ከጥር 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የኃይማኖት ነፃነት መብትና ህገ-መንግሥቱ እንዲከበር፤ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሙስሊሙ ማኀበረሰብ የመንግሥትን ህገወጥ እርምጃ ተቃውሞ መቀጠሉን ተከትሎ፤አሁንም በያዝነው የካቲት 2007 ዓ.ም. ከየቤቱና ከስራ ቦታ ጭምር የጅምላ እስሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የክልል ከተሞች የሚመጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ የመንግሥትን ያይል እርምጃ እና የኃይማኖት ነፃነት መብታቸው እንዲከበርና መንግሥትም ከኃይማኖት ጣልቃ ገብነት እንዲወጣ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሰሞኑን የጅምላ እስር እየተካሄደ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የጅምላ እስሩ እየተከናወነ የሚገኘው መንግሥት በመጪው ምርጫ 2007 ዓ.ም. ከሙስሊሙ ማኀበረሰብ ድጋፍ እንደሌለው በመረዳቱና በርካቶችም የድምፅ መስጫ በረቀት መውሰዳቸው የደረሰው መረጃ አስደንግጦት እንደሆነ ቢጠቆምም፤ ከመንግሥት በኩል ግን እየተወሰደ ስላለው የጅምላ እስር የተሰጠ ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተለይ ሰሞኑን በተወሰደውና እየተወሰደ ባለው የጅምላ እስር ተጠናክሮ መቀጠሉን ከመጠቆም ባለፈ፤እስካሁን ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡
ከዚህ ቀደም መንግሥት የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጋር ሲደራደር ቆይቶ፤ በመጨረሻም በጅምላ በማሰር የሽብር ክስ መስርቶባቸው የኮሚቴው አባላት ያለምንም ፍትህ እስካሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡