የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

∙ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል

z9

በሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው 6ቱ የዞን 9 ብሎገሮችና 3ቱ ጋዜጠኞች ዛሬ የካቲት 11 ቀን 2007 ዓ.ም ለ20ኛ ጊዜ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም ተከሳሾች ከችሎት እንዲነሱ አቤቱታ ያቀረቡባቸው ሰብሳቢ ዳኛ ሳይቀየሩ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም ከሁለተኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉ ጀምሮ እያንዳንዳቸው ‹‹በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም?›› የሚል ጥያቄ እየቀረበላቸው ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡

በዚህ መሰረት ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ እንዳልፈጸሙ ለችሎቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ 2ኛ ተከሳሽ በፍቃዱ ኃይሉን ጨምሮ ተከሳሾቹ ክሱን በተደጋጋሚ ቢያነቡትም ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ቢገልጹም የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠት እንዳለባቸው ተገልጾ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ናትናኤል ፈለቀ የተጠቀሰውን ክስ እንዳልፈጸመ በመግለጽ “ህግ የተከበረበት ሀገር ቢሆን ኖሮ በእኔ ቦታ ከሳሾቼ ነበሩ መቆም ያለባቸው” ብሏል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን አስረድተዋል፡፡ 10ኛ ተከሳሽ ተስፋለም ወልደየስ በበኩሉ፣ “እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፤ ጋዜጠኝነት ወንጀልም ሽብርም አይደለም፡፡ ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲል ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያሰማ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ከመጋቢት 21-23  ቀን 2007 ዓ.ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት ቀጠሮ መስጠቱን የነገረ-ኢትዮጵ ዘገባ አመልክቷል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: