚወሰደው ህገ-መንግስት ከፀደቀ በኋላ ቀደም ሲል በአዋጅ የተቋቋመው “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ” በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 1ዐ2 መሠረት ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቋቋመ ሲቪል ተቋም ነው ቢልም፤ ዛሬም ድረስ ከገዥው ስርዓት በስተቀር በህዝቡም ሆነ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃና ገለልተኛ አይደለም በሚል ይተቻል፡፡
ቦርዱ ከተሠየመበት ከህዳር 1986 ዓ.ም ጀምሮ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች ተከትሎ በተፈጠሩ ቅሬታዎች መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ሐሳቦችን አካቷል በሚል የምርጫ አዋጁ አምስት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡ይሁን እንጂ ችግሩ በተለይም ቦርዱ ነፃና ገለልተኛ አይደለም፣ የገዥው ስርዓት አንዱና ዋነኛው መሳሪያ ነው የሚሉ በርካታ ቅሬታዎች ከማስረጃ ጋር ቢቀርብም፤ ቦርዱ ራሱን ነፃና ገለልተኛ ነኝ በሚል ዛሬም ቀጥሏል፡፡
በተለይ በዘመነ ኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የተቋቋመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በስምና በስልት ካልሆነ በግብር ከቀደሙት ብዙም የተለየ አይደለም በሚል ቢተችም፤ በሀገሪቱ የነበረውን የምርጫ ታሪክ ወደ ጎን በመተው፤ ራሱን ቀዳሚ በማድረግ 1ኛው ምርጫ ብሎ የሚጀምረው በግንቦት1987 የተደረገውን ነው፡፡ በመቀጠልም 2ኛው በግንቦት 1992፣3ኛው በግንቦት 1997፣ 4ኛው በግንቦት 2002ዓ.ም. ብሎ 5ኛውን የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ለማካሄድ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ቦርዱ አከናወንኳቸው በሚላቸው ያለፉት አራቱም ምርጫዎች አስፈፃሚዎች፣ የህዝብ ታዛቢዎችና የቦርዱ አባላት ከአባልነት ጀምሮ ለገዥው ስርዓት ወገንተኝነት ስላለ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አልነበረም በሚል ወቀሳ የቀረበበት ሲሆን፤በተለይ በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ግን ያልተጠበቁ በርካታ ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ ከነበሩ ክስተቶች መካከልም ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ያልተጠበቀ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው፣ በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከምርጫ ውጤት ጋር በተያያዘ በንፁሃን ሲቭሎች ላይ የተፈፀመው ግድያና እስራት እንዲሁም ስደት የማይረሳ ክፉ ትዝታን ጥሎ አልፏል፡፡
ቦርዱ በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የነበረውን የምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በምርጫ ቦረድ፣በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በዋነኞቹ ተፎካካሪ በነበሩት ቅንጅት እና ህብረት ከፍተኛ ቅራኔ ተፈጠረ፡፡ በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞች ሲሰሙ፤በተለይም በአዲስ አበባ በመንግስት የመከላከያና ፖሊስ አባላት ህፃናትን ጨምሮ ከ160 በላይ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ የአሁኑ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የመጨረሻ ውጤት መሰረት ከ547 የህዝብ ተወካዮች (ፓርላማ) መቀመጫዎች መካከል ኢህአዴግ 327፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች 174 (ቅንጅት 109፣ ህብረት 52፣ ኦፌዴን 11)፣ የኢህአዴግ አጋር ፓርቲዎች የሚባሉት 45 እና 1 የግል ተወዳዳሪዎች መቀመጫ ማግኘታቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በወቅቱ በምዕራብ ወለጋ ደምቢዶሎ የግል ተወዳዳሪ ሆነው ያሸነፉት ደግሞ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡
በግንቦት 2002 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ ደግሞ ተስፋ ሲጣልበት የነበረው የዴሞክራሲ ስርዓት በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ስር መውደቁ ራሱ ገዥው ኢህአዴግንም እጅግ ያስደነገጠ ነበር፡፡ ይህም ገዥው ስርዓት በሚከተለው አሰራር ከቢሮ ጀምሮ የመንግስትን ንብረት ከህግ አግባብ ውጭ በይፋ ከመጠቀም አልፎ ከራሱ ውጭ መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ሚና እንዳይኖራቸው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በገዥው ፓርቲ ጥብቅ ቁጥጥርና መልካም ፈቃድ ካልሆነ ተፎካካሪዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንም ሆነ የአደባባይ የፖለቲካ ምክክርና ክርክር እንደ 1997 ዓ.ም. እንዳያደርጉ በርካታ የእጅ አዙር አሉታዊ ገደቦች የተጣሉ ተጣሉ፡፡ ከነዚህም መካከል በቴሌቪዥን መስኮት ለህዝቡ ፊትለፊት የሚደረግ ክርክር ቀርቶ በስቱዲዮ ተቀርፆና ተቀንሶ እንዲተላለፍ ተደረገ፡፡ በዚህም መሰረት በዓለም ላይ በመድበለ የፖለቲካ ፓርቲ ስርዓት ታይቶ የማይታወቅ በግንቦት 2002 ዓ.ም.በተደረገው ምርጫ ከ547 የፓርላማ መቀመጫ ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ 545 መቀመጫ ድምፅ ሲያገኙ፣ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 1 ተወዳዳሪ ከአዲስ አበባ የአንድነት/መድረክ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ፣ ከደቡብ ክልል ልዩ ቦታው ከፋ ቦንጋ በሚባል አካባቢ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚባሉ 1 የግል ተወዳዳሪ ሆነው ብቻ ማሸነፋቸውን ቦርዱ ይፋ አደረገ፡፡ ከዛ ውጭ ያለውን 99.6 በመቶ የሚሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በአንድ ፓርቲ ሐሳብና ድምፅ ውክልና ተዋጠ፡፡
መጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. እና ሰብዓዊ መብቶች
ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በሀገሪቱ አንፃራዊ ሐሳብን የመግለፅ መብትና የፕሬስ ነፃነት ሙከራ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ 1997 ዓ.ም. ተከትሎ በተወሰዱ ስልታዊ እርምጃዎች 101 የነበሩ የህትመት መገናኛ ብዙኃን በ2007 ዓ.ም. ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ ያሉት ጋዜጦችና መፅሔቶች በአጠቃላ ከ25 አይበልጡም፡፡ ከነዚህም 16 ያህሉ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኀበራዊ ላይ ትኩረት አድርገው ይሰሩ ከነበሩት ውስጥ 8ቱ መንግስት በመሰረተው ክስና ስልታዊ እርምጃ ከአንባቢው ውጭ ሆነዋል፡፡ የብሮድካስ ሚዲያ በተለይ ከጥቂት መዝናኛ ላይ ትኩረት ከሚያደርጉ ኤፍ ኤም ጣቢያዎችና ንብረትነታቸው የገዥው ፓርቲና የመንግስት ከሆኑት ውጭ አጭርና መካከለኛ የሬዲዮ ሞገድ ስርጭት ጣቢያ እስካሁን አልተፈቀደም፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ እስካሁን ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አንድም የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የለም፡፡ ይህም ምርጫ 1997 ዓ.ም. ለነበረው ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና የነበራቸው በመሆኑ ገዥው ስርዓት እንዲቀጥሉ ባለመፈለጉ የተወሰዱ እርምጃዎች ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡በተለይ ከምርጫ 1997 ዓ.መ. በፊት አዲስ ብሮድ ካስቲንግ ካምፓኒ የሚባል የሬዲዮ ጣቢያ የስራ ፈቃድ ወስዶ ለስርጭት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ቢያስገባም፤ኩባንያው ስርጭት ሳይጀምር ከምርጫ በኋላ መሳሪያዎቹ እንዲወረሱና ፈቃዱም እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ይሄም አንዱ ያለፈው ምርጫ አሉታዊ ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡
የነበሩት የጋዜጦችና የመፅሔቶች መጠን በእጅጉ መቀነስ ዋነኛው ምክንያት ያ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ያ እንዳይቀጥል የተለያዩ አዋጆች ተከታትለው የወጡ ሲሆን፤በዋነኝነትም የፕሬስ ነፃነት አዋጅ፣ የብሮድካስት ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት አዋጆች ይጠቀሳሉ፡፡ አዋጆቹም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የፕሬስ ነፃነት እና ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የፕሬስ ነፃነትና የሲቪክ ተቋማትን መጎልበት አሽመድምደውታል፡፡ በተለይ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ ነፃ ፕሬስ መመስረትና ነፃና ገለልተኛ የሲቪክ ተቋም (የሙያ ማኀበርም ሆነ የብዙኃን ማኀባር) ማቋቋም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የምርጫ ውጤትን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ ሲሆን፣ ለዚህም እርምጃ ህጋዊነት ለማላበስ ተቋማቱ ከገዥው ስርዓት ቁጥጥር እና ፍላጎት ውጭ እንዳይሆኑ የሚያስችል አዋጅ ከመደንገግ በተጨማሪ መዋቅር ዘርግቶ ተቋም እስከመመስረት ተደርሷል፡፡ የዚህም ውጤት ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲጣሱ ሰፊ እድል መፍጠሩ ቢታወቅም፤ በመንግስት በኩል ግን እስካሁን የተወሰደ እርምት የለም፡፡
በተለይ በ2001 ዓ.ም. የወጣው የፀረ-ሽብርተንነት አዋጅ የሀገሪቱን እና ህዝቧን ደህንነት ለመጠበቅ በሚል የወጣ አዋጅ ነው ቢባልም፤ በተግባር እየታየ ያለው ግን የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም አዋጁ ህገ መንግስቱን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥሱ አንቀፆች ያሉበት በመሆኑ ሐሳባቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሞከሩና በህዝቡ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ብሎገሮች የአዋጁ ሰለባ ሆነዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ አዋጁን ተከትሎ 17 ጋዜጠኞችና ብሎገሮች እንዲሁም ከ200 ያላነሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ለከፍተኛ ስቃይና እስር ተዳርገዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይፋ እያወጧቸው ያሉና ይፋ ያልወጡ በየ አካባቢው በሺህዎች የሚቆጠሩ እንደታሰሩ፣ ፍርድ ቤት ያልቀረቡና ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎችም ቀላል አይደሉም፡፡ በዚህም የዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለፅ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውና አካላቸው ያለመደፈር መብትን ጨምሮ የዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መነፈጉ ይነገራል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ተደርጎ ቢወሰድም፤ በግንቦት 16 ቀን ለሚካሄደው መጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡
ተፅዕኖውም ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ገልፀው በሚፈልጉት የፖለቲካም ሆነ ማኀበራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉና ገዠው ስርዓት በሚያከናውናቸው አሉታዊ ድርጊቶች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እስር እንደሚጠብቃቸው በመገመት በፍርሃት እንዲቀድቁ ምክንያት መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ይህም በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ገዥው ስርዓት ካላዘዘና ካልፈቀደ በስተቀር በፖለቲካው፣ በማኀራዊ እና በኢኮኖሚው ላይ ነፃ ተሳትፎ እንዳይኖር ተጨማሪ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ብለው የሚከራከሩም አልታጡም፡፡
ቀደም ሲል በተወሰዱ እርምጃዎች መጪው ግንቦት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ከወዲሁ የፍርሃት ድባብ እንዳጠላበት በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ለአብነትም ከሚያዚያ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በፖለቲካውና ማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የሚታመኑ ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መታሰራቸውና በርካታ ጋዜጠኞች መሰደዳቸው ሌላው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ በስልጣን ላይ ለመቆየት ካለው ጉጉት የተነሳ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱና እንዳሉና፤ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ይገመታል፡፡ለዚህመ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የስርዓት ለውጥ ፍላጎቶች፣ የኑሮ ውድነት፣ በገዠው ስርዓት የሚፈፀሙ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ውጤቱንም ሆነ ሂደቱን በፍርሃትና በጉጉት እንዲጠበቅ አስችሎታል፡፡
በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና በመራጩ ህዝብ በኩል አሁን ያለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎችም ሆኑ የህዝብ ታዛቢ ተደርገው የሚቀመጡ ሰዎች ነፃናት ገለልተና ሳይሆኑ ለገዥው ስርዓት ወገንተኝነት የሚታይባቸው ናቸው ተብለው ቅሬታ ቢቀርብባቸውም በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻለም፡፡ እንደ ምርጫ 1997 ዓ.ም. የአውሮፓ ህብረት፣ የአሜሪካና ሌሎች ነፃና ገለልተኛ ናቸው የሚባሉ በርካታ የሲቪክ ተቋማት ከሀገሪቱ እንዲባረሩ በመደረጋቸው ምርጫ 2007 ዓ.ም. እንደማይታዘቡ መረጃዎች የጠቀሙ ሲሆን፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካ ህብረት ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ምርጫው ከወዲሁ የፍርሃት ድባብ ያጠላበት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ምናልባትም የፍርሃት ድባቡ ወደ እውነት የሚቀየር ከሆነና መንግስት ካለበት ውስጣዊና ውጫዊ ችግር በማንኛውም መንገድ ራሱን በስልጣን ለማቆየት ካለው ፍላጎት አንፃር እንደ ከዚህ ቀደሙ የኃይል እርምጃን የሚጠቀም ከሆነ፤ በሀገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ሌላ ከፍተኛ የፖለቲካና ማኀበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተለይም ምርጫውን አስመልክቶና ተከትሎ ሰብዓዊና ዴሞክራሲም መብቶች መጣስ በቀጠናወም ላይም የፖለቲካ አለመረጋጋት በመፍጠር በማኀበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም መጪው ምርጫ ከሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብት አንፃር ከአዎንታዊ ጎኑ ይልቅ አሉታዊ ተፅዕኖው ሊወጣ ይችላል በሚል ከሀገሪቱ ዜጎች በተጨማሪ የዓለም አቀፍ ትኩረት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡