በደቡብ አፍሪካ በያዝነው ሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በወደብ ከተማዋ ደርባን ጥቁር የውጭ አፍሪካውያን ነጋዴዎች ላይ የተቀሰቀሰው ጥላቻ የ6 ሰዎች ህይወትን እንዳጠፋ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ዘገባ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በሌሎች የአፍሪካ ጥቁር ዜጎች ላይ የተጀመረው ጥላቻ ከደርባን ከተማ ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የተዛመተ ሲሆን፤ ትናንት ቅዳሜ ጆሃንስበርግ ከተማ ላይ አንድ ሞዛምቢካዊ መግደላቸውን የተለያዩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
በጥቃቱ በብዛት ሰለባ የሆኑት የኢትዮጵያ፣ የሶማሌ፣የናይጄሪያ፣የሞዛምቢክ፣የዙምባቤና የማላዊ ዜጎች የገለፀ ሲሆን፤ ከተገደሉት መካከልም 3ቱ ኢትዮጵውን መሆናቸውን የተለያዩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ በጥቃቱ ምክንያት ኬንያ፣ ማላዊ እና ዙምባቤ ወዲያውኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወጣት የሞከሩ ሲሆን፤ በተለይ ዙምባቤ እና ቦትስዋና ዜጎቻቸው በሰላም እስኪወጡ ድረስ ከጥቃቱ ለመከላከል ልዩ የጦር ኃይል ወደስፍራው መላካቸው ተሰምቷል፡፡ ሞዛምቢክ በበኩሏ ዜጎቿና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያንን ለመታደግ ድንበሯን የከፈተች ስትሆን፤ ጥቃቱ ወዳለበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ዜጎቻቿን ለመታደግ ትራስፖርትና አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ስታቀርብ ተስተውሏል፡፡
በተለይ ናይጄሪያና የሶማሊያ መንግሥት ድርጊቱን ከማውገዝ አልፎ፤ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የተፈጠረውን ቀውስ በአስቸኳይ እንዲቆጣጠርና እንዲያቆም ማስጠንቀቂያ ጠይቀዋል፡፡ በናይጄሪያ በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የተፈረጀው ቦኮ ሃራም በበኩሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በናይጄሪያውያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በ24 ሰዓታት ውስጥ ማስቆም ካልቻለ በምዕራብ አፍሪካ ባሉ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲና ዜጎቿ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ከመዛት በተጨማሪ የደቡብ አፍሪካዋን ጆሃንስ በርግን ባግዳድ አደርጋታለሁ ሲል ማስጠንቀቁ አነጋግሯል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት በጥቃቱ የሞተው አንድ ኢትዮጵዊ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮረፖሬሽን አስታውቋል፡፡
በደርባን የተቀሰቀሰው በተለምዶ የውጭ ሀገር ዜጋን የመጥላት “ዜኖፎቢያ” ዘመቻ በአሁን ሰዓት ጋብ ያለ ቢመስልም፤ወደተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች መዛመቱንና ችግሩ ከከተማ ውጭ የሚሰሩ ሌሎች ጥቁር የአፍሪካ ዜጎች አደጋ ላይ መሆናቸውንና እስካሁንም የደረሰባቸውን ችግር ለማወቅ እንዳልተቻለም ተጠቁሟል፡፡ ድርጊቱንም የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማና የተለያዩ የሀገሪቱ ዜጎች በይፋ ቢቃወሙም፤የአመፁ ዋና ቀስቃሽ ተደርገው የተወሰዱት በደርባን ያሉት የዙሉ ጎሳ ንጉስ ጉድዊል በወቅቱ በአንድ መድረክ ባደረጉት የጥላቻ ንግግር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሬዘዳንቱ ጃኮብ ዙማ ልጅም ድርጊቱን የሚያበረታታ ነገር ከዚህ በፊት በሌላ መድረክ መናገራቸው እየተጠቆመ ይገኛል፡፡ በጥቃቱም ሁለት ጥቁር አፍሪካውያን ከነ ህይወታቸው በደቡብ አፍሪካውያን የተቃጠሉ ሲሆን ሌሎቹ ስለት ባላቸው መሳሪያዎችና በድንጋይ ተደደብድበው መገደላቸው ታውቋል፡፡
በተቀሰቀሰው የጥላቻ አመፅም የኢትዮጵያውንን ጨምሮ የበርካታ የጥቁር አፍሪካውያን ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ከዝርፊው የተረፉትም ተቃጥለዋል፡፡ ድርጊቱን ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ቢያወግዘውም ወደሌሎች ከተሞች መዛሙቱ አሁንም ስጋትን ጭሯል፡፡ በርካቶችም የንግድ ሱቆቻቸውን ጥለው በተለይ በደርባን ከተማ ጊዘየያዊ የስደተኛ መተጠለያ ጣቢያና በፖሊስ ጣቢያዎች እንደተጠለሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በተፈፀመ ተመሳሳይ ጥቁር አፍሪካውያን ስደተኞች በተሰማሩበት የንግድ ስራ ጥላቻ ከ60 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውንና የበርካቶች ሱቆችና ሌሎች የንግድ ተቋማት መዘረፋቸውን መረጃዎች አመለክተዋል፡፡
ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን አነስተኛ የንግድ ሱቅ በሚሰሩ አፍሪካውያን ላይ በጥላቻ ቢዘምቱም፤ለዛሬው ነፃነታቸው ያበቋቸው በዋናነት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አፍሪካውያን ትልቅ ሚና እንደነበራቸው አይዘነጋም፡፡