አንድነት ፓርቲ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አስቸኳይ ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ጠራ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ጠራ፡፡ ፓርቲው ነገ እሁድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ በድጋሚ እንዲጠራ የተገደደው ገለልተኛ እንዳልሆነ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች የቀረቡበትና እየቀረቡበት ያለው ምርጫ ቦርድ ባደረገበት ጫና መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተለይ በአሁን ወቅት በርካታ አመራሮቹና አባሎች የታሰሩበት አንድነት ፓርቲ፤ የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው ምርጫ ላይ ለመሳተፍ መወሰኑን እና በመላ ሀገሪቱም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ 450 ዕጩዎቹን ማዘጋጀቱንና ምርጫውንም በአሸናፊነት ለመወጣት ህዝቡን “2007 ለለውጥ ተደራጅ” በሚል መርህ ሰፊ ሀገራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ይህንንም ተከትሎ አንድነት ፓርቲ፣ ከኢህአዴግና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከቀድሞ በበለጠ እየተካረረ መሄዱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው መግለጫ አውጥቷል፡፡ የፓርቲውን ሙሉ መግለጫ ከታች ይመልከቱ፡-

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዓርማ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፖለቲካዊ ደባ አንድነት ከመስመር አይወጣም!
*******************************************************************************

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
በየትኛውም የአለም ክፍል በተለያየ አጣራርና ስያሜ ቢሰጣቸውም ምርጫን ለማስፈፀም በሕግ የሚቋቋሙ ተቋማት ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት በአንድ ሀገር ዘላቂ ለሆነ ሠላምና መረጋጋት ብሎም ለዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በአንባገነን ስርዓት ውስጥ ላሉ ሀገሮች ደግሞ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና ከምንም በላይ ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራው ምርጫ ቦርድ ይህን የመሰለ ግዙፍ ተግባር እንዲያከናውን፣ የሕዝብ እና የሀገር አደራ እንዲወጣ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ነው፡፡ የዚህ ተቋም አሰራር በተቋቋመለት ዓላማ፣ ሕግ እና አለም አቀፍ መስፈርት መሠረት ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀደሙት አሠራሮችና ውሳኔ አሰጣጦች በበርካታ ኢትዮጵያውያን እና አለም አቀፍ ታዛቢዎች በአሉታዊ ጎኑ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የ2ዐዐ7 ሀገር አቀፍ ምርጫን ‹‹የኢህአዴግ መጨረሻ›› እናደርገዋልን ብሎ ፖለቲካዊ አቋም ወስዶ እንቅስቃሴ ሲጀምር የምርጫ ቦርድን ቀደምት አሉታዊ ተግባሩን ዘንግቶ አይደለም፡፡ ይህ ተቋም መልካም ስም እንዲገነባ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን እድል ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህ ስትራቴጂ መሠረት ቦርዱን በተግባር ፈተና ላይ ጥለነዋል፣ ማንነቱንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለዓለም ማህበረሰብ በማጋለጥ ላይ እንገኛለን፣ ዛሬ ለሁለም የሚዲያ አካላት ያካሄድናቸውን የደብዳቤ ልውውጦች በይፋ አንሰጣለን፣ ሁሉም ዜጋ እንዲደርሰውም እናደርጋለን፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን ከ2ዐዐ7 አጠቃላይ ምርጫ ገፍቶ ለማስወጣት ካልተሳካለትም በተዳከመ የአባላትና ደጋፊ ስሜት ውስጥ ገብተን እንድንጫወት የፈለገ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የአንድነት ፓርቲ በ2ዐዐ7 ዓም ሀገራዊ ምርጫ ከጅምሩ በሁሉም ሂደቶች በንቁ ለመሳተፍ የያዘው አቋም እንዳስደነገጠው፤ ከዚያም አልፎ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠውን ስልጣን አጣለሁ በሚል መሸበሩን የሚያጋልጥ ነው፡፡ ይህን ፍርሃቱን በህዝብ ፊት በሚደረግ ትግል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የመረጠው ሜዳ በብሔራዊ ምርጫ ቦርደ በኩል እንዲሆን ነው፡፡ የቦርዱ ኃላፊዎች ተቋማዊ በሆነ መልክ ደብዳቤ ሲሰጣቸው፣ በደብዳቤ መልስ ከመስጠት ይልቅ በመገናኛ ብዙሃን ምላሻቸውን ቀድመው መናገር ጀምረዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው ታህሣሥ 27 ቀን 2ዐዐ7 ዓም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዝአብሔር ከቦርዱ ስብሰባ በፊት በሚዲያ ወጥተው ውሳኔ በመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ቦርዱ እንደተቋም ሳይሆን በግለሰብ ውሳኔ የሚመራ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም መገለጫው በታህሳስ 30/2007 የደረሰን ደብዳቤ የቦርዱን ምክትል ስብሳቢ ከሚዲያ መግለጫ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ ከምርጫ ቦርድ ባልተናነሰ ሁኔታ በኢትዮጵያ በህግ የተቋቋሙት እና በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱት የመገናኛ ብዙሃንም በፍጥነት ተቀብለው ማስተጋባታቸው በውዥንብር ፈጠራ ላይ ተሳታፊነታቸውን ያሳያል፡፡ ዓላማው በአባላት፣ በደጋፊና በህዝቡ ውስጥ ውዥንብር ለመፍጠር ታሰቦ የሚካሄድ ፖለቲካዊ ደባ ነው፡፡

በሀገራችን አስተማማኝ ሠላም እና ዘላቂነት ያለው ደህንነት የሚያረጋግጠው እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋሞች ነፃ፣ ገለልተኛ እና በህዝብ ዘንድ አመኔታ ሲጣልባቸው ነው፡፡ ይህ ተቋም አሁን በያዘው ሁኔታ ከቀጠለ ከታሪክ ተጠያቂነት አይድንም፡፡ ገዢው ፓርቲም ጧት ማታ የሚያባንነው ሕዝባዊ እምቢተኝነት መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ፓርቲያችንን ለመታደግ እና የቦርዱን የመጨረሻ ካርድ ለማስጣል አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተናል፡፡ ይህ ማለት የትግሉ መጨረሻ አይደለም፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያደረሰብንን የሕግ ጥሰት ይዘን በፍርድ ቤት ክስ እንመሰርታለን፡፡ እስከ አሁን ያለውን ሂደት ስናየው የቦርዱ ፖለቲካዊ ደባ ቀጣይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም መላው አባሎቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምንወስዳቸው ተከታታይ ፖለቲካው ውሳኔዎች እና እርምጃዎች ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን በአክብሮት እናስተላልፋለን፡፡

ድል የሕዝብ ነው
ጥር 1 ቀን 2ዐዐ7 ዓም
አዲስ አበባ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: