የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናት ተከሰሱ

በታምሩ ፅጌ

-79 ሰዎች መሞታቸውና 13,034 ነዋሪዎች መፈናቀላቸው በክሱ ተጠቅሷል

 

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ጋምቤላ ክልል በመሄድ በማዣንግ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በሕጋዊ መንገድ ሠፍረው ለበርካታ ዓመታት ሲኖሩ የነበሩ የሌላ ብሔር ተወላጆችን በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚሏቸውን በመግደል፣

ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት በማድረስና በማፈናቀል የተጠረጠሩ፣ የጋምቤላ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥን ጨምሮ 17 ባለሥልጣናትና ሌሎች 20 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በክልሉ ተወላጆችና በደገኞቹ መካከል ያለውን የመሬት አጠቃቀም በሚመለከት ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2006 ዓ.ም.፣ ማዣንግ ዞን ጐደሬ ወረዳ ሜጢ ከተማ ውስጥ በተለያዩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች የወረዳ አመራሮችንና ኅብረተሰቡን በመሰብሰብ ውይይት ማድረጋቸውን የፌዴራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠሩት ተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ፣ ‹‹ደገኞቹ በማዣንግ ዞን ውስጥ የያዙትን የእርሻና የቡና ተክል መሬት ለማዣንግ ብሔር ተወላጆች ሊያካፍሉ ይገባል፡፡ የማያካፍሉ ከሆነ ከአካባቢያችን ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል፤›› በሚል አጀንዳ ላይ ተወያይተው መመርያ ማስተላለፋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ክልሉ ሄደው የሠፈሩትና ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል የተባሉት በአካባቢው አጠራር ‹‹ደገኞች›› የሚባሉት የሌላ ብሔር ተወላጆች፣ ተጠርጣሪዎቹ ያስተላለፉትን መመርያ ‹‹አንቀበልም›› ማለታቸውንም ክሱ ጠቁሟል፡፡

‹‹ደገኞቹ›› መመርያውን እንደማይቀበሉ ሲያሳውቁ የማዣንግ ብሔር ተወላጅ የሆኑ አንዳንድ የዞኑ የፖሊስና የሚሊሻ ታጣቂ አባላትን በማደራጀትና በማስታጠቅ፣ ጥቃት እንዲፈጽሙ (በደገኞቹ ላይ) ትዕዛዝ በመስጠትና ራሳቸውም በመሳተፍ፣ ከሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. እስከ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ቀናት፣ በብሔሩ ተወላጆችና በ‹‹ደገኞች›› መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲከሰት ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

በማዣንግ ዞን በተለይ በመንገሺና ጐደሬ ወረዳዎች፣ ከተሞችና ቀበሌዎች ውስጥ ግጭቱ እንዲከሰት በመደረጉ፣ ክሱ እስከሚመሠረት ድረስ የታወቀው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 79 መሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡ 27 ሰዎች ከፍተኛ የአካል ጉዳትና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 273 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸው ንብረትም መውደሙና 13,034 ዜጐች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪዎቹና ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው በማዣንግ ብሔር ተወላጆችና በ‹‹ደገኛው›› ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ክላሽኒኮብ፣ ጦርና የተለያዩ ሥለቶችን በመጠቀም ዜጐችን መግደላቸውን፣ አካል ማጉደላቸውን፣ ማቁሰላቸውንና ቤቶችን በማቃጠል ንብረት በማውደማቸው፣ በወንጀሉ ድርጊት በቀጥታ ተሳትፎ ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የአምስትና የ12 ዓመት ሕፃናትን፣ ጐልማሶችንና ወጣቶችን በጥይት ደብድበው፣ በሥለት ወግተውና አርደው ከመግደላቸውም በተጨማሪ፣ የስምንት ወር ነፍሰ ጡርንና ሌሎች ነዋሪዎችን ወደ ቤት ውስጥ እንዲገቡ በማዘዝ፣ ቤታቸውን በእሳት በመለኮስ አቃጥለው የገደሏቸው መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በቡድንና በተናጠል 30 ክሶችን መሥርቶ ታህሳስ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ የክስ ዝርዝሩ ለተጠርጣሪዎች ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከክሱ ጋር የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ዝርዝር ተያይዞ በመቅረቡ ዓቃቤ ሕግ የምስክሮቹ ዝርዝር ከተሰጠ ለደኅንነታቸው እንደሚያሠጋቸው በመግለጽ እንዳይሰጥ በማመልከቱ ነው፡፡

በወንጀል ድርጊቱ የተጠረጠሩት የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ያዕቆብ ሸራተን ታኪካን፣ የማዣንግ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትንሳኤል ራንጃን ኮንዜን፣ የጐደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮናስ ማርቆስ፣ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ጌታቸው ደቢሊው ተልቲካ፣ የጐደሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር አብዮት ሮኬት ኮርኮት፣ የማዣንግ ዞን ፖሊስ መምርያ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ዋና ኃላፊ ኢንስፔክተር ማቴዎስ ማጥኦት ሀኪ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የአስተዳደርና ማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ አቶ አብርሃም ማይክል፣ የጐደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አማካሪ አቶ ያኬት ሪካ፣ የጐደሬ ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ ተፈራ፣ የዞኑ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይማም ፋሪስ፣ የሜጢ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የግዥና ፋይናንስ ኃላፊ አቶ  ደንገቱ ረጳሽ፣ የጐደሬ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሐቅ አብረሃም፣ የዞኑ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ስምዖን ኮኛንንና ሌሎችም ተጠርጣሪዎች በድምሩ 37 መሆናቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: