-“የፍትህና የነፃነት ጥያቄያችን ደም በማፍሰስ አይቀለበስም!”- አንድነት
-በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞችም ተከታታይ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲቀጥሉ ተወስኗል
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ዛሬ ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አራት የክልል ከተሞች የጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በፖሊስ ድብደባ ተጠናቀቀ፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻውን ቀበና ከሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት በማድረግ መዳረሻውን ጥቁር አንበሳ አካባቢ በሚገኘው ኢትዮ-ኩባ አደባባይ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰልፍ በፅህፈት ቤቱ አካባቢ በተፈፀመ የፖሊስ ድብደባና እገታ ሊቋረጥ ችሏል፡፡
የተቃውሞ ሰልፉ ዋነኛ ዓላማም ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ አንድነት ወደ ምርጫው መግባቱን በመወሰን በመላ ሀገሪቱ ከ450 በላይ ዕጩዎቹን ማቅረቡን ይፋ ማድረጉን ተክትሎ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፓርቲው ለ3ኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ በሚል ፓርቲውን ከምርጫ ውድድር ለማስወጣት የሚደረገውን ተግባር ለመቃወም መሆኑን ቀደም ሲል ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከተጠቀሰው ዓላመ በተጨማሪ በዜጎች ላይ የሚደርስ ህገወጥ እና የግፍ እስር እንዲቆም፣ የታሰሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈጡ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ እንዲኖር፣…የሚሉ ጥያቄዎች ይገኙበታል፡፡
መረጃዎች ከስፍራው እንደጠቆሙት ከሆነ፤ የተቃውሞ ሰልፉ ቀበና ከሚገኘው የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት የተነሳው ከ 150 በላይ የሚሆን ሰልፈኛ ከጽህፈት ቤቱ 100 ሜትር ርቀት ላይ ከሚጠብቁ ከ500 በላይ ሰልፈኞች ጋር ከመቀላቀላቀላቸው አስቀድሞ ፖሊሶች ቆርጠው በመግባት ከባድ ድብደባ አድርሰዋል፡፡ አራት ኪሎ፣ በፒያሳና የሰልፉ ማጠናቀቂያ በሆነው ኢቲዮ -ኩባ አደባባይ ይጠባበቅ የነበረው ሰልፈኛ ሊበተን መቻሉንም ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
በተፈፀመው የፖሊስ ድብደባም ከ26 በላይ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከሰልፉ ጋር ምንም ንክኪ ያልነበራቸውና ቀበና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የነበሩ የ70 ዓመት አዛውንትም ከፍተና ጉዳት ደርሶባቸው በአቅራቢያው በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በክልል ከተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች መካከል ፓርቲው በደብረማርቆስ፣ በሸዋሮቢት እና በጋሞጎፋ ከምባ የተሳካ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጉዳት ከደረሰባቸው የአንድነት አባላት መካከል የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ስለሺ ሐጎስና የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ ዳግማዊ ተሰማ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰባቸው ራሳቸውን ስተው እንደነበርና ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበር የዓይን እማኞች ከስፍራው አስታውቀዋል፡፡ በተመሳሳይም ……የተባሉ ነፍሰጡር በፖሊስ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተጠቆመ ሲሆን፤በፖሊስ ድብደባ ከተፈፀመባቸውና ጉዳት ከደረሰባቸው የፓርቲው ስራ አስፈፃሚና አባላት መካከል፡-
- አቶ አስራት አብርሃም (የህዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ሃላፊ)
2. አቶ ዳንኤል ተፈራ (የውጭ ጉዳይ ሃላፊ)
3. አቶ ብሩ ብርመጅ (የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ)
4. አቶ ፀጋየ አላምረው (ምክትል አፈ-ጉባኤ)
5. አቶ አሻግሬ መሸሻ (የሰሜን ቀጠና ሃላፊ)
6. አቶ ሰለሞን ስዩም (የኤዲቶሪያል ቦርድ ሰብሳቢ)
7. ወ/ት ልዕልና ጉግሳ (የም/ቤት አባል)
8. አቶ ዳግማዊ ተሰማ (የም/ቤት አባል)
9. ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጎስ (የም/ቤት አባል)
10. አቶ ስንታየሁ ቸኮል (የአዲስ አበባ የወጣቶች ጉዳይ ሃላፊ)
11. አቶ አሸናፊ አሳምረው (የወረዳ አመራር)
12. አቶ ኢሳያስ ቱሉ (አባል)
13. ወ/ት መስከረም ያረጋል (አባል)
14. አቶ ሃይሉ ግዛው (የወረዳ ሰብሳቢ)
15. አቶ አዲሱ መኮንን (የወረዳ ሰብሳቢ)
16. አቶ ሲሳይ ካሴ (አባል)
17. አቶ ወጋየሁ አድማሴ (አባል)
18. አቶ ክብረት ሃይሉ (የም/ቤት አባል)
19. አቶ ስለሺ ደቻሳ (አባል)
20. አቶ ማሩ አካሉ (አባል)
21. አቶ ክፍሉ በዳኔ (አባል)
22. አቶ ፋሲካ አዱኛ (የወረዳ አመራር)
23. ወ/ሮ ገነት ሞገስ (የወረዳ አመራር)
24. ተስፋየ ብዙነህ (አባል)
25. ሙሉጌታ ተፈራ
26.ኤፍሬም ሰለሞን(የአዲስ አበባ ስራ አስፈፃሚ)
በተቃውሞ ሰልፉ ፖሊሶች ያደረሱትን ጉዳት በቅርብ ሲከታተሉ የነበሩት የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች የአንድነት አመራሮችን እና ጉዳት ደርሶባቸው በየሆስፒታሉ የሚገኙ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን አነጋግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮች ከአባላትና ከደጋፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን አንድነት በአዲስ አበባ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን እንደሚያደርግ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህንንም በተመለከተ ፓርቲው መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤ ሙሉ መግለጫውን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡-
የፍትህና የነፃነት ጥያቄያችን ደም በማፍሰስ አይቀለበስም!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
ፓርቲያችን አንድነት ገዥው ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድና የገዥው ፓርቲ ልሳን በመሆን እያገለገሉ ያሉ ሚዲያዎች በመተባበር ከምርጫ ለማስወጣትና ተለጣፊ አንድነት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ መጥራቱ የሚታወቅ ነው፡፡
የተቃውሞ ሰልፉን ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም እንደምናከናውን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ብናሳውቅም መስተዳድሩ በ12 ሰዓት ውስጥ በፅሁፍ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ሰልፉ እውቅና አለው፡፡ መስተዳድሩ ግን የተጣለበትን ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ወደ ጎን በመግፋት የተወሰኑና የማይታወቁ ግለሰቦች ፔቲሽን ተፈራርመው አምጥተዋል በማለት ብዥታ ለመፍጠር ሞክሯል፡፡ ፓርቲያችን ህጉን ጠብቆ ህጋዊ የሆነ ሰልፍ ለማካሄድ ቢሞክርም አሁንም ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፡፡ በተደጋጋሚ እንዳየነው ፖሊስ ደንብ ማስከበር ሲገባው አድሎ ለፈፀመው አካል በመወገን ድብደባ መፈፀሙ ከወገንተኝነት ያልፀዳ መሆኑን እንድናረጋግጥ አድርጎናል፡፡
ጥያቄያችን አሁንም የፍትህ፣ የእኩልነትና ህግ እንዲጠበቅ የማድረግ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመንግስትነት ስልጣኑን በመጠቀም የስልጣን ዘመኑን ለማስረዘም እየከወነ ያለውን ሴራ ማስቆም ነው፡፡ ጥያቄያችን የነፃነትና ያልተሸራረፈ ዴሞክራሲ ይረጋገጥ የሚል ነው፡፡ ጥቄያችን ምርጫ ቦርድ የገዥው ፓርቲ አጋር መሆኑ ቀርቶ ገለልተኛ ሚናውን ይወጣ የሚል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎቻችን ደግሞ ደም በማሰስ፤ በድብደባም ሆነ በእስር ፈፅሞ አይቆሙም፡፡
በሚቀጥለው ሳምንትም በተለያዩ ከተሞችና በአዲስ አበባ የሰላማዊ ተቃውሞ ድምፃችንን ከፍ አድርገን እናሰማለን፡፡ ትግሉ ይቀጥላል፡፡
ድል የህዝብ ነው!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 17 ቀን 2007 ዓ.ም.
አዲስ አበባ