ጎበዝ ጠንከር ነው!

        ግርማ ሰይፉ  (የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ግርማ ሰይፉ
(የአንድነት ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት)

ምርጫ ቦርድ ማንም ይዘዘው ማንም ወይም በግል ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ነገር የኢትዮጵያን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከምን ጊዜውም በለይ ወደኋላ ለመመለስ እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊረዳው ይገባል፡፡ ምርጫ ቦርድ ምርጫ እንዲያሰተዳድር በተሰጠው ኃላፊነት የፓርቲዎች አስተዳደሪ ለመሆን እየቃጣው ያለ ተቋም ነው፡፡ ስናከብረው ለመከበር ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ለዚህ ተቋም መጠናክር የበኩላችንን መወጣት አለብን ብለን የተነሳን ፓርቲዎችን ጭምር እየገፉ አለቆቹን ለማስደሰት ደም ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህን የሚያደርጉትን ሰዎች ደግሞ በህዝብ ፊት ለብይን እንዲቀርቡ በግልፅ ማጋለጥ ይኖርብናል፡፡

ትላንትና ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ ቀርቦ የተናገረው በምንም መልኩ አንድነትን አይመጥንም፡፡ የተቀሩት የቦርድ አባላትም ይመጥነናል ካሉ ትዝብት ላይ ይወድቃሉ፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላት ሳያገባቸው እንፈትፍት ሲሉ መፈተፍቱን ለእኛ ተዉልን ነው ያልናቸው፡፡ ዶ/ር አዲሱ በሚዲያ የቦርድ ውሳኔ ሊሆን ይችላል ብሎ ካቀረበ በኋላ ዛሬ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ቦርድ ተሰብስቦ ውሳኔ ሰጥቶዋል፡፡ ይህን ውሳኔ እንገራችሁ ብለው በስልክ ከጠሩን በኋላ የአንድነት ፓርቲ የወረዳ አባላት የሆኑትንም በተመሳሳይ መልክ ጠርተው ነበር፡፡ ለነገሩ ይህ አካሄድ አንድነትን ስለማይመጥን በፅሁፍ እንዲገልፁልን ነግረናቸው ተመልሰናል፡፡ ለማንኛውም ዶ/ር አዲሱ የሰጠው መግለጫ ይህ መግለጫ እንዲሰጥ የወሰኑትን ጨምሮ ለተቀሩት የቦርድ አባላት ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ቦርዱ ተሰብሰቦ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ውሳኔውን ሚዛን የሚያሳጣ መግለጫ ለመስጠት ምን እንዳጣደፋቸው መገመት ቀላል ነው፡፡ በልባቸው የሚደግፉትን ፓርቲ ለማንገስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡

ልክ የዛሬ አምስት ዓመት አንድነት ላይ ተመሳሳይ ግብ ግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የዚህ ተልዕኮ ፈፃሚዎች ዛሬ ላይ ሆነው ምን እንደተጠቀሙ ሲያሰላስሉ ምን እንደሚሰማቸው ባላውቅም ዛሬ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉት አባላት ደግሞ ምን እንደሚያደርጉ መጠበቅ ነው፡፡ ለመማር ያልተፈጠረን ሁሉ ምን ማድረግ ይቻላል? ማንም ተላላኪና ላኪ ሆኖ ቢያገለግልም ዛሬ የተሰማኝ ነገር አንድነት በምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን እንደዚህ ዓይነት ተቋማት በምን ያህል ደረጃ ለመዋረድ ዝግጁ እንደሆኑ ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ አሁንም ትግሉ መራራ፣ የሚያስከፍለው መስዋህትነትም ውድ ሊሆን እንኳን ቢችል የአንድነት አባላት በድል እንደሚወጡት ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ እሩቅ እንደሆነ አውቀን ለጀመርነው ትግል አቋራጭ እንደማንፈልግ መግለፅ ይኖርብናል፡፡

ውድ የአንድነት አባላት ለቀጣይ አንድነት ከምርጫ ቦርድ አሻጥር ለማላቀቅ ለምናደርገው ትግል ቀበቶ ጠበቅ ነው፡፡ ከሰማይ በታች አንድነት ለመፍታት የማይችለው ፈታኝ ነገር ምርጫ ቦርድም ሆነ በውሰጥችን ያሉት ዙንቢዎች ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ ጎበዝ ጠንከር ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: