በቅርቡ በ”ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ” ፈርሶ ዋና ጽህፈት ቤቱ በፖሊስና በደህንነት ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ፤ የፓርቲው ጽህፈትም “ምርጫ ቦርድ” መርጫቸዋለሁ ላላቸው አካላት ከተላለፈ በኋላ አባላቱና አመራሩ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው የአንድነት ዓላማዎችና እሴቶች በገዥው ፓርቲ እና ምርቻ ቦርድ ህገ-ወጥ ሴራ እንደማይጠፋ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ከታች ይመልከቱ፡-
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሠጠ መግለጫ
********************************************************************************
የአንድነት ፓርቲ አላማዎችና እሴቶች በገዢው ፓርቲ እና በምርጫ ቦርድ ህገወጥ ሴራ አይጠፋም!!
***********************************************************************************
ገዢው ፓርቲ ለጻፋቸው ህጎችም ሆነ ይህን እንዲተገብሩ ኃላፊነት የወሰዱትን ሰዎች ክብር በሚያዋርድ መንገድ፤ በየደረጃው ያሉ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችም ለመዋረድ ፈቃደኛ ሆነው በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) አባላት አንድ ድምፅ ለማግኘት ለተቸገረ፤ ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ ለመላላክ ቁርጠኛ ለሆነ ግለሰብ ዕውቅና ሰጥቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድነት ፓርቲ የተቋቋመበት መሰረት የምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሳይሆን በእያንዳንዱ አባላት ዘንድ የሚቀጣጠለው የነፃነት ስሜት እና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የአንድነት ፓርቲን መንፈስ፣ አላማዎቸና እሴቶች በዚህ ዓይነት እኩይ ደባ ከአባላትና ደጋፊ አዕምሮ ማውጣት አይቻለም፡፡
የምርጫ ቦርድ ተብዬው ተቋም በገዢው ፓርቲ ደህንነት የተደራጁ የፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ያልሆኑ ሰዎች ያካሄዱትን ህገወጥ ስብሰባ ጉባዔ ነው በማለት እውቅና ሰጥቻለሁ ሲል፤ የተሰበሰቡት ሰዎች የአንድነት አባላት መሆናቸውን እና የጠቅላላ ጉባዔ ተወካይ መሆናቸውን አረጋግጣችኃል ወይ? ለሚል ቀላል የጋዜጠኛ ጥያቄ መልስ መስጠት አልቻሉም፡፡ ዕቅዱም አንድነትን እንደተቋም ማፍረስ ስለነበር ይህን ሊያስፈፅም ለሚችል ተላላኪ መስጠታቸውን በይፋ ከተናገሩ በኋላ በማግስቱም የፓርቲውን ፅ/ቤት በጠብመንጃ አፈሙዝ አስወርረው ለህገወጥ ቡድን በህገወጥ መንገድ አስረክበዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ በዚህ ዓይነት ህገወጥ ድርጊት የሚፈርስ አይደለም፡፡ የአንድነት አባላት በየትም ቦታ የምትገኙ ሁሉ ይህን ህገወጥ እርምጃ በፅኑ እየተቃወማችሁ ለነፃነትና ለኢትዮጵያዊነት የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመከፍል ዝግጁ መሆን ይኖርባቸኋል፡፡ አንድነት ፓርቲ በሰላማዊ ትግል ስልት የሚያምን በመሆኑ ይህን ትግል በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል አበክሮ ይስራል፡፡ እያንዳንዱ አባልም አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ሳይደናገጥ ለሰላማዊ ትግል ያለውን ፅናት እንደሚያስቀጥል እምነታችን ነው። በአንድነት ስራ አስፈፃሚ እምነት አሁን ባለው ሁኔታ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ተቀበረዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል።
በመሆኑም ስርዓቱ ለመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ የሚመች የአስተሳሰብ ለውጥ እሰካላመጣ ድረስ ምርጫን በየአምሰት ዓመት የሚደረግ ክብረ በዓል አድርጎ ለማድመቅ እና የህዝብ ሀብት ለማባከን በሚደረግ ሂደት ተሳተፊ ለመሆን አዲስ ፓርቲ መመስረትም ሆኖ አሁን ካሉት ፓርቲዎች ጋር ተቀላቅሎ መታገል የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱም ልከ በአንድነት ላይ እንደተደረገው በሀይል እንዲፈርሱ የማይደረጉበት ምንም ዓይነት ዋስትና አለ ብለን ስለማናምን ነው። ከዚህ በኋላ በመድብለ ፓርቲ ሰርዓት ስልጣን ይያዛል ብሎ ማመን ህዝቡን ማታለል ነው የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ ነገር ግን አሁንም የፓርቲ ፖለቲካ አላበቃም ብለው የሚያምኑ የአንድነት አባላት ካሉ በራሳቸው ነፃ ውሳኔ ወደ ፈለጉት ፓርቲ ተቀላቅለው የመታግል መብታቸው የተጠበቀ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን ካለበት አምባገነናዊ ስርዓት ተላቆ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሸጋገር ለማድረግ ህዝቡ የትግሉ ባለቤት ሆኖ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ እኛም የበኩላችንን ሀገራዊ ግዴታችንን ለመወጣት ቁርጠኞች ነን፡፡
ድል የህዝብ ነው!!!
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)
ጥር 26 ቀን 2007