ግሩም ተ/ኃይማኖት
(ከየመን)
በየመን ሰነዓ ያለ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥሪ አስተላለፈ፡፡ “..አሁን በየመን ውስጥ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው፡፡ ማኛውችሁም ወደ ሀገር መግባት የምትፈልጉ ዜጎች ሁሉ ተመዝገቡ እና ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ፡፡ ችግር በሚነሳ ሰዓት ወደ ሀገር እንድትገቡ ኤምባሲው አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዜጎቹን በትኖ ኤምባሲው ስለማይዘጋ አለን…ተመዝገቡ፤ እስከ መጨረሻው ዜጋዎቻችንን ሳናወጣ ኤምባሲውን አንዘጋም…” ማለታቸው በየመን በስደት ለሚኖሩ ኢትዮጵውን ደስታ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የመን ያለችበት የከፋ የፖለቲካ ውጥረት አስፈሪ እና በከፍተኛ ሁኔታ የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከትላ ተብሎ ተፈርቷል፡፡ አንዳንዶች ከሶማሊያ በከፋ ሁኔታ በዘር፣ በጎሳ የመከፋፈል ግጭት ይካሄዳል ብለው ይገምታሉ፡፡ በእርግጥም አይቀሬ አይነት እየሆነ ነው ያለው፡፡ ከ16 በላይ ኤምባሲዎች ዘግተው ወጥተዋል፡፡ UNHCR ስደተኛውን በትኖ ሰራተኞቹን አውጥቷል፡፡ ጥቂት የመናዊያን ሰራተኞች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ማንኛውም መንግስታዊ ተቋማት ወለም ዘለም፣ አገም ጠቀም አይነት ነው አስራራቸው፡፡ ፈራ ተባ እያሉ…ነው ሂደታቸው፡፡
ተቃውሞውና ድጋፉ በማይለይበት ሁኔታ ሰላማዋ ሰልፈኞች በከተማዋ በተለያየ አቅጣጫ ብቅ ጥልቅ ይላሉ፡፡ መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች እና የሁቲ አማጺሚሊሻዎች ከተማዋ ተወጥራ የሞት አረማሞዋን የምታዜም…የማትወልደው ምጥ የምታምጥ መስላለች፡፡ ይህ ሁኔታ ፍርሃት ያልፈጠረበት ሀገር ዜጋ የለም፡፡ አሜሪካን የመን ሰነዓ ከተማ ውስጥ የነበረውን ሼራተን ሆቴል ተከራይተው ወታደራዊ ቤዝ አድርገው የነበሩ ወታደሮቻቸውን አንስተው ኤምባሲውን ዘግተው ያላቸውን መረጃ ሁሉ አጥፍተው ወጥተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በሰው አልባ የጦር ጀት ታጅበው ነው የሄዱት፡፡ በሰላም ከየመን ምድር ወጥተዋል፡፡ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ዜጎቻቸውን የማውጣት ስራ ሰርተዋል እየሰሩም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኤምባሲም ዜጎቼ ሆይ ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በየመን በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
በየመን ሰነዓ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጥሪ አስመልክቶ ጋዜጠኛ ግሩም ከየመን “በእውነቱ ይህ እሳቤ ራሱ የሚያስመሰግን መሆኑ አይካድም፡፡ ሁሉ ዜጎቹን የበተነ ላለመሆን ይህ በጎ ጅምር ነው፡፡ ‘..ኑ!! ተመዝገቡ፡፡..’ የሚለው ጥሪ ለቦንድ ወይም ለእከሌ ልማት ማህበር ክፈሉ ለማለት ሳይሆን ህይወታችሁን አድኑ በመሆኑ ከልብ ያስመሰግናል፡፡” ሲል በፌስ ቡክ ገፁ አስፍሯል፡፡