ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት በሊቢያ፣በደቡብ አፍሪካና በየመን ኢትዮጵያውያን በግፍ መገደላቸውን በተመለከተ በአዲስ አበባ ድርጊቱን ለማውገዝና ለመቃም ሰልፍ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፤ በሰልፍ የተገኙ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ተደብድበው ወደ አካባቢው ሆስፒታሎች የተወሰዱ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንም አልጀዚራን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከስፍራው በቀጥታ ዘግበዋል፡፡ በተለይ በአሸባሪው በ አይ ኤስ አይ ኤል (ISIL) ቢያንስ 28 ኢትዮጵያውያን በጭካኔ መገደላቸውና መንግሥትም ለዚህ ያሳየው ቸልተንነት ህዝቡን የበለጠ በማስቆጣቱ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ያለማንም ቀስቃሽ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለተቃውሞ ሰልፍ ቢወጣም መንግሥት ፈቃድ አልሰጠሁም በሚል በርካቶች ከደበደበ በኋላ ለሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ራሱ ድርጊቱን በመቃወም ሰልፍ ቢጠራም መጨረሻው በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባና እስር ተጠናቋል፡፡ ሰልፉ ከመጀመሩ በፊት የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ወደሰልፉ ሲሄዱ የታሰሩ ሲሆን፤ ከሰልፉ በኋላ የመንግሥት ባለሰልጣናት መስቀል አደባባይ ንግግር ሲያደርጊ ህዝቡ በልቅሶ ተቃውሞ ካሰማ በኋላ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ እዛው ሰልፉ ቦታ ሲደበድብ ታይቷል፡፡ ይሄንንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ አሰራጭተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ አሸባሪው ቡድን ISIL በሊቢያ የገደልኩት ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ቢልም፤ በአዲስ አበባው ተቃውሞ የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች በጋራ ድርጊቱን ሲያወግዙ ተስተውሏል፡፡ በዕለቱም በርካታ መፈክሮች የተሰሙ ሲሆን፤
ታርዷል ወገኔ፣ ታርዷል ወገኔ…(በኡኡታና ልቅሶ)
ሽብርን እንቃወማለን፣እናወግዛለን
መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም
ሞት ለወያኔ፤ ያረደንም ያሳረደንም ወያኔ ነው
ይለያል ዘንድሮ የዌኔ ኑሮ
ውሸት ሰለቸን፤ የወንድሞቻችን ደም ይመለስ
የሀገር ውስጥ ISIL ወያኔ ነው፤…በቃን
ISIL እስልምናን አይወክልም፤ እኛ የኢትዮጵያውያ ሙስሊሞች ወንድሞቻችን ክርስቲያኖች በአሸባሪ ቡድኑ መገደላቸውን አጥብቀን እናወግዛለን፤ ድርግቱም ሽብር እንጂ እስልምናን አይወክልም (በተለይ በሰልፉ የተገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች)
መንግሠት የሌለው እዚህ ብቻ ነው
የኢትዮጵ አምላክ ይፍረድ (በተለይ የሟቾቹ ቤተሰቦች)
ና ና መንጌ ና ና (የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን)
የቤት አንበሳ የውጭ እሬሳ (መንግሥትን) የሚሉ መፈክሮች ይገኙበታል፡፡
በመጨረሻም በመንግሥት ላይ የህዝቡ ተቃውሞ ተጠናክሮ ሲቀጥል የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግር በቅጡ ሳይሰማ የተቋረጠ ሲሆን፤ ፖሊስም ወዲያውኑ ያገኘውን ሁሉ እያሳደደ ሲደበድብ ለማየት ተችሏል፡፡ በቂርቆስ ሰፈር ልቅሶ ቤት አካባቢ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ መነሻ በስፍራው እጅግ በርካታ ፖሊሶች በስፍራው የነመበሩ ሲሆን፤ በኋላም ከፍተኛ የመሳሪያ ተኩስ ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በተተኮሰው ጥይት በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ስለማደረሱ የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም መስቀል አደባባይ በነበረው የፖሊስ ድብደባ ራሳቸውን ስተው የወደቁ ሴቶች፣እናቶችና ወጣቶች የታዩ ሲሆን፤ ብዙ ወጣቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአምቡላንስ እና በሰው እግዛ ወደ ህክምና ጣቢያ ሲሄዱና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ታይቷል፡፡
መንግሥትም በተመሳሳይ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሽብር ድርጊቱን በመቃወም በመዋቅሩ ሰልፍ ማዘጋጀቱና ለዚህም የኢህአዴግ ሊግና ፎረነም አባላት ከየቀበሌው በነበረው መዋቅር ወደሰልፍ እንዲወጡ፣ ሌላ ወደተቃውሞው ሰልፍ የሚመጣ ካለ በደንብ ከበው እንዲከታተሉት፣ መፈክሮችም በኢህአዴግ ብቻ እንዲዘጋጅ ከዛ ውጭ ያለ መፈክር ይዞ የሚመጣ ማንኛውም አካል ካለ ወደሰልፉ መሐል ከመቀላቀሉ በፊት ጥብቅ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ትዕዛዝ መሰጠቱንም ምንጮች ለአዲስ ሚዲያ ገልፀዋል፡፡
በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ቀደም ሲል የሽብር ድርጊቱን በማውገዝ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ በፌስ ቡክ ግድግዳቸው ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢናገሩም፤ በመጨረሻም አሸባሪው ድርጅት ላይ በመንግሥት እርምጃ ይወሰዳል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በአዲስ አበባ ሰልፈኛ ላይ እርምጃ ሲወስድ ታይቷል፡፡ መንግሥት በበኩሉ እርምጃ የተወሰደው ፖሊሶች ላይ ድንጋይ ስለተወረወረ ነው የሚል ምክንያት ሰጥቷል፡፡
በተለይ በሊቢያ የሟቾች ማንነት እየተለየ ሲሆን፤ ስማቸውም ኢያሱ ይኮኖአምላክ፣ ባልቻ በለጠ፣ ብሩክ ካሳ፣ በቀለ ታጠቅ እና ኤልያስ ተጫኔ ከአዲስ አበባ ቂርቆስ ሰፈር፤ መንግሥቱ ጋሼ እና አወቀ ገመቹ ከወለጋ ነቀምት፣ በቀለ አርሰማ ከጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ካራቻ አካባቢ፣ የጅማ ዩኒቨርስቲ ምሩቅ የነበረው ዳንኤል ሓዱሽ፣ አለም ተስፋይ እና ዳዊት ሀድጉ ከትግራይ መቀሌ አካባቢ፣ ክርስቲያን ወንድሞቼን ለይታችሁ አትገድሉም፤ በእስልምና የሰውን ህይወት ማጥፋት ኃጥትም ወንጀልም ነው፣ እኔ ከእነሱ አልለይም በማለት ሲከራከር የነበረው ኢትዮጵዊው ሙስሊም ጀማል ረህማንም አብሮ መገደሉ ታውቋል፡፡ በአሸባሪው ቡድን ከተገደሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ተስፋይ ኪዳኔን ጨምሮ ሶስት ኤርትራውያንም እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን፤ በተለይ ተስፋይ ከዚህ በፊት በእስራኤል ጥገኝነት ጠይቆ በመከልከሉ በሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ሲሞክር በአሸባሪ ቡድኑ እጅ መግባቱ ተጠቁሟል፡፡