የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ህንድ ባለፉት 6 ወራት ውስጥ 2 መቶ ሺህ ለሚደርሱ ስደተኞች መጠጊያ መሆኗን አስታውቋል፡፡
በህንድ እየታየ ያለው የስደተኞች መጨመር በፈረንጆቹ 2014 በዓለማችን አለመረጋጋት ከበረከተባቸው መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ የሚጎርፉ ስደተኞች ቁጥር መጨመር እንደምክንያት ተጠቅሷል፡፡
በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት 5.5 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
ታዲያ በህንድ በተለያየ ምክንያቶች በመግባት በስደት ላይ ከሚገኙ ህዝቦች መካከል ኢትዮጵያዊያንም እንደሚገኙበት የተጠቀሰ ሲሆን በህንድ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮያዊያን ቁጥር 580 ሺህ ይደርሳል ተብሏል፡፡
የሶርያ ስደተኞችም በህንድ ቁጥራቸው እጅጉን የበዛ ነው ተብሏል፡፡
የሶማሊያ ፣ የደቡብ ሱዳን ፣ የኬንያ ፣ የኮንጎ፣ ማይናማር እና ኢራቅም በህንድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ያስመዘገቡ ሀገራት ናቸው ሲል ድሬ ቲዩብ ዘግቧል፡፡
በየጊዜው ኢትዮጵያውያን ባህርና የብስ እንዲሁም አየር አቋርጠው ሀገራቸውን ጥለው የሚሰደዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኞች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ግን ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ከሚያደርጉት ስደት በተጨማሪ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ ህንድን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የሩቅ ምስራቅ እስያ ሀገሮችም እየተሰደዱ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መረጃዎች ያስረዳል፡፡