ባለፈው ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በገዥው ኢህአዴግ አሸናፊነት መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ እስካሁን ቦርዱ ደረሱኝ ባላቸው ከ547 ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ፤ 440 መቀመጫ ውጤቶች በሙሉ ኢህአዴግ ማሸነፉን ይፋ አድርጓል፡፡ ቀሪዎቹ 107 መቀመጫ ውጤቶች አሸናፊ በቦርዱ ባይገለፅም፤ የኢህአዴግ ደጋፊ መሆኑን በድረ-ገፁ የገለፀው “አይጋፎረም” ገና ምርጫው ሳይጠናቀቅና በይደር የታለፉ ጣቢያዎች እያሉ በምርጫው ዕለት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ኢህአዴግ 100 ማሸነፉን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ ድረ-ገፁ የመድረክ አንጋፋ ተወካዮች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሁሉም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች በመላ ሀገሪቱ ሙሉ ለሙሉ በኢህአዴግ መሸናፋቸውን ይፋ ያደረገውን መረጃ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ሊያነሳ ችሏል፡፡ ምርጫ ቦርድም ለጊዜው በቁጥር ካስቀመጠው መቀመጫ በስተቀር ምርጫው ሳይጠናቀቅ ቀድሞ የኢህአዴግን ማሸነፍ ይፋ ካደረገው አይጋ ፎረም የተለየ መረጃ እስካሁን ሊሰጥ አልቻለም፡፡
በምርጫው ዋዜማ እና ዕለት በተለይም ከገዥው ኢህአዴግ ጋር ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (መድረክ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ምርጫ ጣቢያዎች በደህንነት እና ፖሊሶችታስረውና ታግተው እንዳይታዘቡ መደረጋቸውን ፓርቲዎቹ ቀድመው ማሳወቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መድረክ እና ሰማያዊ ፓርቲ የምርጫውን ውጤትም ሆነ ሂደቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ በምርጫ 1997 ዓ.ም. በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽንፈት ገጥሞት ስልጣኑን ባይለቅም፤ በምርጫ 2002 ዓ.ም. 99.6 በመቶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማግኘቱን ይፋ ካደረገ በኋላ የነበረው የምርጫ ሂደትና ውጤት ላይ በሀገር ውስጥና ከውጭ የተለያዩ ቅሬታዎችን እና ትችቶችን ማስተናገዱ ባይዘነጋም፡፡
ምርጫውን የታዘበው የአፍሪካ ህብረት በሰጠው ጊዜያዊ መግለጫ ታዛቢ ቡድኑ ከታዘባቸው ከ21 በመቶ የማያንሱ የምርጫ ጣቢያዎች ኮሮጆዎች ድምፅ መስጠት ከመጀመሩ በፊት በዶ መሆናቸው ተከፍቶ እንዲታይታዛቢ ቡድኑ ቢጠይቅም፤ በየጣቢያው ያሉ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እና የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎቹ ተከታታይነት ያለው ቁልፎች እንዳልነበሩት በመግለፅ ምርጫው ነፃ ነበር ለማለት እንደሚቸገር አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያያን ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲታዘቡ የነበሩት የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካው ካርተር ማዕከል ምርጫ 2007 ዓ.ም. ሂደትን እንዳልታዘቡ ታውቋል፡፡
የእሁዱ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ውጤት ግን ከቀድሞው በባሰ 100 % የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያለምንም አማራጭ ሐሳብ በገዥው ኢህአዴግና አጋሮቹ ሊሞላ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ውጤቱም የህዝብ ድምፅ ዘረፋና ማጭበርበር እንዲሁም የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ በደረሰው ተፅዕኖ የመጣ እንጂ በነፃ ምርጫ የተገኘ የህዝብ ድጋፍ አይደለም በሚል ከወዲሁ ውግዘትና ትችት ገጥሞታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውጤቱ የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነትንም የበለጠ ጥያቄ ውስጥ ቢከትም፤ ውጤቱን አስመልክቶ ከዥው ፓርቲ በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋ መግለጫ የለም፡፡