ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቤተ እስራኤላውያን ሴቶች ለረዥም ጊዜ የሚያገለግለውን ዴፖ ፕሮቬራ የተባለ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለመወጋት ካልተስማሙ ወደ እስራኤል ሊገቡ እንደማይችሉ ይነገራቸው እንደነበር ይታወቃል።
ክሊኒኩን ያስተድድር የነበረው “Joint Distribution Committee” እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውንጀላውን ማስተባበላቸው የሚታወስ ቢሆንም ዛሬ በወጣው ሪፓርት የእስራኤል መንግስት ውንጀላውን አምኗል።
በርካታ ሴቶች፣ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በክትባት መልክ የሚሰጠውን የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒት እንዲወስዱ እንዴት ያግባቧቸውና ያስፈራሯቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ቤተ-እስራኤላውያኑ ሲገልፁ “የማትወስዱ ከሆነ ወደ እስራኤል አትሄዱም፤ እርዳታና ህክምናም አታገኙ ተባልን፡፡ ይሄኔ ፈራን፤ ምንም ምርጫ አልነበረንም፡፡ ያለ እነሱ እርዳታ መውጣት አንችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ክትባቱን ለመወጋት ተስማማን፡፡” ሲሉ ቤተ-እስራኤላውያን መናገራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በመጥቀስ ዎርልድ ቡሌቲን ዘግቧል፡፡ ቤተ-እስራኤላውያኑ ከዚህ ቀደም በእስራኤል መንግሥትና ቀድመው እስራኤል በገቡ ዜጎች ከተለያዩ ማኀበራዊ የመንግሥት አገልግሎቶች ጭምር ይገለሉ እንደነበር መዘገቡ አይዘነጋም፡፡