ጌታቸው ሽፈራው
አቶ ቀኖ የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ በጥበቃነት ይሰራሉ፡፡ አቶ ቀኖና ጎረቤቶቻቸው ሰብሰብ ሲሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተለይ ኢህአዴግ ስለሚወስዳቸው ህገ ወጥ እርምጃዎች፣ ስለተቃዋሚዎች ጥንካሬና ድክመት… የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ያወራሉ፣ ይወያያሉ፣ በሚያከራክሯቸው ነገሮችም ይከራከራሉ፡፡ ይህ የእነ አቶ ቀኖ ሰፈር ሰዎች የውይይት መድረክ በእነሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ጉዳዩ በመደጋገሙ ህፃናት ልጆቻቸው ሳይቀር ‹‹ሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ፣ ኢህአዴግ…..›› እያሉ የአቅማቸውንና የገባቸውን ያህል ያወራሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸው ሲከራከሩና ሲያወሩ ከሰሙት! በዚህ አቋማቸውም ህፃናቱ ‹‹ፀረ ሰላም›› ተብለው ታስረውበታል፣ ተደብድበውና ይቅርታ ጠይቀውም ተለቀዋል፡፡
ማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው መስከረም 2 ት/ቤት ተማሪዎች የሆኑት 14 ያህል ህጻናት ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ህፃናቱ እንደወትሯቸው ከት/ቤተ መልስ እየተጨዋወቱ፣ እየተቀላለዱ፣ እየተሯሯጡ ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ መሃል ላይ ግን ቤተሰቦቻቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ጉዳይ አንስተው መከራከር ጀምረዋል፡፡ የ13 አመት እድሜ ያለውና የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የአቶ ቀኖ ልጅ ‹‹ኢህአዴግኮ ፈሪ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ይፈራዋል›› ይላል፡፡ ጓደኛው ደግሞ ‹‹ኢህአዴግማ የሚፈራው አንድነትን ነው፡፡›› ይላል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ‹‹መድረክ የሚባል ፓርቲምኮ አለ፡፡ እሱንም ይፈራዋል፡፡ ኢህአዴግ ፈሪ ነው!›› ይላል፡፡ ሌሎቹም ቤተሰቦቻቸው ውሃ፣ መብራትና ኔትዎርክ ሲጠፋ፣ ኑሮ ሲወደድ፣ ሙስና ሲያስመርራቸው በስርዓቱ ላይ ከሚያሰሙት ሮሮ መካከል የሚያስታውሱትን እየጠቀሱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይከራከራሉ፣ ያወራሉ፡፡ ይቀልዳሉ!
ይህኔ ነው አስገራሚው ነገር የተከሰተው፡፡ ፖሊስ 14ቱንም ህፃናት በ‹‹ፀረ ሰላም›› እንቅስቃሴያቸው ከእነ ሙሉ የትምህርት መሳሪያቸው በቁጥጥር ስራ ካዋላቸው በኋላ በጥፊና በእርግጫ እያለ ወደ ወረዳ 7 ፖሊስ ጣቢያ ይወስዳቸዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ከደረሱ በኋላም ‹‹ተንበርከክ!›› ተብለው ‹‹ማን ነው ሰማያዊ፣ አንድነት፣ መድረክ እያለ ሲያወራ የነበረው?›› እየተባሉ ህፃናት ላይ ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብ ድብድባ ይፈፀምባቸዋል፡፡ ህፃናቱ ‹‹ፀረ ሰላም›› ለተባለው እንቅስቃሴያቸው ቅጣትና ማስፈራሪያ ከተደረገባቸው በኋላ ‹‹ከአሁን በኋላ አይደግመንም›› ብለው ይቅርታ ጠይቀው በ‹‹ፖሊስ ሆደ ሰፊነት›› ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ ከእስር ተለቀዋል፡፡
እነዚህ ህጻናት ‹‹ዳግመኛ አይለምደንም!›› ብለው ይቅርታ ባይጠይቁ ኖሮ ታስረው ሊያድሩም ይችሉ ነበር፡፡ ምን አልባትም ፖሊስ ‹‹ያልተፈቀደ ቅስቀሳ አድርገዋል፣ ህገ መንግስቱን ለመናድ ጥረዋል፣ ህዝብን ለማናወፅና አመጽ ለመቀስቀስ ተደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል፣ ምርጫው ሰላማዊ እንዳይሆን እየሰሩ ነው….›› የሚል ክስ እንደማይመሰርት እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ እስካሁን ፖሊስ ሲያቀርባቸው ካየናቸው አስቂኝ የቀጠሮ ማራዘሚያ ‹‹ምክንያቶች›› አንጻር ‹‹አብረዋቸው የሚማሩት ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው አልተያዙም፣ ቢወጡ አሁንም ተመሳሳይ ‹ፀረ ሰላም› ተግባር ይፈፅማሉ፣ መረጃ ይደብቁብኛል›› በሚል ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ላለማለቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ስርዓቱን ለመከላከል ሲባል እስሩ እዚህ ደርሷል!