ታዋቂውና ስመ ጥር የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ሳይንቲስትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶ/ር መረራ ጉዲና በመንግስት መደበኛው በስራ በቆያ ዕድሜያቸው በመጠናቀቁ ስራቸውን በሚታደስ ውል ስራቸውን እንዲቀጥሉ የትምህርት ክፍሉ ፈቃደኝነታቸውን በጠየቀው መሰረት ውል ፈርመው በስራ ገበታቸው ላይ እንደሆኑ አስታወቁ፡፡
ዶ/ር መረራ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ እንደገለፁት ከሆነ፤ በዩኒቨርስቲው በማስተማርና በምርምር ከ25 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉና አሁን ዕድሜያቸው 60 ዓመት ስለሞላቸው የጡረታ ጊዜያቸው በመሆኑ፤ በእሳቸውና በዩኒቨርስቲው መካከል በሚታደስ አዲስ የኮንትራት ውል ስምምነት መሰረት ስራቸውን ለመቀጠል ከዚህ ቀደም ከሚያስተምሩበት ትምህርት ክፍል እና ከዩኒቨርስቲው ማኀበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር መፈራረማቸውን እና ስራቸውንም መቀጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው በኮንትራት መልክ የሚታደሰው አዲሱ የውል ስምምነት ሊፀና የሚችለው በእሳቸውና በትምህርት ክፍሉ ስራውን ለመቀጠል የሚያስችል ፈቃደኝነት ስምምነት በዩኒቨርስቲው አስተዳደር በኩል ሲፀድቅ መሆኑንም ሳይገልፁ አላለፉም፡፡
አዲስ ሚዲያም በቅርቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዶ/ር መረራ ከሚሰሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተባረሩ የሚል ዜና ተሰምቷልና እውነት ነው ወይ ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ “እኔ እስካሁን የደረሰኝ መረጃ የለም፣ መደበኛ ስራዬን እየሰራሁ ነው፣ ነገር ግን አንዳንድ ወሬ እኔም እሰማለሁ እንጂ እሳካሁን የደረሰኝም የእግድ ደብዳቤም ሆነ መሸኛ የለም፣ አዲስ ነገር ካለ ወደፊት አብረን የምንሰማው ነው ሚሆነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ለዶ/ር መረራ ስራ ጋር በተያያዘ ስለተወራው ነገር ለማጣራትና ምላሽ ለማግኘት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ክፍል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነታቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና ያላቸው ሲሆን፤ በአሁን ወቅት የኦፌኮ ሊቀመንበርና በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡