በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የዞን ዘጠኝ ብሎገሮችና ጋዜጠኞች፤ ሰብሳቢ ዳኛው ከችሎት እንዲነሱ ጠየቁ፡፡
ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ለ17ኛ ጊዜ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ብሎገሮቹና ጋዜጠኞቹ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ሸለመ በቀለ “የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስከበሩልንም” በሚል ከችሎት እንዲነሱ በጽሑፍ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተሰየመው ተሻሽሎ ቀርቧል በተባለው የአቃቤ ህግ ክስ ላይ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት እንደነበር ዳኞቹ ቢናገሩም፣ ተከሳሾች አቤቱታ እንዳላቸው በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃል ለመስጠት ዝግጁዎች አለመሆናቸውን ለችሎቱ ማስረዳት ችለዋል፡፡
ተከሳሾች ‹‹እኛ በሰብሳቢ ዳኛው ላይ አቤቱታ አለን፤ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እንኳ አላከበረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት ዝግጁዎች አይደለንም›› በሚል ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን እንዲቀበል ጠይቀዋል፡፡
ዳኛ ሸለመ በቀለ “ፍርድ ቤቱ ቃሉን አላከበረም›› በሚለው ጉዳይ ላይ መልስ ሲሰጡ ‹‹የእኛን ውሳኔ የማትቀበሉ ከሆነ ጉዳዩን በይግባኝ እንዲታይ ማድረግ ይቻላል” ብለዋል፡፡
“ላለፉት ስድስት ወራት በነበረው የክርክሩ ሂደት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ሂደቱን በአግባቡ በመምራት የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታችንን አላስጠበቁልንም፡፡ በተለያየ ጊዜም ሐሳባችን ለመግለጽ ስንሞክር ክልከላ አድርገውብናል፡፡ አሁን ደግሞ ችሎቱ ራሱ የሰጠውን ትዕዛዝ ራሱ ሽሮ ፈጽሞ ልንረዳው በማንችለውና የመከላከል መብታችንን በሚያጣብብ የክስ ሁኔታ ክርክሩን እንድንቀጥል ሲበየንብን የችሎቱ ሰብሳቢ ወሳኝ ሚና ነበራቸው” ሲሉ ተከሳሾች በሰብሳቢ ዳኛው ላይ ቅሬታቸውን በአቤቱታቸው ገልፀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸለመ በቀለ ከችሎት እንዲነሱ የሚጠይቀውን አቤቱታ አይቶ ነገ ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡