ሰበር ዜና፤ ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድን ፓርቲን ለእነ ትግስቱ አወሉና ለእነ አበባው መሐሪ ሰጠ

  • ‹‹እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው›› -ፕሮፌሰር መርጋ በቃና

nebe

ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለእነ ትግስቱ አወሉ፣ እንዲሁም መኢአድን ለእነ አበባው መሃሪ መስጠቱን ዛሬ ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹የእነ በላይ በፍቃዱ ቡድን›› በጠቅላላ ጉባኤ እንዳልተመረጠ፣ አምስት አባላት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ አባላት እንዳልመረጠ፣ የተመረጡበትም 51 ሲደመር አንድ መርህ አለመሆኑን፣ ጠቅላላ ጉባኤ ሲያደርግ ሪፖርት አለማድረጉንና ለአባላቱና ለፓርቲው ክብር የሌለው በመሆኑ ፓርቲውን ማስቀጠል እንደማይችል ገልጾአል፡፡

udj

በሌላ በኩል የትግስቱ አወሉ ቡድን መርህ ይከበር እያለ እየታገለ በመሆኑ፣ የኢ/ር ግዛቸው ካቤኔ አባላት ተገፍተው የወጡ በመሆናቸው፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገው ለቦርዱ ሪፖርት እንዳደረጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን›› ፈቃደኛ ባለመሆኑ እንጂ እነሱ ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ በመሆናቸው እንዲሁም ለአባላቶቻቸውና ለፓርቲው ክብር ስላላቸው እውቅናውን ለእነሱ ሰጥቻለው ብሏል፡፡ ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹ምርጫ የሚገባ ፓርቲ በማስፈለጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን ፓርቲውን የሚያስቀጥለው ባለመሆኑና ፓርቲውን እንደ ፓርቲ እንዲቆይ ስለሚፈለግ ዛሬ ጥር 21 ቦርዱ ባደረው አስቸኳይ ስብሰባ እነ ትግስቱ አወሉ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ወስኗል›› ብሏል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ‹‹የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ ስለመሆኑ በምን ታረጋግጡልናላችሁ?›› በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ሁለቱም ችግር አለባቸው፡፡ እኛ ያየነው በአንጻራዊነት ነው፡፡ የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ችግር ቢኖርበትም ከዛኛው የተሻለ ነው፡፡ እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

aeup

በተመሳሳይ እነ ማሙሸት አማረ በጠቅላላ ጉባኤ ባለመመረጣቸው፣ ለተከታታይ 3 ወራት ወርሃዊ መዋጮ ያላወጣ አባል ከአባልነት የሚሰረዝ በመሆኑና ከፓርቲ አባልነትም ስለተባረሩ እንዲሁም ህገ ወጥ ማህተም በማሳተማቸው እውቅና እንዳልሰጣቸው ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል 2005 ዓ.ም ላይ አበባው መሃሪ የተመረጡበት ጠቅላላ ጉባኤ የተሟላ እንዳልነበር ቢታመንም በተደረገ ምርመራ የተሟላ መሆኑ በመታወቁ፣ በትክክለኛው ማህተም ስለሚጠቀም፣ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጉ በተባለበት ወቅት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረጉና ሪፖርቱንም ስላቀረበ ወደ ምርጫው እንዲገባ ወስኛለሁ ማለቱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡

ይሁን እንጂ ፓርቲዎቹ ምርጫ 2007 ዓ.ም. ለመሳተፍ መወሰናቸውን ተከትሎ ህወሓት/ኢህአዴግ  በምርጫ ቦርድ አማካኝነት ሊያፈርሳቸው የተለያየ ህገወጥ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፣ ቦርዱ ገለልተኛ እና ነፃ አለመሆኑን በድርጊቱ እየገለፀ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ተቃውሞና ቅሬታ እያቀረቡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: