በኬንያ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ጋሪሳ የሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ ሐሙስ ጠዋት መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ግቢ ውስጥ በመግባት በከፈተው ጥቃት ሁለት የዩኒቨርስቲው ጠባቂዎችን፣ሶስት የፖሊስ ኦፊሰሮችን እና 142 ተማሪዎች በአጠቃላይ 147 ሰዎች መገደላቸውን የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆሴፍ ነካይዘሪ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል፡፡ በጥቃቱ ከሟቾች በተጨማሪ 79 ተማሪዎች የቆሰሉ ሲሆን፤ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ በታጣቂው ኃይል ታግተው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በፖሊስ እጥረት ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ መክፈል የለብንም በማለት ከፍተኛ የፖሊስ ቁጥር እንዲጨምርና ወደስልጠና እንዲገቡ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አደጋው በደረሰ ቀን ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡ የሶማሊው ታጣቂ አልሸዓባብ በኬንያ ንፁሃን ላይ የሚያደርሰው ጥቃት እየተበራከተ ሲሆን፤ ከዚህ በፊት በናይሮቢ ዌስትጌት የንግድ ማዕከል ውስጥ በፈፀመው ጥቃት 67 ሰዎች መግደሉ ይታወሳል፡፡ ከዛም በኋላ የሐሙሱን የጋሪሳ ዩኒቨረድስቲ ኮሌጅን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በርካታ ጥቃቶችን መፈፀሙ ይታወቃል፡፡ የጥቃቲ ኢላማዎችም ሙስሊም ያልሆነ ማንኛውም አካል ሲሆን፤ በተለይ ክርስቲያኖች ላይ ጥቃቱ መጨመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
እንደ ሀገሪቱ ፖሊስ መጃ መሰረት ከ2004 ዓ.ም. እስከ ታህሳሥ 2007 ዓ.ም. ብቻ የአልቃይዳ ክንፍ በሆነው በሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ አልሸዓባብ የተገደሉ ኬኒያውያን ቁጥር 312 ደርሶ ነበር፡፡ በጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተፈፀመውን የጅምላ ግድያ ጨምሮ በሶማሊያው ታጣቂ አል-ሸዓባብ የተገደሉ ኬንያውያን 459 ደርሷል፡፡
በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ተማሪዎች ላይ ታጣቂው ከፈፀመው የጅምላ ግድያ በኋላ አራት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሲገደሉ፣ አምስት ተጠርጣሪ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር መዋላቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ውስጥ የተገደሉ ሰዎችን ማንነት ለመለየትና ወደ የቤተሰቦቻቸው ለመላክ አሰከሬናቸው ወደ ናይሮቢ መላኩም ታውቋል፡፡
ጋሪሳ ከናይሮቢ ሰሜን ምስራቅ 367 ኪሎ ሜትር ስትርቅ፤ ከኬንያ ሶማሊያ ድንበር ያላት ርቀት ደግሞ 147 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ የታጣቂ ቡድኑ በተመሳሳይ መልኩ በዩጋንዳ የትምህርት ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሞ፤ የዩጋንዳ የደህንነትና ፀጥታ አካላት የሀገሪቱን ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በላቀ በተጠንቀቅ ላይ ሆነው እንዲጠብቁ መደረጉንም የዩጋንዳ ከፍተኛ ፖሊስ ኦፊሰርን ጠቅሶ የአውስትራሊያው ኤቢሲ ዘግቧል፡፡
በተለይ ከጥቃቱ በስተጀርባ ዋና አቀናባሪና በጋሪሳ ከተማ የእስላማዊ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበር የተጠቆመው መሐመድ መሐሙድ የገደለ ወይም ያለበትን የጠቆመም እንዲሁም ይዞ ለሚያስረክብ የኬንያ መንግሥት ፖሊስ 215 ሺህ የአሜሪካን ዶላር (200 ሚሊዮን የኬንያ ሽንልንግ)እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል፡፡ ጥቃቱን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋነ ፀሐፊ ባን ኪ ሙንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማኀበረሰቦች ያወገዙት ሲሆን፤ ታጣቂው አልሸዓባብ በበኩሉ ድርጊቱ የፈፀመው ከኬንያ ጋ ጦርነት ውጊያ ላይ ስለሆንን ነው ማለቱን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል፡፡