ብስራት ወልደሚካኤል
በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመን የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በቅኝ ለመግዛት በያዝነው የካቲት 1888ዓ.ም. ባደረገው ወረራ በኢትዮጵውያን አርበኞች በአዋድዋ ላይ ድል የተደረገበት 119ኛ ዓመት በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውን እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዓሉ ምንም እንኳ በኢትዮጵውን የተገኘ ቢሆንም፤ በቅኝ ግዛት የነበሩ የአፍሪካ ሀገሮችና ሌሎችም ራሳቸውን ነፃ ማውጣት እንደሚችሉ ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረና በቅን የተገዙ ሀገሮች ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ዕድል እንደፈጠረላቸው በርካታ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ስለሆነም በዓሉ በተለይ ከኢትዮጵያ ባለፈ የጥቁሮች ድል ተደርጎም እየተቆጠረ ይገኛል፡፡
በወቅቱ ጣሊያኖች እጅግ ውድና ዘመን ያፈራውን የውጊያ መሳሪያ የተጠቀሙ ሲሆን፤በውጊያውም በጣሊያን በኩል በርካታ የጣሊያን ወታደሮችና ኢትዮጵውን ባንዳዎች ሲሰለፉ፤ኢትዮጵውያን ደግሞ ከተወሰኑ ጊዜ ያለፈባቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች በስተቀር ለውጊያው የተጠቀሙት ኋላ ቀርና በሀገር ውስጥ የተለመዱ መሳሪያዎችን ነበር፡፡
የጦርነቱም መንስኤ የውጫሌ ውል አንቀፅ 17 ሲሆን፤ ጣሊያን በውሉ ላይ በአማርኛውና በእንግሊዘኛው ትርጉም ሆን ብላ እንዲለያይ በማድረግ ኢትዮጵያን በቀላሉ በቅኝ ለመግዛት መነሳቷን ተክትሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በጦርነቱም በርካታ ኢትዮጵያውያን ምንም ተቀጥላና ልጥፍ የሌለበትን የሀገሪቱን አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀይ ደማቅ ሰንደቅዓላማ በመያዝ ፆታ፣ዕድሜ፣ቋንቋና ኃይማኖት ሳይገድባቸው ሀገራችንን ነፃ ለማውጣት ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ በእግርና በፈረስ በሚደረግ ረጅም አድካሚ ጉዞ የተሳተፉ ሲሆን፤ በጦርነቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከጣሊያን ጦርም እንዲሁ በርካታ ሰዎች ሲሞት ብዙዎች ተማርከው ከድሉ በኋላ በዓለም አቀፍ ስምምነት መሰረት ከእስር ተለቀዋል፡፡
ውጊያውን በአዋጅ በማስነገር የመሩትና ወደ አድዋ የሸዋን ጦር ይዘው የዘመቱት የወቅት የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒልክና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ሲሆኑ፤እንደየ ማዕረጋቸውም ከተለያየ የሀገሪቱ አቅጣጫ ያለውን ጦር ይመሩ የነበሩ የተለያዩ የጦር አመራሮችም ንጉሱን በመከተል በአድዋው ጦርነት ላይ ተሳትፈው ሀገሪቱንና ህዝቧን ከቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተዋል፡፡ ይህንንም ድል ሆነ ተሳታፊዎችን ማንም፣ መቼም በምንም ሊሽር በማይችል መልኩ በዓለም ታሪክ ሰፍሮ እንዲህ እየተዘከረ ይገኛል፡፡
በተለይ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ራስ ጎበና፣ የጦር ሚኒስትሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲ-ነግዴ፣ራስ አሉላ አባነጋ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ አባተ፣ራስ መንገሻ ስዩም፣ ባሻ አዋዓሎም (የጠላትን ጦር በመሰለልና መረጃ ለንጉሱ በመስጠት)፣ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ (የአጼ ኃይለስላሴ አባት፤ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲውን በብቃት በመወጣትና የሐረርን ጦር በመምራት፣ የወሎው አስተዳዳሪ ራስ ዓሊ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባሳፎ (ባልቻ አባ ነፍሶ)፣ ራስ አባተ ቧ ያለው፣…እና ሌሎችም ግንባር ቀደም የጦር አመራሮች ከነወታደሮቻቸው ከፍተኛ ተጋድሎ በመፈፀም ለዛሬው የኢትዮጵያና ለመላው ጥቁር ወርቃማ የድል ታሪክ አብቅተዋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያውያን በተገኘው ተጋድሎ የድሉ ታሪክም በአፍሪካና በመላው ዓለም ወርቃማ የጥቁር ድል ታሪክ ሆኖ በክብር ተመዝግቦ ይገኛል፡፡
ወርቃማ የህዝብ ታሪክ ዘመን ሳይሽረው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲህ እየተዘከረ ይኖራል፡፡ በትግሉ ዋጋ የከፈሉና የሰው አያቶቻችንን ነፍስ ፈጣሪ በገነት ያኑርልን፡፡
ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ፤ ክብር ለአድዋ ጀግኖች፣ ክብር ለነፃነት ላበቁን አባቶቻችን እና እናቶቻችን!!